1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም መሪዎች በሰላም ማከበር ተልዕኮዎች ማሻሻያ ላይ ይመክራሉ

ሰኞ፣ መስከረም 8 2010

የዓለም መሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማሻሻያዎች ላይ ይመክራሉ።  በምክክሩ ጠቅላይ ሚኒሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋቂ ማህማት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይታደማሉ።

https://p.dw.com/p/2kE7E
UN Mission UNMIL
ምስል picture-alliance/dpa/N. Bothma

የሰላማ ማስከበር ተልዕኮ ማሻሻያዎች

የዓለም መሪዎች በመጪው ረቡዕ ወታደሮች፣የፖሊስ ሰራዊት አባላት እና የተባበሩት መንግሥታት የበጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ ከ100,000 በላይ ሰራተኞች ያሉት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያሻዋል ባሉት ማሻሻያ ላይ ይመክራሉ። ካለፈው ሐምሌ እስከ መጪው ሰኔ ላለው አንድ አመት ብቻ 6.8 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተመደበለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማሻሻያዎች ያሻዋል ከተባለ ከራርሟል። አቶ ብሩክ መኮንን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ልዑክ ቃል አቀባይ ናቸው። 
"ባለፉት ሁለት አመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል የተጠኑ ጥናቶች አሉ። የእነዚህ ጥናቶች አፈጻጸምን በሚመለከት ነው የዚህ ስብሰባ ዋና ትኩረት። እነዚህ አፈጻጸሞች ምን ደረጃ ላይ ናቸው? በአፈጻጸም ሒደቱስ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው የሚለው ላይ ነው ይኸ ስብሰባ በዋናነት የሚያጠነጥነው።"
ዓለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚደረጉበት ማሻሻያዎች በዋናነት ከሁለት አመት በፊት ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ገለልተኛ የምክክር መድረክ ባቀረባቸው ጥቆማዎች ላይ መሰረት ያደረገ ነው። በጸጥታ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪዋ ሪያና ፓኔራስ የባለሙያዎቹ ስብስብ በዓለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሊደረጉ ይገባል ያላቸውን በርካታ ጥቆማዎች ማቅረቡን ያስታውሳሉ። 

UN Symbolbild Flagge
ምስል Imago/Y. Kourtoglou

"ከትልልቆቹ ጥቆማዎች አንዱ ትኩረቱ ከሰላም ማስከበር ወደ ሰላም የማስፈን ተልዕኮ መሻገር አለበት የሚለው ነው። የሰላም ማስፈን ተልዕኮ ስራ ግጭት የመከላከል እንቅስቃሴዎች ፣ የሰላም ግንባታ፣ የድኅረ ግጭት መልሶ ማቋቋም እና የልማት ሥራን ያካትታል። በባለሙያዎቹ ዘገባ ስለ ፖሊስ ተሳትፎም በርካታ ጥቆማዎች ተካተዋል። ሌላው ግጭት ሲፈጠር ሰላም አስከባሪ ጣልቃ ይገባል።  ዘላቂ ሰላም እንዲኖርም ይጠበቃል። አንዱ ፈታኝ ነገር ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ምንም ሥራ ሳይሰራ ወታደሮቹ እንዲወጡ መደረጉ ነው።በቀውስ በተመቱ አገሮች በመንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ የሕግ የበላይነትን እና ሌሎች አገልግሎቶችን  መልሶ ማስፈን ሌላው ችላ የተባለ ነገር ነው።  ግጭት የነበረባቸውን አካባቢዎች ስንመለከት መላ የጸጥታ ጥበቃ እና የፍትኅ ሥርዓቶቹ ፈርሰዋል።"

ሪያና ፓኔራስ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግጭት ባቀወሳቸው አካባቢዎች በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ብቻ ተወስኖ ቆይቷል ሲሉ ይተቻሉ። ከዚህ ቀደም በሶማሊያ እንደሆነው ሁሉ ዘላቂ ስራ ባልተሰራባቸው አካባቢዎች ሰላም አስከባሪ ሲወጣ ግጭት የሚከላከል ሥርዓት ባለመኖሩ ቀውስ ተመልሶ ሲያገረሽ መታየቱን ባለሙያዋ ተናግረዋል። 

ሪያና ፓኔራስ የጠቀሱት እና በገለልተኛ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተጠናቀረው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግምገማ በአራት ዘርፎች ማሻሻያዎች ሊደረጉ ይገባል ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። በ94 ገፆች የተቀነበበው ግምገማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የፖለቲካ ሒደትን የመደገፍ ሰፊ ሚና አንድ አካል ሊሆን ይገባል የሚል ጥቆማ ሰጥቷል። የሰላም ማስከበር ተልዕኮው ለነባራዊ ሁኔታ ምላሽ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል ያለው ግምገማ ጸጥታ እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የተባበሩት መንግሥታት በአጋርነት እንዲሰራ ጥቆማ አቅርቧል። የተባበሩት መንግሥታት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎቹ መስክ ተኮር እና ሰዎችን ማዕከል ሊያደርግ ይገባል ሲልም አትቷል። አቶ ብሩክ መኮንን የተሰሩት ጥናቶች የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮዎች ከሰላም ማስከበር የዘለለ ሚና እንዲኖራቸው የታቀዱ ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።

"በዋናነት የሰላም ማስከበር ሒደት ውጤታማ እንዲሆን፤የተሰጠውን ተልዕኮ በውጤታማነት ማስፈጸም እንዲችል እና  ከሰላም ማስጠበቅ በዘለለ የዘላቂ ሰላምንና ልማትን የሚያመጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ ያተኮሩ ናቸው።"

የግጭት መንስዔዎች እና ጠባዮቻቸው መለወጣቸውን የሚናገሩት በጸጥታ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪዋ ሪያና ፓኔራስ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንደከዚህ ቀደሙ ገለልተኛ መሆን ስለመቻሉ ጥርጣሬ አላቸው። 

USA United Nations UN Fahne
ምስል Getty Images/S. Platt

"ሽብር እና ድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ወንጀል  በሰላም ማስፈን ተልዕኮ ላይ መሰረታዊ ለውጥ አምጥተዋል። የባለሙያዎቹ ጥቆማ እነዚህን ለመቀልበስ ሰላም ማስከበር በቀጥታ ጥቅም ላይ ሊውል አይገባም የሚል ኃሳብ አቅርቧል። ነገር ግን ተፅዕኖ እስካለው ድረስ አንድ ተልዕኮ ቸል ሊለው ይገባል ብዬ አላምንም። ለምሳሌ ሶማሊያን እንውሰድ። በዚያ የአፍሪቃ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ አለ። የተደራጀ ወንጀል ተቃዋሚዎችን እና አል-ሸባብን ወደ ወደ ፊት እየገፋቸው ነው። ስኳር እና ከሰል ከመሳሰሉ ንግዶች ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛሉ። መንግሥት ይኸን ለመፍታት ደካማ በመሆኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መፍትሔ ካልፈለገለት ማን ሊፈታው ነው? ሌላስ ምን ምርጫ አለ?  ከዚህ በተጨማሪ ግጭት ከተከሰተ በኋላ ከመታገል ይልቅ ከመከሰቱ በፊት እንዴት መከላከል ይቻላል የሚለው ኹነኛ መፍትሔ ይሻል።"

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማሻሻል ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ሪያና ፓኔራስ ተናግረዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድ ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን የበጀት ቅነሳ እንዲደረግ መሻታቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮው ሌላ ፈተና ነው።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ባለፈው ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር ስልጣን ላይ በቆየባቸው አምስት ወራት ከዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወጪዎች ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ማዳናቸውን ተናግረዋል። አምባሳደሯ የወጪ ቅነሳውን እንደ ታላቅ ስኬት ቢቆጥሩትም ተንታኞች ግን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መፃኢ ፈተና ጠቋሚ ምልክት አድርገውታል። 
እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ