1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትራምፕ ለቡድን 20 ስብሰባ ጀርመን ገቡ።

ሐሙስ፣ ሰኔ 29 2009

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራፕም በሰሜናዊ ጀርመን በሚካሄደዉን የቡድን 20 ጉባዔ ላይ ለመካፈል ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ ገቡ። ቡድን 20 በመባል የሚታወቀው በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ጠንካራ ኤኮኖሚ ያላቸው ሀገራት የሁለት ቀን ጉባዔ አርብ ሀሙቡርግ ውስጥ ይጀምራል።

https://p.dw.com/p/2g67z
G20 Gipfel in Hamburg | Donald Trump & Angela Merkel
ምስል Getty Images/AFP/M. Kappeler

Trump geht auf Distanz zu Russland - MP3-Stereo

ትራምፕ ወደ ጀርመን ከመምጣታቸዉ በፊት በፖላንድ አጭር ጉብኝት አድርገዋል። ትራምፕ በፖላንድ ዋርሶ ጉብኝታቸዉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ « አፍራሽ ባህሪ ያላት» ሲሉ ሩስያ ላይ ትችት አሰምተዋል።  

«አሜሪካ  በመካከለኛው ምስራቅ እና በምስራቅ አውሮጳ ውስጥ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ሆናለች። በሩሲያ  አፍራሽ ባህሪ  ላይ ምላሽ ለመስጠት ከፖላንድ ጋር እየሰራን ነው። ፖላንድ  የፋይናንስ ግዴታዎቻችን ከሚያሟሉ ጥቂት የኔቶ አባል አገሮች አንዷ በመሆኗ በምሳሌ የምትጠቀስና ነች፤ አመስጋኞችም  ነን። »

ትራምፕ ይህን የተናገሩት ዋርሶ ላይ ከፖላንዱ ፕሬዚዳንት አድሬዚጅ ዱዳ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነዉ። የፕሬዚዳንት ትራምፕን ወቀሳ ተከትሎ  « ይህን አይነቱን አቀራረብ አንቀበልም፤ በዚህም ምክንያት የሁለቱ ሃገራት ፕሬዚዳንቶች ፊት ለፊት እስኪገናኙ እንጠብቃለን » ሲል ሞስኮ የሚገኘዉ የፕሬዚዳንታዊዉ ቢሮ አንድ ቃል አቀባይ መግለፁ ታዉቋል።  ትራምፕ በሃምቡርግ በሚካሄደዉ የቡድን 20 ጉባዔ ላይ ቭላድሚር ፑቲንን ለመጀመርያ ጊዜ ያገኝዋቸዋል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነዉ። በአዉሮጳ የሦስት ቀናት ፖለቲካዊ ዉይይታቸዉን ዛሬ ፖላንድ ላይ የጀመሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል  ጋር ሃምቡርግ ከተማ ዉስጥ ተነጋግረዋል። ትራምፕ በዚሁ ቆይታቸዉ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ እና ከደቡብ ኮርያዉ ፕሬዚዳንት ሙን ጃይ ኢን ጋር በሰሜን ኮርያ ጉዳይ እንደሚነጋገሩም ታዉቋል። የቡድን 20 ጉባዔን የምታስተናግደዉ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጉባዔዉ ላይ ለመገኘት ጀርመን የመጡ የተለያዩ  ሃገራት ርዕሳነ ብሔራትና መራህያነ መንግሥታትን ተቀብለዉ እያነጋገሩ ነዉ። ቡድን 20 በመባል የሚታወቀው በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ጠንካራ ኤኮኖሚ ያላቸው ሀገራት የሁለት ቀን ጉባዔ አርብ ሀሙቡርግ ውስጥ ይጀምራል።

G20 Gipfel in Hamburg | Donald Trump & Angela Merkel
ምስል Reuters/M. Schrader

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ