1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስረኞቹ መለቀቅ፤ አስተያየት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

ረቡዕ፣ ጥር 9 2010

ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 እስረኞች ዛሬ መለቀቃቸውን ይፋ ከኾነበት ቅጽበት አንስቶ ጉዳዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ኾኗል። እስረኞቹ ተፈቱ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እስኪገናኙ ድረስ ረዘም ያለ ሰአት ቢወስድም ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ግን አልተቋረጡም። ​​​​​​​

https://p.dw.com/p/2r1Ym
Äthiopien Gudina Freilassung
ምስል DW/G. Tedla Hailegiorgis

የዶ/ር መረራ ጉዲና እና ሌሎች እስረኞች መለቀቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት

ዛሬ ረፋዱ ላይ ኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ከፍተኛ ትኩረት የሳበ አንድ ጉዳይ ተከስቶ ነበር። የበርካቶችን ትኩረት የሳበው ይሕ ጉዳይም፦ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 እስረኞች ከእስር መለቀቃቸውን ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ዘዴዎች መዘገባቸው ነው። መገናኛ ዘዴዎቹ፦ እስረኞቹ የተለቀቁት የኢትዮጵያ መንግሥት የመሰረተባቸዉን ክስ ስላቋረጠ መኾኑንም ጠቅሰዋል፤ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎችም ተስተጋብቷል። ተማን አህመድ የዶይቸ ቬለ የአማርኛ ክፍል ትዊተር ገጽ ላይ በአጭሩ፦  «መልካም ዜና» ብሎ ጽፏል።

በርካቶች የእስረኞቹን መፈታት በመልካም ዜና የወሰዱት ሲሆን፤ መንግሥት ቃል በገባው መሠረት ሌሎቹንም እስረኞች ያለ አንዳች ቅድመ ኹኔታ ይፍታ ሲሉ ድምጻቸውን አሰምቷዋል። ጋዜጠኛ ሞሐመድ አዴሞ በእንግሊዝኛ ያሰፈረው የትዊተር ጽሑፍ በኢትዮጵያ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች የማይፈቱ ከሆነ፦ «የመረራ መለቀቅ የይስሙላ እና ትርጉም አልባ ይኾናል» ሲል ይነበባል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ምክትል አቶ በቀለ ገርባ እና የፓርቲው አባላት በአጠቃላይ «ያለ አንዳች መንጓተት» ሊፈቱ እንደሚገባ ጠቅሷል።

ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ በበኩሉ ትዊተር ላይ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቋል። «ሁለት የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ዛሬ ተለቀዋል። ሌሎች የኮሚቴው አባላት ግን  አሁንም እስር ላይ ናቸው። ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፍቷቸው» ሲልም ጽፏል።  የዶክተር መረራ ጉዲና ጠበቃ የኾኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ ዛሬ ከእስር ከተፈቱት እስረኞች መካከል 95 በመቶው የእሳቸው ደንበኞች መኾናቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናገረዋል። ዶክተር መረራ የተፈቱትም ከ1 ዓመት ከ1 ወር ከ18 ቀን ቆይታ በኋላ መኾኑን አክለዋል።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በርካታ ደጋፊዎች በተለያዩ ቦታዎች ዶክተር መረራን ለመቀበል አደባባይ መውጣታቸውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭተዋል። መንግሥት ከፖለቲካ ኃይላት ጋር፦ «ሀቀኛ ድርድር» ማድረግ እንደሚጠበቅበት፤ ብሎም «ሁሉንም በእኩል የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር» ማድረግ እንደሚገባው ዶክተር መረራ በመገናኛ ብዙኃኑ ተናግረዋል የሚሉ መልእክቶችም በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተነበዋል። እስረኞች መለቀቃቸው ከመነገሩ ቀደም ብሎ ዶክተር መረራ ከበስተኋላ ነጠል ብለው፤ ከፊት ደግሞ በርካታ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው የሚታዩበት ፎቶግራፍ ተሰራጭቶ ነበር። በፎቶግራፉ ላይ ብርትኳንማ የእስር ቤት ቱታ የለበሱ ሰዎችም ይታያሉ። ፎቶግራፎቹ እስረኞች ከመለቀቃቸው አስቀድሞ ቂሊንጦ እስር ቤት «ስልጠና» ሲሰጣቸው የሚያሳይ መኾኑም ተገልጧል።

በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተጻፉ መልእክቶ መካከል የተወሰኑትን እናሰማችሁ። «እስቲ ሁሉንም ፍቷቸው። ሀገራችን ሰላም እድትሆንልን የፈጣሪ በረከት እዲመለስላት።  እንኳን ደስ አላቸው ለቤተሰቦቻቸው» የምሕረት ዳኜ መልእክት ነው።  ዮዲት አበበ፦ «ሁሉም ከእስር ተፈተው ወደቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ እንፀልያለን» ብላለች።  «ወዶ ሳይኾን ተገዶ ነው የሚፈታው» ያለው ጂማ አባጅፋር ነው። መኩሪያ ግርማ፦ «ፍቅር ሰላም ለኢትዮጵያ፤ በህዝቦቿ ልብ ውስጥ ፍቅርን፣ ርህራሄን፣ መግባባትን፣ አንድነትን ከብሄር ጎጥነት ይልቅ የኢትዮጵያዊ አንድነትን ሙላው።ኢትዬጵያ ለዘላለም ትኑር» ሲል ጽፏል። ሰለሞን ብርሃነ ነጋሲ በበኩሉ፦ ሌሎቹስ እስረኞች ይፈቱ እንደሆን ጠይቋል።  «ዶ/ር መረራ ቀድሞውንም ወንጀልም አልሠራም ነፃነታችንን ስጡን አለ እንጂ» ያለው ብርሃነ፦ «አሁንም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱልን፤ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በቀለ ገርባ፣ አንዱአለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ኮነሬል ደመቀ እና ሌሎችም ይፈቱልን» ብሏል።

ዛሬ ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ከጥቂት ሰአታት በፊት እቤታቸው መግባታቸውን ከእስር ቤት የተቀበሏቸው ለዶይቸ ቬለ አረጋገጡ።

እናና የኋላ፦ «ገና ጀግኖች ይቀራሉ» ብላለች። መንግሥት 528 እስረኞችን ሰሞኑን በተከታታይ እንደሚፈታ አስታውቆ ነበር። ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሁለት ሳምንት በፊት«አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞች» እንደሚፈቱ፤ የማሰቃያ ተግባር የሚፈጸምበት ማእከላዊም እንደሚዘጋ በጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኩል ይፋ ካደረገ ሁለት ሳምንት አልፎታል።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Lei

ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ግለሰቦች

«በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ዶ/ር #መረራ #ጉድናን ጨምሮ በአዲስ አበባ ታስረው የነበሩ 115 እስረኞች መለቀቃቸው አስደስቶታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቷን የፖሊቲካ ምህዳር ለማስፋት አስፈላጊ የሆነውን ይህን እርምጃ መውሰዱ ይበል የሚያሰኝ ነው። በኢትዮጵያ ሁሉም የፖሊቲካ ኃይሎች ድምጻችው እንዲሰማና አሁን በአገሪቷ የሚታዩ ውጥረቶች ዘላቂ መፍትሔ ይገኝላቸው ዘንድ ቀጣይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኤምባሲው ያበረታታል።»

የአሜሪካን ኤምባሴ ትናንት ባወጣው መግለጫው፦ «የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ መሪዎችን ጨምሮ የእስረኞችን ክስ አቋርጦ ምሕረት ለማድረግ መወሰኑን» እንደሚያበረታታ አስታውቋል። የእስረኞች መፈታት ጉዳይንም «ለኢትዮጵያውያን በመላ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ተጨባጭ ርምጃ» አድርጎ እንደሚወስደው አስታውቋል።  

የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት፤ የአውሮጳ ምክር ቤት አባሏት የእንደራሴ አና ጎሜሽ «ዶክተር መረራ ጉዲና በመፈታታቸው ታላቅ ደስታ እና እፎይታ ነው የተሰማኝ። የእሳቸው እስር የኢሕአዴግ መንግሥት ጨቋኝነትን የሚያሳይ ነው። መለቀቃቸው ደግሞ የዚህ መንግሥት ፍጻሜ መዳረሱን ያሳያል» ሲሉ በእንግሊዝኛ ትዊተር ላይ ጽፈዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ነጋሽ መሐመድ