1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሪያ ልሳነ ምድር ዉዝግብ

ዓርብ፣ ሰኔ 30 2009

የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈዉ ማክሰኞ-ያስሞከሩትን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል «ለአሜሪካኖች የነፃነት ስጦታ» ብለዉታል።ማክሰኞች ለአሜሪካኖች የነፃነት ዕለት ነበር።ሚሳዬሉ፤ አዋቂዎች እንደሚሉት፤አሜሪካዋ ሰሜን-ምዕራብ ግዛት አላስካ ላይ የሚገኝ ኢላማዉን ያደባየዋል

https://p.dw.com/p/2gAR5
Südkorea gemeinsame Manöver mit USA Rakete Hyunmoo Missile II
ምስል Reuters/8th United States Army

NM - MP3-Stereo

ሠሜን ኮሪያ ባለፈዉ ማክሰኞ የረጅም ርቀት ሚሳዬል መሞኮርዋ ወትሮም ያልቀዘቀዘዉን የአካባቢዉን ዉጥረት ይበልጥ አንሮታል።ሙከራዉን የተለያዩ መንግሥታት ሲቃወሙት ዩናይትድ ስቴትስ፤ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ለመዉሰድ እየዛቱ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ከሰሜን ኮሪያ አልፈዉ ቻይናን ማዉገዛቸዉ የዉዝግቡን አድማስ አስፍቶታል።የአሜሪካ ባለሥልጣናት የኮሪያ ልሳነ ምድርን ዉጥረት ከሚያንሩ ቃላትና ድርጊት እንዲታቀቡ ቻይና መክራለች። 

የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈዉ ማክሰኞ-ያስሞከሩትን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል «ለአሜሪካኖች የነፃነት ስጦታ» ብለዉታል።ማክሰኞች ለአሜሪካኖች የነፃነት ዕለት ነበር።ሚሳዬሉ፤ አዋቂዎች እንደሚሉት፤አሜሪካዋ ሰሜን-ምዕራብ ግዛት አላስካ ላይ የሚገኝ ኢላማዉን ያደባየዋል።
ያቺ ትንሽ፤የአንድ ሐገር ግማሽ፤ በሐብታም፤ጠላቶችዋ የተከበበች ደሐ ሐገር እንዳአጀማመሯ ከቀጠለች፤ በጥቂት ዓመታት ዉስጥ መላዉን ዩናይትድ ስቴትስን መምታት የሚችል ሚሳዬል ማምረት አይገዳትም መባሉ ለአሜሪካኖችን  አሳሳቢ ነዉ።ሚሳዬሎ የኑክሌር አረር መሸከም ይችላል-መባሉ ደግሞ አስደንጋጭ።
አሳሳቢ-አስደንጋጩን ሥጋት ለመቀነስ የዩትድ ስቴትስ ዲፕሎማሲን፤ከወታደራዊ ጡንቻ፤ ማዕቀብን ከሳይበር ሻጥር ጋር የቀየጠ ሥልት የምትከተል መስላለች።ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን በዲፕሎማሲዉ መስክ የዶቸ ቬለዉ ክርስቶፍ ሐሰልባኽ እንደሚለዉ፤ የሳቸዉን ሥራ ሌሎች እንዲሰሩላቸዉ ይፈልጋሉ።በተለይ ቻይኖች።«ቻይና በሰሜን ኮሪያ ላይ ጠንካራ ጫና ታሳድራለች ብለዉ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ለረጅም ጊዜ ጠብቀዉ ነበር---ይገርማል» ፃፉ (ትዊቱ-ይባል ይሆን) በቀደም አስገራሚዉ መሪ።
ትራምፕ የጃፓን ወይም የደቡብ ኮሪያ መሪ የሆኑ ይመስል በሁለቱ ሐገራት ስም ቤጂንጎችን ሲተቹ፤ የምድር ያየር እና የባሕር ጦራቸዉ ከደቡብ ኮሪያ አቻዉ ጋር ሆኖ የኮሪያ ልሳነ-ምድርን በዉጊያ ልምምድ «እያተራማሰዉ» ነዉ።የትራምፕ አስተዳደር ደቡብ ኮሪያ ላይ ፀረ-ሚሳዬል-ሚሳዬል ለመትከልም አቅዷል።
ቻይናና ሩሲያ የፒዮንግዮንግን የሚሳዬል ሙከራ የሚቃወሙትን ያክል የዋሽግተንና የተከታዮችዋን የጦር ዝግጅትና የጦር መሳሪያ ግንባታንም ይቃወሙታል።የትራምፕ ሹማምንት ተቃዉሞዉን አሜሪካ በሠላማዊ ዉቅያኖስ ላይ የምታደርገዉን ወታደራዊ ዘመቻ ለመቀነስ ያለመ ባዮች ናቸዉ።በ1990ዎቹ ሥለሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ-ግብር በተደረገዉ ድርድር የአሜሪካ ተደራዳሪ የነበሩት ሮበርት ጋሉቺ መጠቋቋም-መወቃቀሱ የሚፈይደዉ የለም ባይ ናቸዉ።ድርድር እንጂ።
                          
«ሁኔታዉ የማይለወጥ አይደለም።የሚመለከታቸዉ ወገኖች ለመነጋገር ከፈለጉ፤ ሌላ ቢቀር ሥለ ንግግር ቢነጋገሩ እንኳን፤ ሥለ ዋናዉ ድርድር መደራደር ራሱ በተገቢዉ አቅጣጫ አንድ እርምጃ ነዉ።»
ድርድር ለመጀመር የፈለገ ያለ አይመስልም።ዶናልድ ትራምፕ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ መንግስታትን ድጋፍ ለማግኝት  ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።ይሁንና ከንግድ እስከ ተፈጥሮ ጥበቃ፤ ከስደተኛ እስከ ምጣኔ ሐብት መርሐቸዉ ሐገራቸዉን ከነባር ተከታዮችዋ እየነጠሉ እዉነተኛ ድጋፍ ማግኘታቸዉ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነዉ።
በዚያ ላይ የትራምፕ እቅድ ከሰሜን ኮሪያ በተጨማሪ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ይሳራሉ የሚባሉ የቻይና ኩባንዮችን በማዕቀብ መቅጣትን ያካተተ በመሆኑ የሚፈልጉትን ያሕል ደጋፊ አያገኙም።የደቡብ ኮሪያና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄኔራሎች የሰሜን ኮሪያን የጦር መሳሪያ ማምረቻና ማከማቻዎች ድንገት የሚመቱበትን ሥልት እያረቀቁ-መቅደዳቸዉ አልቀረም።
«ሳይቀድሙ-መቅደም» የሚባለዉን ይሕን ሥልት «እኔም ራሴ ብዙ ጊዜ አስቤዉ ነበር» አሉ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ዊሊያም ፔሪ «አይሆንም።» በሰወስት ምክንያት፤ አንደኛ አስር ሚሊዮን ሕዝብ የሚርመሰመስባት የደቡብ ኮሪያ ርዕሠ-ከተማ ሶል ለየትኛዉ የሰሜን ኮሪያ ከባድ መሳሪያ ደረቱን የሰጠ ነዉ።ሁለተኛ የኑክሌር አፀፋ ሊከተል ይችላል።ሰወስተኛ፤-ሳይቀድሙ መቀደም ቢመጣስ።
ዩናይትድ ስቴትስ የሰሜን ኮሪያን የሚሳዬልና የኑክሌር መሳሪያ የኮምፒዉተር መርሐ-ግብር በሳይበር ዝቃት ለማዛባት ብዙ ጊዜ ሞክራ ነበር።ኢራን ላይ የተደረገዉ ሻጥር ተሳክቶ ነበር።ፒዮንግዮንግ ግን ቴሕራንን ሆና አልተገኘችም።ሮበርት ጋሉጪ እንደሚሉት ግን ቢደራደሯቸዉ ሰሜን ኮሪያዎች  ይሕን ያሕል አስቸጋሪ አይደሉም 
                                
«የሰሜን ኮሪያን መግለጫ ሰምቶ የሚያምን ሰዉ፤ እነሱ የኑክሌር ባለቤት ናቸዉ፤ ኒኩሌራቸዉን መስጠት አይፈልጉም የሚል አስተያየት ሲሰጥ ያደናግረኛል።የሰሜን ኮሪያዎች ብዙ ጊዜ «ጭራሽ አይሆንም» ይላሉ።የዚያኑ ያክል የተወሰኑ ነገሮችን የሚደርጉ ብልሕ መሆናቸዉንም አይተናል።»
ላሁኑ ድርድርን የተቀበለዉ የለም።በተባበሩት መንግሥታት የዩናይትድ ስቴትሷ አምባሳደር ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንደነገሩትማ «አስፈላጊ ከሆነ ሐገራቸዉ የኃይል እርምጃ ለመዉሰድ  ዝግጁ ነች።የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጌንግ ሹዋንግ «ካፍንም፤ከጅም ሰብብ» ያሉት ለዚሕ  ነዉ።

US Botschafterin Nikki Haley
ምስል Reuters/M. Segar
Nordkorea Raketentest Hwasong-14 public viewing
ምስል Reuters/KCNA

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ