1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦብነግ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ 

Merga Yonas Bula
ሰኞ፣ ነሐሴ 7 2010

የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱን ድርጅቱ ለዶይቼ ቬሌ ገልጿል። የልዑካን ቡድኑም ከሶማሌ ክልል ባለስልጣናት እና ከክልሉ ማህበረሰቡ ጋር እንደሚነጋገር ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/336WO
Mitglieder der ONLF/Ogaden National Liberation Front
ምስል Getty Images/A.Maasho

ONLF Delegation in Ethiopia - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ መቀመጫቸዉን ዉጭ አገር  ያደረጉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትጥቃቸዉን በማስቀመጥ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸዉ ይታወሳል። ይህን ጥሪ ተቀብለው ከመንግስት ጋር ስምምነት ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ካሳዩት መካከል የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) አንዱ ነዉ። ግንባሩ ባለፉት ሁለት ሳምንት በኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልል ለተፈጠረዉ የሰላም መድፍረስ ከመንግስት ጎን በመሆን መፍትሄ ለመፈለግ ትናንት አራት አባላቱን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል። የግንባሩ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ሃሳን አብዱላሂ በኢትዮጵያ የልዑካን ቡድኑን እንቅስቃሴ ምን እንደሚሆን ለዶቼቬለ ገልጸዋል።

በግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ ሁሴን ኑር የሚመራዉ ይህ የልዑካን ቡድን ከመንግስት ባለስልጣናትና ከማህበረሰቡ ጋር በክልሉ የፖለቲካ ቀዉስ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለግንባሩ ዘገባ እንደሚያቀርቡ አቶ ሃሳን ይናገራሉ። በዚህ ዘገባ ላይ ተመስርቶ ግንባሩና የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ድርድር እንደሚገቡ አቶ ሃሳን አክለዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ  የትጥቅ ትግል ስያካሂድ የነበረዉ ኦብነግ ከትናንት ጀምሮ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን አውጇል። ግንባሩ የተኩስ አቁሙ የተደረገው ፣ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ያነጣጠሩትን ወታደራዊ እና የፀጥታ ዘመቻዎቹን በሙሉ ለማቆም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አጠቃላይ ስምምነት እስኪደረስ መሆኑን ገልጿል።

በቅርቡ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ-ሶማሌ ክልል የተመለሱት አቶ ጋራድ ኡመር ዶን በክልሉ የሚደርሰው በደል እንዲቆም እየሰራሁ ነው ይላሉ። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱት የግንባሩን ልዑካን እስካሁን እንዳላገኙ የሚናገሩት ጋራድ ኡመር ኦብነግ የጠ/ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ኢትዮጵያ ልዑካን መላኩን በበጎ ይመለከቱታታል። ይሁን እንጅ በርሳቸው አስተያየት ግንባሩ ከመንግስት ጋር እደራደራለሁ ማለቱ «ለራሱ ጥቅም እንጅ ለህዝቡ አስቦ አይደለም» ይላሉ።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1984 የዛሬ 34 ዓመት የተመሰረተዉ ኦብነግ ኦጋዴንን ወይም የኢትዮ-ሶማሊ ክልልን ነጻ ለማዉጣት እንደሚታገል የግንባሩ መረጃ ያመለክታል።

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ