1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ ኩባንያ ለታላቁ ኅዳሴ ግድብ 5 ተርባይኖች ሊያቀርብ ነው

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 2011

በውሉ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት አምስት ተርባይኖች ለሚያቀርበው እና የተከላ እና የፍተሻ ሥራዎችን ለሚያከናውነው የፈረንሳይ ኩባንያ 53.9 ሚሊዮን ዩሮ ይከፍላል። ተርባይኖች ከመገጠማቸው በፊት የዘገዩ የውሐ ማስተንፈሻ፤ የውሐ መቆጣጠሪያ፤ የጎርፍ በሮች ሥራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል።

https://p.dw.com/p/3Aw0V
Äthiopien Grand Renaissance Staudamm
ምስል Reuters/T. Negeri

የኢትዮጵያ መንግሥት ለኩባንያው 53.9 ሚሊዮን ዩሮ ይከፍላል

የፈረንሳዩ ጄኔራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ ለታላቁ ኅዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ የሚያስፈልጉ አምስት ተርባይኖችን ለማቅረብ፣ የተጓደሉ አቅርቦቶችን ለማሟላት እና የተከላ እና የፍተሻ ሥራዎችን ለማከናወን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውል ገብቷል። ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ላይ በተፈረመው ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ለኩባንያው 53.9 ሚሊዮን ዩሮ ይከፍላል። ኩባንያው ከዚህ ቀደም የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የስቲል ስትራክቸር ሥራዎች ሲያከናውን ከነበረው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የአቅርቦት ውል ነበረው።  በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ከዚህ ቀደም "ተርባይን ጄኔሬተሮቹ ከቀረቡ በኋላ ማን ነው የሚተክላቸው? የጎደለ እቃ ቢኖር ማን ነው የሚያሟላው? እቃዎቹ በአግባቡ መስራታቸውን፤ በአግባቡ መገጠማቸውን ማን ነው ፈትሾ እንዲሰራ የሚያደርገው የሚለው የስምምነቱ አካል አልነበረም" ሲሉ ተናግረዋል። የፈረንሳዩ ኩባንያ ጋር ሜቴክ የነበረውን ውል የሚቀይረው እና ባለፈው ሰኞ በተፈረመው ስምምነት መሠረት ጄኔራል ኤሌክትሪክ "ተርባይን ጄኔሬተሮቹን ያመርታል፤ አጓጉዞ አገር ውስጥ ያስገባል፤ ቀደም ሲል በነበረው ስምምነት መሰረት አገር ውስጥ ገብተው የነበሩ ተርባይን ጄኔሬተሮች ላይ የተጓደሉ አቅርቦቶችን ለይቶ የማሟላት ሥራ ይሰራል፤ ተከላ፤ የፍተሻ ሥራ ያከናውናል" ሲሉ አቶ ሞገስ አስረድተዋል።

ጄኔራል ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ መንግሥት የገባውን ውል የሚሰራው ኮምኔክስ ከተባለ ሌላ ኩባንያ ጋር በጥምረት ይሆናል። አቶ ሞገስ እንደተናገሩት ለኃይል ማመንጫ ከሚያስፈልጉት እና ጄኔራል ኤሌክትሪክ ከሚያቀርባቸው አምስት ተርባይኖች አራቱ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ስምምነት ከተፈረመባቸው አምስት ተርባይኖች መካከል ሁለቱ የግድቡ ግንባታ ከመጠናቀቁ በፊት ተገጥመው ኃይል ያመነጫሉ ተብሎ ነበር። እቅዱ ግን አሁን ውሉን የተነጠቀው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሬንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በገባበት ውጥንቅጥ ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ጦር ሥር ለነበረው ብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ሰጥቶት የነበረውን የሥራ ውል ያቋረጠው ባለፈው ነሐሴ ነበር።

Äthiopien Nil
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Asmare

የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሖሮ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ እንደተናገሩት በኃይል ማመንጫ ግንባታ ዘርፍ የከበረ ስም ያላቸው ኩባንያዎች ከሜቴክ ጋር በንዑስ ተቋራጭነት አስፈላጊ ግብዓቶች ለማረብ ውል ነበራቸው። አቶ ክፍሌ የፈረንሳዩ ጄኔራል ኤሌክትሪክ እና የጀርመኑ ቮይት ኩባንያዎች ቀደም  "የጎደሉ አቅርቦቶች ካሉ እንዲያቀርቡ ሁለተኛ ደግሞ ተክለው ፈትሸው እንዲያስረክቡ" መደረጉን ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ጄኔራል ኤሌክትሪክ ሞተሮች እና ተርባይኖች በማምረት የተካነ ስመ-ጥር ኩባንያ ነው። ግዙፍ ተርባይኖች፣ የኃይል ማመንጫ ግብዓቶች፣ ለኃይል ማመንጪያ የሚያገለግሉ መቆጣጠሪያዎች (Hydro Control Systems) እና ሌሎች ቁሳቁሶች ለደንበኞቹ ያቀርባል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብርሐም በላይ (ዶ/ር) ኩባንያዎቹ "ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው በሜቴክም በተወሰነ ስኬል እንዲሰሩ ሲደረጉ የነበሩ ተቋማት ናቸው። እነ ቮይልት፤ ጂኢ አልስቶም በዓለም ላይ የታወቁ ናቸው። ለእነሱ እየሰጠን ያለንው የጥራት ችግርም አያጋጥመንም። የጊዜ ጉዳይም በድርድር በታቀደ ጊዜ ላይ መጨረስ ይቻላል። ወጪውም በታወቀ ወጪ መጨረስ ይቻላል" ሲሉ የመንግሥታቸው ውሳኔ አዋጪ መሆኑን ገልጸው ነበር።

የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን በነበረበት የአቅም ውስንነት እና ገጥሞታል በተባለው ሙስና ምክንያት በርካታ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራዎች ተጓተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት ሜቴክ ለግንባታው 25 ቢሊዮን ብር ገደማ ተዋውሎ ሥራውን በአግባቡ ሳያከናውን 16 ቢሊዮን ብር ገደማ ተከፍሎታል። ለግንባታው ከታቀደው የባከነው አሊያም የተመዘበረው ገንዘብ መጠን እስካሁን በትክክል ባይታወቅም ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በርካታ የሜቴክ የቀድሞ ሹማምንት ፍርድ ቤት ቆመዋል።

Infografik Karte Grand Ethiopian Renaissance Dam ENG

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት የግድቡ የሲቪል ግንባታ 80 በመቶ ገደማ ሲገባደድ የኤሌክሮ ሜካኒካል ሥራው በአንፃሩ ከ30 በመቶ በላይ ፈቅ አላለም። ይሕ የግንባታ ሒደት አለመጣጣም ወደ ፊት በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ጭምር ጫና እንደሚያሳድር አቶ ሞገስ ይናገራሉ። አቶ ሞገስ "ተርባይን ጄኔሬተሮቹን ለመግጠም ከብረታ ብረት ሥራዎች ጋር የሚጠበቁ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ የውሐ ማስተንፈሻ፤ የውሐ መቆጣጠሪያ በሮች፤ የጎርፍ በሮች የዘገዩ እና መሠረታዊ የሚባሉ ሥራዎች ናቸው። እነዚህ ሥራዎች ካልተሰሩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን መግጠም አይቻልም" ብለዋል።

የግድቡን የሲቪል ሥራ የሚያከናውነው የጣልያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጊሎ ኩባንያ በግንባታ መዘግየት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን ገልጾ ተጨማሪ ክፍያ ጠይቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብርሐም በላይ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም የግንባታውን መጓተት አስመልክቶ በተሰራ ዘገባ ላይ ሳሊኒ ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ እንደጠየቀ ተናግረው ነበር።  ሳሊኒ ኢምፕሬጊሎ ኩባንያ  ያነሳቸው ጉዳዮች "በምን አይነት መንገድ መመለስ አለባቸው" የሚለውን ከዓለም አቀፍ የግንባታ ሕግጋት አኳያ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሟል ሲሉ አቶ ሞገስ መኮንን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ