1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

ካቅማችን በላይ ግብር ተጭኖብናል የሚሉት ነጋዴዎች ለቅሬታችን መፍትሔ አላገኘንም እያሉ ነው

ሰኞ፣ ነሐሴ 1 2009

ካቅማችን በላይ ግብር ተጥሎብናል ያሉ የወልዲያ ከተማ ነጋዴዎች በዛሬው ዕለት ቅራኔያቸውን ለማሰማት ሱቆቻቸውን ዘግተው ውለዋል።

https://p.dw.com/p/2hq8C
Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የወልዲያ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ዘግተው ዋሉ

55 ሺህ ብር አመታዊ ግብር የተጣለባቸው የወልዲያው ነጋዴ ዛሬ ሱቃቸውን አልከፈቱም። ጨርቃ ጨርቅ የሚነግዱት ከድር ኡስማን (ስማቸው የተቀየረ) ለከተማው የግብር መሥሪያ ቤት አቤት ቢሉም መፍትሔ አላገኙም። "አሁን እኛ የቤት ኪራይ ከፍለን በሳምንት አንድ ሸጠን የማንውል ነን።" የሚሉት አቶ ከድር የተጣለባቸው ግብር "የተሳሳተ ነው" ብለው አቤቱታ ሲያቀርቡ "ትከፍላላችሁ ትከፍላላችሁ ነው" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። ሱቃቸውን በመዝጋታቸው "ካልተከፈተ ችግር ትፈጥራላችሁ እያሉ ሲያስፈራሩን ውለዋል" የሚሉት ነጋዴ አቤት ብለው ምላሽ በማጣታቸው ቅሬታ አስገብተው መፍትሔ ባለማግኘታቸው ወደ ተቃውሞ ፊታቸውን አዙረዋል።

የነጋዴዎች ተቃውሞውን ካስተባበሩት መካከል በሕንጻ መሳሪያዎች ንግድ የተሰማሩ ግለሰብ ይገኙበታል። "ጣሪያ የነካ የግብር ክፍያ እንድንከፍል ነው የተገደድንው።" የሚሉት ነጋዴ በሁለት ሱቆቻቸው 13,000 ብር የቀን ገቢ ያገኛሉ ተብሎ ተገምቶባቸዋል-በመንግሥት ባለሥልጣናቱ። እርሳቸው ግን የመንግሥት ሹማምንቱ በገመቱት ስሌት አይስማሙም። እርሳቸውም እንደ አቶ ከድር ሁሉ ለቅሬታ ሰሚ የመንግሥት አካል ያቀረቡት አቤቱታ አመርቂ ምላሽ አላስገኘላቸውም።  እናም ከመሰሎቻቸው ጋር ተማክረው ሱቃቸውን ዘጉ። የመንግሥትን ግብር ተቃውመው ሱቆቻቸውን የዘጉት ግን የጨርቃ ጨርቅ እና የሕንፃ እቃዎች ነጋዴዎቹ ብቻ አይደሉም።

በወልዲያ ከተማ ጎንደር በር፤አዳጎ እና ፒያሳ በተባሉ አካባቢዎች የንግድ ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን የሚናገሩት የአይን እማኝ የጸጥታ ኃይሎች በግዳጅ ለማስከፈት መሞከራቸውን አስተውለዋል። "ብዙ ሱቆች ተዘጋግተው ውለዋል። ፖሊሶች ለማስከፈት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ሕብረተሰቡ አልከፍትም ብሎ ዘግቶ ነው የዋለው።" ሲሉ ያክላሉ የወልድያው ነዋሪ።

በወልዲያ ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን ያልከፈቱ ግለሰቦች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደርሷቸዋል። ያቀረቡት ቅሬታ ምላሽ ያጣባቸው ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን በመዝጋት ተቃውሟቸዋን ለማሰማት መገደዳቸውን የሕንጻ እቃዎች ነጋዴው ይናገራሉ። "ቅሬታችንን ለመግለፅ ያክል ነው። ቅሬታ ሰሚ አካልም የለም። ስለዚህ ያለን አማራጭ ተቃውሟችንን በዚህ እንግለጽ በሚል ነው።ወልዲያ ሙሉ በሙሉ ሱቆች ተዘግተዋል። ከመቶ አምስት የሚሆኑ ያልተዘጉ አሉ። የተዘጉትን ደግሞ የማስጠንቀቂያ ወረቀት እየለጠፉባቸው ነው።"

በጨርቃ ጨርቅ ንግድ የተሰማሩት አቶ ከድር ኡስማን ሱቅ በመዝጋት አድማ በመምታታቸው የመንግስትን ቀልብ ለመግዛት አልመዋል። ተገቢውን ምላሽ ለማግኘታቸው ግን ጥርጣሬ አላቸው። "በአዲስ አበባ በኩል ተዘግቶ ትንሽ ቅራኔ ተሰምቶላቸዋል የሚል ሲሰማ በዚህ በመነሳሳት ነው እንጂ እርግጥ ሱቅ በመዘጋቱ መፍትሔ እንደማይገኝ ሁሉም ሰው አምኖበታል። ግን መንግሥትን ሕዝቡ የጠላ መሆኑን ይወቀው በሚል ብቻ ነው።"

የኢትዮጵያ መንግሥት የጣለው የገቢ ግምት ግብር በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተቃውሞ መቀስቀሱ አይዘነጋም።   

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ