1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩኤስ አሜሪካና ብሪታንያ ላይ እምነት የለንም«ሜርክል»

ሰኞ፣ ግንቦት 21 2009

በኢንዱስትሪ የበለፀጉትን የዓለም ሃብታም ሃገራትን የሚያስተናብረዉ የቡድን ሰባት ጉባዔ ከተበተነ በኋላ አዉሮጳ በዩኤስ አሜሪካና ብሪታንያ ላይ እንደማይተማመን የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ገለፁ። ሜርክል ይህን የገለፁት ትናንት እሁድ ሙኒክ ጀርመን ዉስጥ በተካሄደ የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2dmF9
München Bierzeltauftritt von Angela Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/S. Hoppe

Merkel_ Europa muss sein Schicksal in die eigene Hand nehmen - MP3-Stereo

 

በሌላ በኩል በመጪዉ ዓመት መስከረም ወር ጀርመን በምትካሂደው ምርጫ ከመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር የሚፎካከሩት የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ እና እጩ መራሄ መንግሥት ማርቲን ሹልስ በበኩላቸዉ ምርጫም ኖረ አልኖረ፤ በጉባኤው ወቅት ትራምፕ ለአንድ በነጻ ምርጫ ሥልጣን ለያዘ የጀርመን መሪ ያሳዩት ባህርይ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ታኦርሚና ኢጣሊያ  ለሁለት ቀናት የተካሄደዉና ባለፈዉ ቅዳሜ ምሽት በተጠናቀቀዉ የቡድን ሰባት ጉባዔ ዉጤት ማዘናቸዉን የተናገሩት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትናንት ሙኒክ ጀርመን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የክርስትያን ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ /CDU/ እና እህት ፓርቲዉ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ  /CsU/   የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ባደረጉት  ንግግር የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያን አጋርነትን ጥያቄ ውስጥ ከተዋል። በኢንዱስትሪ የበለፀጉትን የዓለም ሃብታም ሃገራትን የሚያስተናብረዉ የቡድን ሰባት ጉባዔ ከተነጋገረባቸዉና አጨቃጫቂ ከተባሉት ርእሶች መካከል፤ አምና ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ፊርማቸዉን ያኖሩት አባል ሃገራት የዓለም የሙቀት አማቂ ጋዞች  ቅነሳን ገቢራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸዉ ነዉ። በጉባዔዉ ከተቀመጡት ቡድን ሰባት አባል ሃገራት መሪዎች መካከል ስድስቱ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የተገባዉን ዉል ገቢራዊ ለማድረግ ሲስማሙ፤ በጉባዔዉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙት አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን አልተቀበሉትም።  ሜርክል ትናንት ከእንግዲህ በሌሎች ላይ ያለን ተስፋ ጠቧል ነዉ ያሉት።

Belgien Nato-Gipfel | Trump und Merkel
ምስል picture alliance/dpa/K. Nietfeld

«ከእንግዲህ በኋላ በሌሎች ላይ ተስፋ የምንጥልበት ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ጠቧል። ሁኔታዉን ባለፉት ቀናቶች ያየነዉ ነዉ። ስለዚህም እኛ አዉሮጳዉያን የራሳችንን እድል በራሳችን መወሰን ይኖርብናል። እርግጥ ነዉ በተቻለዉ ሁሉ ከዬናይትድ ስቴትስ ጋር በጥሩ ወዳጅነት፤ ከብሪታንያ ጋር በጥሩ ጉርብትና እንቀጥላለን፤ ከሩስያ እና ከሌሎች ሃገራትም ጋር እንዲሁ ።  ነገር ግን እንደ አዉሮጳዊ ማወቅ ያለብን ፤ ለወደፊት እድል እጣ ፋንታችን መዋደቅ ያለብን ራሳችን ነን። ይህንንም ከናነተ ከሁላችሁ ጋር በጋራ ተግባራዊ ማድረግ እፈልጋለሁ»   

በመጪዉ ዓመት መስከረም ወር ጀርመን በምታካሂደዉ ምርጫ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን የሚፎካከሩት ፤ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ እና የፓርቲው እጩ መራሄ መንግሥት ማርቲን ሹልስ በበኩላቸዉ፤ ጀርመናዉያንን በየቦታዉ የሚወክሉት መሪ በአንድ አምባገነን ሰዉይ በእኩይ መያዛቸዉ ተቀባይነት የለዉም ብለዋል።

«ሃገራችንን ለማስተዳደር በነጻ ምርጫ የተመረጠ መራሂተ መንግሥትም ሆነ መራሄ መንግሥት በእንዲህ ዓይነት መንገድ እንዲዋረድ እንድትዋረድ መፈቀድ የለበትም ስል አፅኖት ሰጥቼ መንገር እፈልጋለሁ። ሰውየው አምባገነን መሪ እንደሚያስበው ብረስልስ ላይ አዋርዳቸዋለሁ ብለው አምነዋል። ምርጫዉ ኖረም አልኖረም በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ ግልጽ ማድረግ የምፈልገዉ ፤ መራሂተ መንግሥትዋ በሁሉም ጉባዔና ስብሰባዎችን እኛን ሁላችንንም ነዉ የሚወክሉን። ስለዚህ ሰውየው የሀገራችን መንግሥት መሪን በዚህ መንገድ መግለፃቸው ተቀባይነት  የለውም ።»

ከትራምፕ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መስማማት የልተቻለበትን ጉባዔን በተመለከተ ሜርክል ጉባኤው እንደተጠናቀቀ በሰጡት መግለጫ ቅር መሰኘታቸዉና ጉባዔዉ ምንም ዓይነት አጥጋቢ ነገር ያልታየበት ሲሉ ተናግረዋል።    

Berlin SPD-Chef Martin Schulz nach NRW Landtagswahl
ምስል Getty Images/AFP/J. McDougall

«ሦስተኛ፤ ስለ አየር ንብረት የተደረገዉ ዉይይት በሙሉ በጣም አስቸጋሪ ነበር። የማያረካ ነበር።ስድስት የአዉሮጳ ኅብረት ከተጨመረ ደግሞ ሰባት ለ አንድ ነን። ይህ ማለት ዩናይትድ ስቴትስ የፓሪስን ስምምነት ማክበር አለማክበሯ እስካሁን ግልፅ አይደለም።ስለዚህ እኛ ዙሪያ ጥምጥም አልሄድንም በግልፅ ነዉ ያስታወቅነዉ። ከቡድን ሰባት አባል መንግስታት እኛ ስድስታችን እና የአዉሮጳ ኅብረት ለዕቅዱ ግብ መምታት የምንሰጠዉን ድጋፍ እንቀጥላለን።»   

ባለፈዉ ቅዳሜ ከተጠናቀቀዉ የቡድን ሰባት ጉባዔ በኋላ በወጣዉ የጋራ የአቋም መግለጫ መሰረት ዩናይትድ ስቴትስ የአየር ንብረት መርሕዋን በመከለስ ላይስ በፓሪሱ ስምምነት ላይ ያላትን አቋም አሁን ማሳወቅ አልፈለገችም። ትራምፕ በትዊተር ባስተላለፉት መልክታቸዉ ፤ ሃገራቸዉ አምና ፓሪስ ላይ ከተደረሰዉ ስምምነት መዉጣት አለመዉጣትዋን በዚህ በያዝነዉ ሳምንት ቁርጡን አሳዉቃለሁ ብለዋል። ትራምፕ ለስደተኞች  ድጋፍ መስጠት እና የንግድ ልዉዉጥን የተመለከቱት የጉባዔዉን የመነጋገርያ አጀንዳዎች የተቀበሉት ከብዙ ሙግት በኋላ መሆኑም ተዘግቦአል። በዚህም አለ በዛ የጀርመኗ መራሂተ መንስት የአማሪካንን አጋርነት በጥርጣሪ መያዛቸዉን በይፋ ተናግረዋል። ታዋቂ ፖለቲከኞችም የዶናልድ ትራምፕን ፈር የለቀቀ ሥነ ምግባር በአንድ ድምፅ አይሆንም ያሉት ይመስላል።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ