1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፀጥታ ዉጥረት በኢትዮ-ሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ መንገሱ

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ግንቦት 20 2010

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ አለመረጋጋት ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/2yTIH
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

Conflict on Ethio-Som+Oro Reg border continued - MP3-Stereo

ካለፈዉ ረቡዕ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በጭናቅሳን ወረዳ በተለያዩ ቦታዎች ዳግም የተከሰተዉ ግጭት ለአራት ሰዉ ሞትና ከ250 በላይ ቤቶች መቃጠል ምክንያት መሆኑን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ለግጭቱ ተጠያቂ የአሮሚያ ሚሊሽያ ነዉ ሲሉ፤ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ ደግሞ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን አውግዟል።

በጭናቅሳን ግጭት በሁለቱም በኩል ሰዉ መሞታቸውን እና ንብረት መዉደሙን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ለንጮ ለአገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ ሶማሌ በኩል የታጠቀ ሃይል ለግጭቱ መንስዔ መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ኮማንድ ፖስቱን ለታየው የፀጥታ ችግር ተጠያቂ አድርገዋል።

ዶክተር ነገሪ፤ «መነሻዉ፤ ያዉ፤ ሰላም እንዲኖር የማይፈልጉ የታጠቁ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ሶማሌ በመምጣት በሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸዉ ነዉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የሁለቱም ክልሎች መንግሥታት ኮማንድ ፖስቱ አከባቢዉን እንዲቆጣጠርና በሁለቱም አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የነበሩት የታጠቁ ኃይሎች የተወሰኑ ኪሎሜትሮች እንዲርቁ ተስማምተው ነበር። ባካባቢው የታጠቀ ኃይል እንዳይንቀሳቀስ መቆጣጠሩ ለኮማንድ ፖስት ቢጠዉም ፣ በሰዉ ሕወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ኮማንድ ፖስቱ በዚህ ድርጊት የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር ማዋሉና ትጥቅም እንዳስፈታቸዉ ፣ ግን ዳግም በድብቅ የሚያስታጥቃቸዉ ምንጭ/አካል ስላለ የመከላክያ ኃይል ርምጃ እየወሰደ እንደሆነ መረጃ ደርሶናል።»

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የቁምቢ ወረዳ ነዋሪ መሆናቸዉን የገለፁት ግን ስማቸዉን እንዳጠቀስ የፈለጉ አንድ ግለሰብ ጭናቅሳንን ጨምሮ አማዩ ሙሉቄ፤ ሚዳጋንና ባብሌ ወራዳዎች ዉስጥ የፀጥታና የደህነት ስጋት መንገሱን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

በመስከረም ወር 2010 ዓ/ም ተመሳሳይ ችግር በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በመከሰቱ ለብዙዎች ሞትና መሰደድ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። በሁለቱም ክልሎች ባለስልጣናት በኩል የበለጠ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደርገነዉ ሙከራ አልተሳካም።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ