1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት በድሬዳዋ ከተማ

ዓርብ፣ ሐምሌ 27 2010

በድሬዳዋ ከተማ ልዩ ስሙ «መልካ ጀብዱ» በተባለ ቦታ በትናንትናዉ ዕለት ግጭት ተቀስቅሶ ማምሸቱ ተገለፀ። አንድ የአካባቢዉ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት ግጭቱ ከማንነት ጋር የተያያዘ ነበር። የከተማዋ አስተዳደር ግን  ግጭቱ  ስለ መከሰቱ ምንም መረጃ እንደሌለዉ ገልጿል። 

https://p.dw.com/p/32b6U
Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

Conflict in Diredawa City - MP3-Stereo


በፍቅር ከተማነቷ የምትታወቀዉ የድሬደዋ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭቶች እየተስተዋሉባት መሆኑን ነዋሪዎቿ በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። በከተማዋ ባለፈዉ ማክሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2010 አ/ም «ገንደ ተስፋ »በተባለ አካባቢ በሶማሌና በአካባቢዉ ወጣቶች መካከል የንብረት ዉድመት ያስከተለ ግጭት ተከስቶ ነበረ ። በትናንትናዉ ዕለትም «መልካ ጀብዱ» በተባለ  አካባቢ ሌላ ግጭት ተቀስቅሶ ማምሸቱን ስማቸዉን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢዉ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

«ትናንት ማርማራት አካባቢ ድሬደዋ አካባቢ የጉርጉራና የኢሳ ወጣቶች ግጭት ተፈጥሮ ቤቶች ተሰብረዋል።»ካሉ በኋላ «ትናንት ማታም በገንደ ዉርሶ ሰፈር በሚባል አካባቢ እዚህ  መልካ ጀብዱ  ዉስጥ ማለት ነዉ።ያዉ ግጭት ተመልሶ ተከስቷል።»
እንደ ነዋሪዉ ገለፃ ግጭቱ  ከዚህ ቀደም በጉርጉራና በኢሳ የጎሳ አባላት መካከል ተከስቶ ከነበረ አለመግባባት ጋር የተያዘ ነዉ።

Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

«ያዉ ከአሁን በፊት የሆነ ልጅ ሞቷል።እና ሰዉ ሞቶብን እንዴት እንቀመጣለን በሚል መልኩ ይመስለኛል።የመበቃቀል አይነት አካሄድ ነዉ።»ካሉ በኋላ  እስካሁን የተጎዳ ሰዉ የለም ግን በድንጋይ ቤት የመደብደብ ነገር  ነበር።በዉል ግን እስካሁን ድረስ እዛ አካባቢ ለመድረስ የፌደራል ፖሊስ ከበዉ ነዉ ያሉት ።» ብለዋል።
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የድሬደዋ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ በየነ ፤ በትናንትናዉ ዕለት በመልካ ጀብዱ ተከሰተ ስለ ተባለዉ ግጭት መረጃ እንደሌላቸዉ ገልፀዉ፤ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረዉ የጉርጉራና የኢሳ ጎሳ አባላት ግጭት ግን በሽምግልና መቋጨቱን አብራርተዋል።

«ስለአሁኑ ዝርዝር መረጃ የለኝም።ከዚህ በፊት ቆይቷል በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ጥል እንደነበር እናዉቅ ነበር።ነገር ግን በወቅቱ በሀገር ሽማግሌዎች ተፈቷል።እኔ እስከማዉቀዉ መረጃ።።አሁን ግን ያኛዉን መነሻ አድርጎ ተፈጠረ ለተባለዉ እኔም እንደ አስተዳደርም የጠየኳቸዉ አካላትም መረጃ የላቸዉም።»ነዉ ያሉት። 
በዛሬዉ ዕለት ግጭቱ መብረዱን የሚናገሩት ነዋሪዉ የአካባቢዉ ኅብረተሰብ ከዚህ በፊት በፍቅር  ይኖር የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግለሰቦችን ጠብ ሳይቀር ወደ ብሔር ለማጠጋጋት ስለሚሞከር በነዋሪዎች ዘንድ ጉዳዩ ስጋት እየፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል። በመሆኑም መንግሥት ጉዳዩን በዘላቂነት እንዲፈታ ጠይቀዋል።
እንደ አቶ ፈቃዱ የድሬዳዋ ከተማ በርካታ ብሔርና ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ ከዚህ ቀደም ግጭት የከተማዋ መገለጫ ሆኖ አያዉቅም። ከዚህ የተነሳ አሁን እየተከሰቱ ባሉት ግጭቶች  ኅብረተሰቡ ስጋት ማንሳቱ ተገቢ መሆኑን ገልፀዉ የከተማዋ አስተዳደር በትናንትናዉ ዕለት መግለጫ ማዉጣቱም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል። «ከጊዜ ወደ ጊዜ በወጣቶች መካከል የሚፈጠሩ ረብሻዎች ህብረተሰቡን ስጋት ዉስጥ ከተዋል ትክክል ነዉ።ያም እንዳይሆን ነዉ በትናንትናዉ ዕለት መግለጫ ሲወጣ የነበረዉ።»ይሉና  የመግለጫዉን ትኩረት ይዘረዝራሉ። «መግለጫዉ የሚያተኩረዉ አንደኛ የድሬደዋ መልካም እሴት እንዲቀጥል ይፈለጋል፣ድሬደዋ የብሄር ብሄረሰቦች ከተማ መሆኗ፣ስለዚህ አንድ ነገር ሲፈጠር ወደ ብሄር እየተላከከ ብሄርና ብሄር እንዳይጋጭ፣ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ፣ሰላሙ እንዲጠበቅ ፤ወላጆች ልጆቻቸዉን እንዲጠብቁ»መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱ ብሔር ተኮር ግጭቶች የሕዝቡ ሳይሆን የፖለቲካ ነጋዴዎች ነዉ ማለታቸዉ የሚታወስ ነዉ። 

Stadt Dire Dawa in Äthiopien
ምስል Hailegzi Mehari

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ