1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዕርዳታ አቅርቦት እና የጅግጅጋ ውሎ

ዓርብ፣ ነሐሴ 4 2010

በጅግጅጋ ዛሬ የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን ነዋሪዎቿ ለዶይቼ ቬለ ገለፁ። በከተማዋ ሱቆች ተከፍተዋል የሚሉ ዜናዎች ቢነገሩም ሱቆቹ ግን በመዘረፋቸው ሸቀጥ አልባ ናቸው ይላሉ ነዋሪዎቹ። የምግብ እና የውኃ ርዳታ በቀይ መስቀል በኩል እየገባላቸው መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/32zIr
Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

«ጅግጅጋ ተረጋግታለች፤ ቀይ መስቀልም እየረዳን ነው»

ከመሰንበቻው አከራረማቸው ጋር ሲያነፃፅሩትየጥይት ጩኸት  ዛሬ በከተማዋ አልተሰማም ይሏሉ ነዋሪዎቿ። ሰዎች ከሚያድሩበት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቀን ወደየቤታቸው ብቅ እያሉም የተዘረፈ ንብረታቸውን መቃኘች አንዳንዱም የሚገኝበትን ማፈላለግ ጀምረዋል። ሱቆች መከፈቱን ተከፍተዋል፤ ግን ምንም የላቸውም ይላሉ ያነጋገርናቸው የጅግጅጋ ነዋሪ።

«ያለው ሁኔታ እንግዲ ፀጥታው ጥሩ ነው አሁን እንደ ልብ እንንቀሳቀሳለን እንወጣለን እንገባለን። ሱቆች ቢከፈቱም ምን ዕቃ አላቸው ነው ጥያቄው። ሱቆች ተከፍተዋል ብለው ሚዲያ ላይ ይናገራሉ ግን ውሸት ነው። ሱቅ የተከፈተ ነገር የለውም ተከፍቶ ራሱ እንዳለ ምንም አይነት ዕቃ የለውም። ዕቃው እኮ ጠቅላላ ወድሟል እኮ።»

በእሳቸው ግምትም ቤተ ክርስቲያን ግቢ የተጠለለው 52 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ነው፤ ለእነሱም በቀይ መስቀል አማካኝነት ርዳታ እየቀረበ ነው ይላሉ።

«በቂ ውኃ እና ምግብ እየመጣ ነው ከድሬ ደዋ ማለት ነው፤ ያው ቀይ መስቀል ነው ዕርዳታ እያደረገ ያለው። ያው እዚህ ካለው ሕዝብ ጋር ማለት አሁን ሚካኤል ውስጥ የተጠለለው ቢያንስ ወደ 52 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ነው ያለው እና ያው በቂ አይደለም። እያለ እያለ እንግዲህ ይመጣል ብለው ተስፋ እየሰጡን ነው ያሉት።»

የሕዝቡን የተዘረፉ ንብረቶች በተመለከተ አንዳንዱ እየተመለሰ መሆኑን ሌሎቹን ደግሞ ራቅ አድርገው ስለወሰዱት እስካሁን ባለንብረቶቹ ሊያገኙ እንዳልቻሉም አክለው ገልጸዋል። ዋናው ነገር ዛሬ የጦር መሣሪያ ድምፅ እንኳን እንዳልሰሙ በመጠቆም ከሰሞኑ ግርግር እፎይታ መኖሩን አመልክተዋል። በተቃራኒው ከጅግጅጋ ከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖቻቸው ዛሬም የመከላከያ ሠራዊት እንዲደርስላቸው እንደሚሹ እና ሠራዊቱም ወደዚያው እያመራ መሆኑን መስማታቸውንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሊ በሐረር አካባቢዉ የሚገኙ የማሕበሩ ፅሕፈት ቤቶች ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ የአቅማቸውን ለሕዝቡ እያቀረቡ ነው ይላሉ።

Äthiopien, Rotes Kreuz
ምስል DW/G. Tedla

«ከአንድ ከሦስት ቀን ወዲህ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበርም እዚያው ጅግጅጋ የተፈናቀሉ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ ወገኖቻችን አሉ እና ለእነሱ አቅሙ የሚችለውን ያህል ከሐረር ካለው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የታሸጉ ውኃዎችን፤ እንደዚሁም ወደ 200 የሚሆኑ ካርቶን ብስኩቶችን እና እንደዚሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን፤ የመኝታ ቁሳቁሶች፤ ማብሰያዎች እንደዚሁም ደግሞ ለመጀመሪያ ህክምና ርዳታ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ሰጥቷል፤ እንዲሁም የተወሰኑ ኩንታል ሩዞችንም ሲሰጡ ነው የዋሉት።»

ቀይ መስቀል በአካባቢው ያለውን የውኃ ዕጥረት በማሰብም ተጨማሪ 19 ሺህ ሊትር የሚይዝ ቦቴ ልኮ ከትናንት ጀምሮ ከሐረማያ ውኃ እንዲያመላልስ ማድረጉንም ገልጸዋል። ከጂግጂጋ አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለው ገርባሳ ማሰልጠኛ ውስጥም ለተጠለሉ ወገኖች ወደ 35 ኩንታን ሩዝ እና የውኃ ማጠራቀሚያ ሮቶዎችን ማሕበሩ ማድረሱንም ዘርዝረዋል።   አሁን ከበፊቱ አንፃራዊ ሰላም እንዳለ ያመለከቱት ዶክተር ሰሎምን ከድሬደዋና ከሌሎች አካባቢዎችም ርዳታ የማስተባበሩ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ለዚህም 15 የሚሆኑ የቀይ መስቀል የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች መሠማራታቸውንም አስረድተዋል። በሶማሌ ክልል ከጅግጅጋ ውጭም የተፈናቀሉት ወገኖች እንደመኖራቸው የእርዳታ አቅም ማስተማበር እንደሚበት ግን ሳይገልፁ አላለፉም። ዶክተር ሰሎም አክለውም ባለፈው ሳምንት ነፍሰጡር ለመርዳት የጤና ባለሙያ የጫነ አንድ የቀይ መስቀል አምቡላንስ በባቢሌ አካባቢ በታጣቂዎች መዘረፉን፤ የጤና ባለሙያው ተገድሎ አሽከርካሪዉም መጎዳቱን አመልክተዋል።   

10 አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ በስፍራው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ ማዋቀሯን ይፋ አድርጋለች። ቀሲስ ሙሉቀን ዋለ የኮሚቴው አባል እንደገለፁልን ሕዝቡን የሚያፅናና ኮሚቴ ነገ ወደ ስፍራው ይላካል።

«ቤተክርስቲያኗ ኮሚቴ አዋቅራለች የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት መልሶ የሚያሠራ፤ እንገናም ለተጎዱት ወገኖቻችን የህክምና፤ የምግብ የአልባሳት የሚያሰባስብ ሁለት ኮሚቴ ተዋቅሯል፤ አንድ ልዑክ ደግሞ ነገ ወደ ጂግጅጋ ይላካል፤ ባንክ አካውንት ተከፍቷል።»

ሸዋዬ ለገሠ 

አርያም ተክሌ