1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በጀመረችው 2010 ዓ.ም. የፖለቲከኞቹ ተስፋ እጅጉን የተራራቀ ነው።

ሰኞ፣ መስከረም 1 2010

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አዲሱን አመት ሲቀበሉ ተስፋ እና ምኞታቸው እጅጉን የተራራቀ ነው። ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዋዜማው ባደረጉት ንግግር በአዲሱ አመት መንግሥታቸው "የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት" ጠንክሮ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2jkBA
Äthiopische Flagge und Polizist
ምስል DW/J. Jeffrey

አዲስ አመት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒሥትር ሐይለማርያም ደሳለኝ እና ኢሕአዴግ አብዝቶ የፈተናቸውን እስከ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድረስም ያንደረደራቸውን 2009 ዓ.ም. ተሰናበቱ። የኢትዮጵያ መንግሥት በዋዜማው ባዘጋጀው ድግስ ጠቅላይ ሚኒሥትሩ በእርግጥ የጸጥታ መደፍረስ በተጫነው 2009 ዓ.ም. የገጠሟቸውን ፈተናዎች አልጠቀሱም። ጠባሳዎቹንም ዘለዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒሥትሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታደሙት እና በቀጥታ የቴሌቭዥን ሥርጭት በተላለፈው ንግግራቸው ስለ መቻቻል እና አንድነት ሰብከዋል። 

"በጥላቻ ፍቅርን፤በመገፋፋት ፋንታ መደጋገፍን፤በመለያየት ፋንታ መቀራረብ እና አብሮነትን፤በመናቆር ፋንታ መቻቻል እና አንድነትን ማሰብ ማሰብ መለማመድ እና መተግበር እናም እነዚሁ የቀደሙ ኢትዮጵያዊ እሴቶች በመከራ ውስጥም ቢሆን ተፈትነው የወጡ በወርቅ የነቸሩ ባሕሎቻችንን ማዳበር ይገባናል።"

ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመንግሥታቸውን ውጥኖች ከግብ ለማድረስ የአገሪቱ ዜጎች "ያልተቆጠበ" ያሉትን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል። በየእንኳን አደረሳችሁ ንግግራቸው እንሰራቸዋለን ያሏቸው ቃል-ኪዳኖችም ነበሯቸው። 

Äthiopien Anti-Regierungs-Protesten
ምስል REUTERS/T. Negeri

"ለጋው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችን ሁሉንም የአገራችንን የሕብረተሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሳተፈ መልኩ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የጀመርንውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን። ሰላማችን እንዲረጋገጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የጀመርንውን የጸረ-ሙስና ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን።"

ዶ/ር ያዕቆብ ሐይለማርያም ኢትዮጵያ አዲሱን አመት ስትቀበል እንደ ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ተስፈኛ አይደሉም። "ብዙም የሚባል ነገር የለም" የሚሉት የሕግ ባለሙያ በአሮጌው አመት የተከሰቱ ኩነቶችን እያስታወሱ ይብሰለሰላሉ። የበርካታ ሰዎች ህይወት ያለፉባቸው፤አካል የጎደለባቸው የቆሼ እና የኢሬቻን የመሰሉ አደጋዎች ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖች ተጠያቂ አለመሆናቸውን እያነሱ ይተቻሉ። ጠቅላይ ሚኒሥትሩ የጠቀሱት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲህ በቅርበት ለመምጣቱም እርግጠኛ አይደሉም። 

"ከሌላው ዓመት ምንም የተለየ ነገር አያደርገውም። በነበረው ሁኔታ የሚቀጥል ነው። አገሪቷ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ነው ያለችው። ፓርቲው አንድ ፖሊሲ አለው ያንን ፖሊሲ መቀጠሉ አይቀርም። መድብለ-ፓርቲ በሌለበት ሥርዓት ብዙ ለውጥ አይታይም። መጀመሪያ ፓርቲው ዓላማውን ይቀርፃል። ያንን ዓላማውን እና ግቡን ይገፋበታል። ብዙም ጊዜ አዲስ ነገር አያመጣም። ደግሞም እንዲህ እንዲያደርግ የሚገፋፋው ሌላ ፓርቲ እስከ ሌለ ድረስ ያ ፓርቲ በጀመረው መስመር ይቀጥላል። አሁን ኢሕአዴግም በጀመረው መስመር ነው የቀጠለው። የተለወጠ ነገር የለም። የሚለወጥም ነገር አይኖርም።"

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው መልካም ምኞት መደርደር ከባድ አልነበረም ሲሉ ይናገራሉ። አገሪቱ ገጥመዋታል የሚሉትን ውስብስብ ችግሮች እየጠቀሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨባጭ መፍትሔ ለማበጀቱ ግን እርግጠኛ አይደሉም። 

Äthiopische Volksgruppe der Oromos
ምስል picture alliance/WILDLIFE

"አሁን ያሉብን ችግሮች ብዙ ናቸው። ስለ ፍቅር ስለ ሰላም ማውራት የሚቻለው ከአሁን በፊት በግፍ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ፈቃደኝነት ቢገኝ ኖሮ {ነበር}። የተራቡ ወገኖቻችን በልተው ማደር የሚችሉ ከሆነ፤ አሁን በድንበር ምክንያት በየቦታው እየተዋደቁ ደም እየፈሰሰ ዜጎች በሰላም እጦት በሚቸገሩበት ጊዜ፤የኑሮ ውድነቱ ጣራ በነካበት ሁናቴ፤ሕዝባችን በመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ላይ ባለበት፤ሙስና በተንሰራፋበት፤ሥርዓቱ በቁርጠኝነት ዴሞክራሲያዊ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ በተሳነበት ሁኔታ ላይ ነው ያለንው። ስለዚህ መጪው ዓመት እግዚያብሔር ከፈቀደ እነዚህ ሁሉ የሚስተካከሉ እና ለሕዝባችን ሰላም ፍትኃዊ አንድነት ሁሉ እኛ እንመኛለን። ግን ይኼ ባልተቀረፈበት ነው አሁን ያለንው።"

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ እንደ አቶ ሙላቱ ሁሉ ያለፈው ዓመት ፈታኝ እንደነር ይስማማሉ። እርሳቸው ያለፈው ዓመት ተቃውሞ የአገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት ለማሻሻል ሁነኛው መንገድ እንደሆነ ያምናሉ።

"በሚመጣው አመት ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ የማስበው ሕዝቡ በሰላማዊ ትግል ሥርዓቱን በካርድ ለመቀየር ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ነው። ይቺ አገር እንደ አገር እንድትቀጥል፤ዜጎቿ በዴሞክራሲ መስመር እንዲጓዙ እና ዴሞክራሲ በአገሪቱ እንዲሰፋ ንቁ ተሳትፎ ቢኖረው ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።"

እሸቴ በቀለ 
ኂሩት መለሰ