1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

Merga Yonas Bula
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 26 2010

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ዩኒቨሲቲዎች ተማሪዎችም ከፊሉ ወደ የቤታቸዉ እንደተመለሱ እና የቀሩት ደግሞ በፀጥታ ኃይሎች ችግር እንደሚደርስባቸዉ በመግለፅ የፀጥታ ኃይሎቹ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ቅጥር ግቢ ለቅቀዉ እንዲወጡ ሲጠይቁ ይሰማል። ሰሞኑንም የአዳማ ዩኒቨርሲቲ በተቃዉሞ ተሳትፈዋል ያላቸዉን 15 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ ማገዱ ተሰምቷል። 

https://p.dw.com/p/2qIjq
Karte Äthiopien englisch

The state of universities in Ethiopia - MP3-Stereo

በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ የፖለትካ ቀዉስ ከአንደኛ እስክ ከፍተና ደረጃ የሉትን ትምህርት ተቋሞችን የመማር እና ማስተማር ሒደቱን ማወኩን ሲዘገብ ቆይቷል። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም ትምህርት እንዳልተጀመረ፣ ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የዩኚቨርሲቲ ቅጥር ግብ ለቅቀዉ ወደ ቤተሰቦቻቸዉ እንደተመለሱ፣ በግቢዉ ዉስጥ የቀሩት በፀጥታ ኃይሎች ችግር እንደሚደርስባቸዉ እንዲሁም አንዳንዶችም ከትምህርት ገበታቸዉ እየታገዱ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

በሌላ በኩል የነበረዉ አለመረጋጋት አሁን እንደሌለ እና «ሰላማዊ» የሆነ የመማር ማስተማር ሒደቱም ቀደም ብሎ እንደ ነበረ መቀጠሉን የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ ማስታወቅያ ባወጣዉ መሰረት የተወሰኑ ተማሪዎች መመለሳቸዉን ለመረዳት ችለናል። ተማሪዎቹም ቢመለሱም ግን አሁንም በአስተዳደሩ በኩል ችግር እንደሚታይ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት እና ስማቸዉ እንዳይገለፅ የፈለጉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከአንድ ሳምንት በፊት የዩኒቨርሲቲ ቦርድ አመራሮችና ፕሬዝዳንቶች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዉይይት ማካሄዳቸዉን ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ይህን ጉዳይ በማንሳት በፌስቡክና በዋትስአፕ አወያይተን ነበር። አብዛኞቹ ተወያዮች ትምህርትን ከፖለቲካ አካል ተጽዕኖ ነጻ መሆን ያልቻለበት ምክንያት ለምን ይሆን ሲሉ ይጠይቃሉ። መንግሥት በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ የተርጋጋ ነው ቢልም ሁኔታው ግን የታመቀ እንጂ የተርጋጋ ነው ለማለት ይከብዳል የሚሉት አንድ አስተያየት ሰጭ፣ «ብዙ ተማሪዎች የተባረሩበት የታሰሩበት በፀጥታ መታወክ ምክንያትም ብዙዎቹ ፈርተዉ ግቢውን ለቀው ወደ ትውልድ ቀያቸው የተመለሱበት ሁኔታ እያለ እንዴት ወደ ነበረበት ሊመለስ ይችላል?» በማለትም ጠይቀዋል። 

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ