1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን መንግሥት የልማት ርዳታ እና ዛምቢያ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10 2011

ግዙፍ የሙስና ቅሌት በዛምቢያ ቁጣ ቀስቅሷል፤ ድንጋጤም ፈጥሯል። ይህን ተከትሎ ብሪታንያ እና ሌሎች አውሮጳውያት ሀገራት ለዚችው ሀገር የሚሰጡትን በሚልዮን የሚቆጠር የልማት ርዳታ አቋርጠዋል። የDW ባልደረባ ዳንየል ፔልስ ከበርሊን ዝንደዘገበው፣ የጀርመን መንግሥት ግን ይህን ርምጃ የመውሰድ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘውም።

https://p.dw.com/p/36qr3
Sambia Straßenhändler in Lusaka
ምስል DW/C. Mwakideu

የሙስና ቅሌት በዛምቢያ


ዛምቢያ በአርአያነት ትነሳ የነበረበት ጊዜ አክትሟል። ይሁን እንጂ ፣ ከዓለም ድሆች ሀገራት መደዳ አንዷ የሆነችው የዚችው አፍሪቃዊት ሀገርዛምቢያ ህዝብ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይፋ በሆነው የሙስና ቅሌት አስቆጥቷል። በመጨረሻ በወጡ ዘገባዎች መሰረት፣ የዛምቢያ መንግሥት ሰራተኞች ላለፉት ብዙ ዓመታት ወዲህ የመንግሥቱን ንብረት ልክ እንደራሳቸው ሀብት ሲጠቀሙበት መቆየታቸው ተገልጿል።  ሁነኛ መረጃ ባማቅረብ የሚታወቀው የብሪታንያውያኑ መጽሔት  አፍሪካ ኮንፊዴንሺያል እንደዘገበው፣ በሚልዮን የሚቆጠር ዩኤስ ዶላር በሙሰኛ ውሎች የት እንደገባ ሳይታወቅ ባክኖ ቀርቷል። በዚሁ ተግባር የጠፋው ገንዘብ መጠን ገና በግልጽ አልታወቀም። ይሁን እንጂ፣ በመገናኛ ብዙኃን የቀረቡት መረጃዎች እጅግ አስደንጋጭ ናቸው። ለምሳሌ የመንግሥት ሰራተኞች ለይስሙላ በተቋቋሙ ኩባንያዎች እና በተጭበረበረ ሂሳብ አማካኝነት ከሀገሪቱ ትምህርት ሚንስቴር በጀት በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ መስረቃቸው ተመልክቷል። በዚሁ ድርጊታቸውም  አብዝቶ የተጎዳው ለችግረኞች የዛምቢያ ዜጎች ርዳታ የሚሰጠው የማህበራዊ ገንዘብ ማሸጋገሪያው መርሀ ግብር አራት ሚልዮን ዶላር አጥቷል። 
ብሪታንያ፣ ፊንላንድ፣ አየርላንድ እና ስዊድን ለዚሁ የዛምቢያ የማህበራዊ ገንዘብ ማሸጋገሪያው መርሀ ግብር ዋነኛ ርዳታ አቅራቢ ሀገራት ናቸው።  የዛምቢያ መርማሪዎች ይህ ቅሌት እንዴት እውን ሊሆን እንደቻለ የማጣራት ስራ ጀምረዋል። ይሁንና፣ ይህን የዛምቢያ ርምጃ  በቂ ሆኖ ያላገኙት ርዳታ አቅራቢዎቹ አውሮጳውያኑ መንግሥታት ለዚችው አፍሪቃዊት ሀገር የሚሰጡትን ድጋፍ አቋርጠዋል። ይኸው አሰራራቸውን በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታግ የተወከለው የተቃዋሚው ነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ፣ በምህጻሩ ኤፍ ዴ ፔ የልማት ፖሊሲ ቃል አቀባይ ክርስቶፍ ሆፍማን  ትክክለኛ ብለውታል።
« ሌሎች አየርላንድ እና  ስዊድንን የመሳሰሉ አውሮጳውያት ሀገራት፣ እንዲሁም፣ ሌሎች የብሪታንያን ርምጃ ተከትለዋል። ይህ አዲስ ነው። አውሮጳውያኑ በሙስና አንጻር ግልጽ አቋም የያዙበትን  ትብብር  የሚደነቅ ሆኖ አግንቼዋለሁ። »
ብሪታንያ ማንኛውንም ሙስናን በጠቅላላ በፍጹም በትዕግሥት እንደማታልፍ የብሪታንያ የልምት ትብብር ሚንስቴር ቃል አቀባይ ለ DW ተናግረዋል። ብሪታንያዊው ቃል አቀባይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ ሀገራቸው ለዛምቢያ በርዳታ የሰጠችው አራት ሚልዮን ዶላር ተመላሽ እንዲሆንላት መጠየቋን የብሪታንያ መገናና ብዙኃን አስታውቀዋል። በብሪታንያ አንጻር የጀርመን መንግሥት በዛምቢያ የተከሰተው ቅን ቅሌት ቀለል አድርጎ ተመልክቶታል። እንዲያውም፣ የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስቴር፣ በምህጻሩ ቤ ኤም ዜድ በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ፣ ከ70 የሚበልጡ የተለያዩ ጎሳዎች በሰላም የሚኖሩባት ዛምቢያ ባለፉት ዓመታት ፖለቲካዊ መረጋጋት የሰፈነባት ሀገር ሆናለች ሲል አድንቋል። በዚችው ሀገር የሚታየውን የሀይማኖት ነፃነት እና ሀገሪቱ የምትከተለው ሰብዓዊ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲንም አሞግሷል። በወቅቱ ብዙ ማነጋገር ስለቀጠለው የሙስና ቅሌት ግን በአንድም ቃል ሳይጠቅስ ነው የቀረው። በጀርመን የልማት ትብብር ፖሊሲ ውስጥ ዛምቢያ ዋነኛ ትኩረት ያገኘች ሀገር መሆንዋ ሲታሰብ ግን ይህ የሚያስገርም ነገር ሆኗል። እንዲያውም፣ የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስቴር፣ ከ2016 እስከ 2018 ዓም ድረስ  ለዛምቢያ  97,5 ሚልዮን  ዩሮ ለመስጠት እቅድ ይዞዋል። እንደ ሚንስቴሩ ድረ ገጽ፣  የቤ ኤም ዜድ ርዳታ በተለይ ያተኮረው በበውኃ አቅርቦቱ እና መልካም አስተዳደር በመትከሉ ስራ ላይ ነው። 
ምንም እንኳን በወቅቱ  በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር መጓደል ቢታይም፣  የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስቴር ለዛምቢያ የሚሰጠውን ርዳታ ለመቀጠል ወስኗል።  የጀርመን የልማት ትብብር ሚንስቴር ቃል አቀባይ  ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከ DW ለቀረበላቸው ጥያቄ በድምፅ ምላሽ መስጠት ባይፈልጉም፣ በጽሁፍ በላኩት አጭር መግለጫ ጀርመን የዛምቢያ መንግሥት ሰራተኞች አራት ሚልዮን ዶላር አጉድለውበታል የተባለው ለችግረኞች የዛምቢያ ዜጎች ርዳታ የሚሰጠው ማህበራዊ የድጎማ ገንዘብ ማሸጋገሪያው መርሀ ግብር በመርዳቱ ተግባር ላይ ከመጀመሪያውም እንዳልተሳተፈች አመልክተዋል።
ከብዙ ዓመታት ወዲህም ዛምቢያ በቀጥታ ወደ መንግሥት ካዝና የሚገባ የበጀት ድጋፍ፣ ማለትም ድህነትን ለመታገያ የምታውለው የልማት ርዳታ ከጀርመን እንደማታገኝም ቃል አቀባዩ አክለው አመልክተዋል። 
በዚህ ፈንታ የጀርመን የልማት ትብብር ሚኒስቴር  ከጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም ወዲህ ከሀገሩ የልማት ባንክ እና ከዓለም አቀፍ ትብብር ተቋም የሚያገኘው እና ለዛምቢያ የተሰጠው ርዳታ ለፕሮዤዎች ማራማጃ  እንደሚውል ገልጿል። እስካሁን በዛምቢያ ስራ በጀመረው፣ ማለትም፣ የውኃ አቅርቦቱን አስተማማኝ የማድረግ ፕሮዤ ላይ  ቤ ኤም ዜድ ቁጥጥሩን ማጠናከሩን እና በወቅቱ ተጨማሪ ክፍያ ማቆሙን አመልክቷል።
ይሁንና፣ በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታግ የተወከለው የተቃዋሚው ነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ፣ በምህጻሩ ኤፍ ዴ ፔ የልማት ፖሊሲ ቃል አቀባይ ክርስቶፍ ሆፍማን ይህ የጀርመን መንግሥት ርምጃ በቂ አይደለም  በማለት፣ ጀርመን በዛምቢያ አኳያ የምትከተለውን ፖሊሲ መልሳ  እንድታጤነው ሀሳብ አቅርበዋል። 
የጀርመን መንግሥት ከአውሮጳዊ የሚጠበቀውን ትብብር ማሳየት አለበት ብዬ አስባለሁ። እስከዛሬ ድረስ እንዳደረገውም  በልማት ትብብሩ መርሀ ግብር ላይ ለፀረ ሙስናው ትግል ጠንካራ ትኩረት በመስጠት ተጨባጭ ውጤት ለማየት እንደሚፈልግ  በግልጽ ማሳወቅ ይኖርበታል። በአፍሪቃ ለልማት በርዳታ ከሚሰጠው ገንዘብ ሰዎች ለራስ ጥቅም የሚሰርቁበት ብዙ ዘዴዎች አሉ። ይህ ዓይነቱ  አሰራር ማብቃት አለበት።

Karte Sambia englisch
GMF Logo BMZ deutsch

አርያም ተክሌ/ዳንየል ፔልስ

ልደት አበበ