1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቶቪትሰው ጉባኤ ውጤት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2011

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በፖላንዷ ካቶቪትሰ ከተማ የተካሄደው 24ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ያለውጤት ሊጠናቀቅ እንደሆነ ሲነገር የቆየውን ስጋት አልፎ ስምምነት ላይ መድረሱ ከተሰማ ቀናት ተቆጠሩ። በማደግ ላይ ያሉት ሃገራት ውሉ ለእነሱ ድጎማ ይዋጣል የተባለው ገንዘብ ላይ ያመጣው ለውጥ የለም በሚል ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።

https://p.dw.com/p/3AKwD
UN-Klimakonferenz 2018 in Katowice, Polen | Symbolbild
ምስል Imago/Zuma Press

«ውሉ የፓሪሱን ስምምነት መተግበሪያ ነው»

«አሁን የCOP ተሳታፊዎች ሲሲሲ ሕዝባር ሲፒ ሕዝባር 2018 ሕዝባር ኤል 27 የተሰኘውን ረቂቅ ውሳኔ እንድታጸድቁ እጠይቃለሁ።»

ከኅዳር 24 እስከ ታኅሣስ 6 2011ዓ,ም ድረስ በፖላንዷ ካቶቪትሰ ከተማ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባኤ ከተጠበቀው ስምምነት ላይ መድረሱ ከተበሰረበት ንግግር የተወሰደ ነው። ውሳኔውን ለተሰብሳቢዎች ይፋ ያደረጉት የፖላንድ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እና የጉባኤው ሊቀመንበር ሚካል ኩርቴካ ነበሩ። ይህ ረቂቅ ውሳኔ 196 ሃገራትን በወከሉት የጉባኤው ተሳታፊዎች እንዲጸድቅ ሲቀርብ በአንድ ጉዳይ ላይ ልዩነቷን ያሰማችው ሕንድ ብቻ ናት። ከዚህ በኋላም ጸደቀ።

ለሁለት ሳምንታት በደቡባዊቱ የፖላንድ ግዛት ካቶቪትሰ ከተማ ተሰባስበው ሲደራደሩ የሰነበቱት 196 ሃገራት ወኪሎች፤ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች፤ የዘርፉ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ላይሳካ ይችላል የተባለውን ስምምነት የማታ ማታ ማሳካት መቻላቸው በአንድ በኩል እፎይታ ሳይፈጥርላቸው የቀረ አይመስልም። የስምምነታቸው  ዋና ጉዳይ የዛሬ ሦስት ዓመት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን ለመቀነስ የደረሰቡበትን ስምምነት ተግባራዊነት መከታተል ያስችላል የተባለውን ማዕቀፍ መቀበል ነው። ዓርብ ዕለት ይጠቃለላል ተብሎ የተገመተው ጉባኤ ወደ ቅዳሜ መሸጋገር ግድ ሆኖበት ነው እኩለ ሌሊት ገደማ ተሰብሳቢዎቹ ከስምምነት የደረሱት። ስምምነቱ የየሃገራቱን ፍላጎት የሚያሟላ አይነት ሳይሆን ሰብዓዊነትን ያስቀደመ መሆኑን ያመለከቱት ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመሩት የአስተናጋጇ ሀገር የፖላንድ ምክትል የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር በርካታ ሃገራት ተሰባስበው በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም ለመያዝ ቀላል እንዳልነበረ ተናግረዋል።

Just Transition Bulgaria  Bulgariens Kohleabbau vor dem Aus
ምስል DW/J. Hilton

«200 የሆኑ ሃገራት በተሰበሰቡበት በዚህ አዳራሽ ውሱን እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ያሉበት ውል ላይ ለመስማማት ቀላል አይደለም። ይህ ባለበት ወደፊት የምትወስደን እያንዳንዷ ርምጃ ታላቅ ስኬት ናት፣ እናም በዚህ ማዕቀፍ በጋራ አንድ ሺህ ትናንሽ ርምጃዎችን ወስዳችኋል። ልትኮሩ ትችላላችሁ።»

በዓለም አቀፍ ደረጃ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የተሰባሰቡበትን ቡድን የሚመሩት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ተነሳሽነት ላይ በአማካሪነት የሚያገለግሉት አቶ ገብሩ ጀምበር ፓሪስ በዋና ዋና ነጥቦች ላይ የተስማማው ጉባኤ ያንን እንዴት ማስፈጸም እና መተግበር ይቻላል የሚለውን በይደር ማስቀመጡን አስታውሰው፤  የካቶቪትሰው ጉባኤ በአጠቃላይ ያን ስምምነት ማስፈጸሚያ ደንብ፤ ማለትም መመሪያ በአንድ መንፈስ መግባባት መቻሉን ገልፀውልናል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በድርድር ተጠምደው የሰነበቱት የየሃገራቱ ተወካዮች በዚህ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ሳይሆን ረዘም ላሉ ጊዜያት ሲነጋገር እንደሰነበተም አስረድተዋል።

Polen COP24 Klimakonferenz in Kattowitz (Imago/ZUMA Press(B. Zawrzel)
ምስል Imago/ZUMA Press(B. Zawrzel

ብራዚል በካርቦን ንግድ ጉዳይ ልትስማማ አለመቻሏ የጉባኤውን የፍፃሜ ዕለት ማራዘሙ እንዳለ ሆኖ ሕንድም በበኩሏ ሃገራት የብክለት ቅነሳው ባደጉ እና ባላደጉ ሃገራት መካከል ተመሳሳይ መሆን የለበትም የሚል መከራከሪያ አቅርባ፤ ልዩነቷን በማስመዝገብ  ነው መስማማቷን የገለጸችው። 156 ገፅ እንዳለው የተነገረው የፓሪሱን ስምምነት መተግበሪያ መመሪያ ሰነድ ሃገራት የሚቀንሱትን የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን የሚለኩበት፤ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የሚደጎሙበት እንዲሁም የመቆጣጠሪያ ስልቶችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም በተመድ አስተባባሪነት ሃገራት የተስማሙበት ወደከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ የመቀነስ ርምጃን ያካተተው ዝርዝር ስምምነት በዚሁ የዘመን ቀመር 2020 ላይ በሥራ መተግበር እንደሚጀምር ነው የተነገረው። በዚህ ጥረትም የዓለም የሙቀት መጠን ከ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዳይበልጥ ለማድረግ ታቅዷል። እንደሲሸልስ እና መሰል በባሕር የተከበቡ ሃገራት ደግሞ የሙቀት መጠኑ ከ1,5 ዲግሪ መብለጥ የለበትም ያን ማድረግ ካልተቻለ ለከፋ አደጋ መጋለጣችን ይቀጥላል በሚል እያሳሰቡ ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ