1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የጀማሪ ድርጅቶች ፈተና በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2011

በኢትዮጵያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ የቴክኖሎጂ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ኩባንያውን ለመዝጋት ያስገደዱትን ምክንያቶች ዘርዝሮ ከሰሞኑ በድረ ገጽ ያወጣው ጽሁፍ መነጋገሪያ ሆኗል። በጽሁፉ በተነሱ ነጥቦች ላይ ከድርጅት ባለቤቶች እስከ መንግስት ባለስልጣናት ድረስ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተውበታል።

https://p.dw.com/p/39Egg
Symbolbild Start-Up
ምስል Colourbox

የጀማሪ ድርጅቶች ፈተና በኢትዮጵያ

አምስት ሳንቲም የዛሬ 13 ዓመት ግድም ተወለደ። አምስት ሳንቲም ወጣቱ ናሆም ታምራት እና ጓደኛው ለመሰረቱት የቴክኖሎጂ ድርጅት ዳቦ የቆረሱለት ስያሜ ነው። በኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአልግሎት ዘርፍ ስራውን አሃዱ ያለው ድርጅቱ የአስመጪነት ሚናም ደርቦ ነበር። ነገሮች በታሰቡት አቅጣጫ አልሄዱ ሲሉ ወደ ተነሳበት አገልግሎት መስጠት ዘርፍ የተመለሰው አምስት ሳንቲም ሲያጣጥር ቆይቶ ከመንፈቅ በፊት ስራ ማቆሙ እርግጥ ሆነ። መስራቾቹ እንዳሰቡት ግን ድርጅታቸውን በቶሎ ዘግተው ከውጣ ውረዱ እፎይ ማለት አልቻሉም። 

በኢትዮጵያ ድርጅት ከመክፈት ይልቅ መዝጋቱ ይበልጥ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገረው የአምስት ሳንቲም ጄነራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ናሆም ታምራት አሁን ያሉበትን ደረጃ ይገልጻል። “ሂደቱ እስካሁን አልተጠናቀቀም። መዝጋቱ እስካሁን ሰባት ወር እንግዲህ ፈጅቷል። ግን አሁን የመጨረሻዋ አንዲት እርምጃ ነው የቀረችው። እንደማስበው በአንድ ወር ውስጥ ይጠናቀቃል። ማለት መዝጋት ከመክፈት የበለጠ እጥፍ ድርብ ከባድ ነው። ስምንተኛ ወሩ ላይ ያልቃል ብለን እናስባለን።”  

ናሆም ድርጅቱን ከመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ አይነት ችግሮችን በየፈርጁ ተጋፍጧል። የገጠሙትን ችግሮች ለወዳጅ፣ ለጓደኞቹ ብቻ አካፍሎ ዝም አላለም። ይልቁንስ ለሌሎች ጀማሪ ድርጅት መስራቾች መማሪያ ይሆን ዘንድ በሚል በዝርዝር ጽፎ በድረ ገጽ ለንባብ አበቃው። ጽሁፉን እየተቀባበሉ ሲያጋሩ የሰነበቱት የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች እነርሱም በየፊናቸው ያስተዋሏቸውን ችግሮች እየዘረዘሩ ይወያዩ ያዙ።

Symbolbild Start-Up
ምስል VRD/Fotolia

መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የናሆም ጹሁፍ አጠቃላይ ይዘት “ኢትዮጵያ አዲስ ጀማሪ ለሆኑ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታዎች የሏትም” የሚል ነው። ናሆም አመቺ አይደሉም የተባሉትን ዋና ዋና ነገሮች ጽሁፉን እያጣቀሰ ይዘረዝራቸዋል። “ያው ከራሴ ልምድ የተረዳሁት ነገር ምንድነው? እንደዚህ አይነት የግል ዘርፍ ላይ ስትሳተፍ አንደኛውን አስበህ የምንትንቀሳቀሰው ያው የገቢ ጉዳይ ነው። እኔ በዚያ ወቅት ያየሁት ነገር እንግዲህ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። የራሴን ድክመቶች እና ጥፋቶች ጨምሮ ግን ከገቢ አንጻር ራሱ በተለይ ሙያ ላለው እና ለተማረ ሰው እንደው በሀቀኝነት ልስራ ካልክ አዋጪ እንዳልሆነ እና ሌላ አማራጭ ብትፈልግ የሚሻልበት ሁኔታ እንዳለ ነገር ነው የተረዳሁት። ገቢውን ደግሞ ሄጄ ስመረምረው አብዛኛው ገቢ የሚሄደው ስታየው ወደ መንግስት ካዝና ነው። እና በተለያየ ምክንያት ዞሮ ዞሮ መጨረሻ አንተ ጋር የሚቀረው ነገር ሲታይ በጣም ጫናው ወደዚያ ይገፋል። 

ያው ምክንያቶቹ እዚያ እንደተዘረዘሩት የመጀመሪያው የግብር አከፋፈል (taxation) ሚዛናዊነታቸው ከባድ ነው። እነርሱ እንኳ ይሁኑ እና እንስራ ቢባል ሌላ ሁለተኛ [ምክንያት] ከመንግስት የገቢዎች ባለስልጣን በኩል በሂሳብ ምርመራ (audit) እና በተለያየ መንገድ የሚደርሱ የግብር ውዝፎች፤ እንደው የግብር ምጣኔን እንኳን ችዬ እኖራለሁ ብትል በእንደዚህ አይነት የሚመጡ ተጨማሪ ጫናዎች ያው አዋጪ የማይሆን ያደርጉታል።  እና ከዚያ ደግሞ ስንቀጥል ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት (import)  ላይ ለተሰማራ ሰው የውጭ ምንዛሬ እጦት የቤት ኪራይ መወደድ እያልን እያልን ስንዘረዝር ያው እየተጨመሩ እየተጨመሩ ያው በመጨረሻ ወገብ ይሰብራሉ። እና ያንን ነው እንግዲህ ብዙ ዓመት የተረዳሁት” ሲል ያስረዳል። 

በተመረቀበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ዓመታት ያገለገለው ናሆም በኋላ ወደ ግሉ ዘርፍ ፊቱን ያዞረው በኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ሙያ የድርሻውን ለማበርከት ነበር። ለዚህም በሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ ሙያ ላይ ያሉ ወጣቶችን በተምሳሌትነት ወስዷል። ወጣቶቹ ሀሳብ እና ሙያቸውን ብቻ ይዘው ወደ ስራ በመግባት ለተጠቃሚዎች በሚሰጡት አገልግሎት በዓለም ዝነኛ የሆኑ ኩባንያዎችን መመስረት ችለዋል። ይህን ለመስራት ደግሞ ከፍ ያለ የመቋቋሚያ ገንዘብ አለመጠየቁ ዘርፉን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው እና የሙያው ሰዎችን የራሳቸውን ድርጅት እንዲመሰርቱ የሚያበረታታቸው እንደሆነ ናሆም ይናገራል። የናሆም እና የጓደኛው አምስት ሳንቲም ጄነራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም በዚህ እሳቤ የተመሰረተ ነበር። የወቅቱን ሁኔታ ናሆም መለስ ብሎ ያስታውሳል። 

“በወቅቱ ያው ገንዘብም አልነበረንም። ፍላጎቱ እና መጠነኛ የሆነ ችሎታ ነበረን እና ያንን ይዘን ስንነሳ በሙያዊ ፍቅር ነው። ብዙ ነገር እንዲህ ብንሰራ፣ እንዲህ ብንሰራ እንል ነበር። ያው ብዙ ነገር የለም ማለት ስለሚቻል  ከዚያ አንጻር ነበር የተነሳነው። በእርግጥ ያንን ስታደርግ ገንዘብም ሰርቼ ራሴን እለውጣለሁ የሚል ሁሌ ከጎን ይኖራል። አሁን ግን ወደ ኋላ ዞሬ ስመለከተው ለሙያው ያለኝ አስተያየት ያው ምንም አልተቀየረም። ሙያው እንዳለ ግን ቅድም በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች መሰረት የግል እንቅስቃሴ ያው ምቹ እንዳልሆነ ነው። 

Mauritius Internet cafe Facebook neben der alten Kirche in Gondar Äthiopien
ምስል Imago/ZUMA Press

በተለይ ደግሞ ይሄ የማምረት  ሳይሆን የአገልግሎት ዘርፍ ነው። ቁሳዊ ያልሆነ ነገር አገልግሎት ነው የምንሰጠው። አገልግሎቶቹ ለሚፈልግ ሰው የሚፈልገውን ሶፍትዌር መስራት ወይም እንደዚህ አይነት ነገሮች ናቸው። እና እንግዲህ እኛ ሀገር ባለው ፖሊሲ ያው ለዚህ ለአገልግሎት ዘርፍ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም ወይም አይሰጠውም። እና ለግብር አከፋፈል ሂሳብ ላይ ራሱ አይመችም። ምክንያቱም ለስራህ ወጪ የምታደርገው የራስህ አእምሮ፣ ጉልበት እና ኃይል ነው እና በሽያጭ ላይ የተሰማራው ግን ለዕቃ ያወጣው ፣የገዛበት እና የሸጠበትን ልዩነት ነው የሚያደርገው። ከግብር ደረጃ እንኳ አያያዙ ለየት ያደርገዋል። ያው በተዘረዘሩት ምክንያቶች ተስፋ አስቆራጭ ነገር ሆኖ ነው ያየሁት” ይላል ናሆም።   

ናሆም በጽሁፉ የዘረዘራቸው ችግሮች በዘርፉ ውስጥ ረጅም ዓመታት ያሳለፉ ባለሙያዎች ሲነጋገሩበት ሰንብተዋል። ጽሁፉን አንብበው አስተያየታቸውን ካጋሩት ውስጥ ማርቆስ ለማ አንዱ ነው። ማርቆስ መስራች በሆነበት እና አሁንም በስራ አስኪያጅነት እያገለገለ በሚገኘው አይስ አዲስ በተሰኘው ኩባንያው ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን ያግዛል። በስራ ላይ በቆየባቸው ሰባት ዓመታት ናሆም ያነሳቸውን ችግሮች አስተውሏል። በጽሁፉ ውስጥ የፖሊሲ ጉዳዮች በዋነኛነት መነሳቱን የሚጠቅሰው ማርቆስ  ጀማሪ ድርጅቶች የሚከፍቱ ሰዎች የሚገጥማቸውን ችግሮች ለማቅለል መንግስት ማድረግ የሚኖርበትን በመፍትሄነት መጠቆሙን አስታውሷል። እርሱ የሚጋራቸውን ነጥቦችንም  ጠቃቅሷቸዋል።

በማርቆስ የተደገፉት የናሆም ሀሳቦች እንዲሁ በቴክኖሎጂ ወዳድ ግለሰቦች ዘንድ ተወስነው አልቀሩም። በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ንቁ ተሳታፊ የሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን ጭምር ትኩረት ስበዋል።  “እውነቱን ያለማወላወል ያፍረጠረጠ” ሲሉ ጽሁፉን የጠሩት ባለስልጣናቱ ጉዳዩን በቸልታ አላለፉትም። በጽሁፉ የተጠቀሱትን መሰናክሎች ከዚህ ቀደም ከተደረገ የዳሰሳ ጥናት ጋር አገናዝበው ችግሮች መኖራቸውን አምነው ተቀብለዋል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ማሞ ምህረቱ ከጽሁፉ መታተም በኋላ በመንግስት በኩል መሻሻል የሚገባቸው 48 የአስተዳደር እና የህግ እርምጃዎችን መለየታቸውን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ጸሀፊውንም እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ብሎ የሚያምንባቸውን ለውጦች እንዲጠቁም ጠይቀውታል። የጻፈው ይህን ያህል መነጋገሪያ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ናሆም ለባለስልጣናቱም ሆነ ለጉዳዩ ትኩረት ለሰጡት ሁሉ ይረዳል ያለውን የመፍትሄ ሀሳብ የያዘ ተከታይ ጽሁፍ ለንባብ አብቅቷል። ኢትዮጵያን ለጀማሪ ድርጅቶች እንዴት ምቹ ማድረግ ይቻላል? በሚል መፍትሄዎችንም ዘርዝሯል።የናሆምን ተከታታይ ጹሁፍ ካነበቡት ባለስልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ ወደ ጽህፈት ቤታቸው ጋብዘው የስራ ተሞክሮውን ለሰራተኞቻቸው እንዲያካፍል አድርገውታል። ወጣቱ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ከመንግስት ባለስልጣናት ያገኘው ምላሽ ተስፋ እንዲሰንቅ ቢያደርገውም፣ ወደፊት ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ተስፋ ቢያሳድርም፣ ድርጅቱን እንደገና የመክፈት የቅርብ ጊዜ ህልም ግን የለውም። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቅሰው ውሳኔው የበርካታ ዓመታት ችግሮች ድምር ውጤት መሆኑን ነው። 

Äthipien Hawassa -  Fitsum Arega, Stabschef im Amt des äthiopischen Premierministers
ምስል DW/T. Waldyes

የማሻሻያዎችን አይቀሬነት የሚናገሩት DW ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ግን መጪው ጊዜ ለእንደ ናሆም አይነቶቹ እና ለጀማሪ ድርጅት ባለቤቶች የተመቻቸ ይሆናል ባይ ናቸው። ለዚህም መንግስታቸው ጥናት እያካሄደ መሆኑን እና በቅርብ ጊዜ ማሻሻያውን ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።  

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ