1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእርቀ ሰላም ማብሰሪያ ጉባኤ በፍራንክፈርት ተካሄደ

እሑድ፣ መስከረም 27 2011

በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አህጉረ ስብከት የእርስ በርስ ትውውቅ የሰላም ማብሠሪያ እና የአንድነት ልዩ ጉባኤ ዛሬ አካሄዱ። በጉባኤው ላይ በአውሮፓ ልዩ ልዩ ከተሞች የተቋቋሙ አገረ ስብከት ተጠሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተካፋይ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/365xd
Äthiopische Orthodoxe Kirchenvereinigung in Europa
ምስል DW/ E.Fekade

የእርቀ ሰላም ማብሰሪያ ጉባኤ በፍራንክፈርት ተካሄደ

ላለፉት 27 ዓመታት ተከፋፍሎ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሁለቱ ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ የተፈጠረውን እርቀ ሰላም የሚያበስር ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ከሁለት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ ከ 25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል። በዛሬው ዕለት ደግሞ በመላው አውሮፓ የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት ተመሳሳይ የሰላም የትውውቅ እና የአንድነት ማብሰሪያ እንዲሁም አውሮፓ አቀፍ የጋራ ማህበረ ካህናት ምሥረታ ጉባኤ ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን አካሂደዋል።  

የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ማጠናከር እና ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላም ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ባደረገው በዚህ ታላቅ ጉባኤም በአውሮፓ ልዩ ልዩ ከተሞች የተቋቋሙ አገረ ስብከት ተጠሪዎች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ካህናት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች እና መንፈሳውያን ማህበራት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተካፋይ ሆነዋል።  ጉባኤውን በጊዜያዊ ኮሚቴ ርዕሰ መንበርነት የመሩት መሪጌታ ብስራት ካሳሁን "ተበታትና የነበረችው ታላቋ ቤተክርስቲያን ወደ አንድነት መምጣቷ በሃዘን ተሰብሮ የቆየውን የምዕመናኑን ልብ የጠገነ በአገራችን ለተጀመረው ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴም በተቀናጀ መልኩ እገዛ ለማበርከት እጅግ ጠቃሚ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

Äthiopische Orthodoxe Kirchenvereinigung in Europa
ምስል DW/ E.Fekade

ጉባኤው በአውሮፓ አቀፍ ደረጃ የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት የሚያጠናክር እና የምዕመናኑን ተሳትፎ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ የጋራ አውሮፓ አቀፍ የማህበረ ካህናት ማህበርም ዛሬ መስርቷል። ይህ ማህበር ከሃይማኖታዊ ተልዕኮ ባሻገር ለአገር ሰላም እና ልማትም ትልቅ እገዛ እንደሚያበረክት ነው የጉባኤው አስተባባሪዎች የገለጹልን።

ዛሬ በፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ደብር የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና በጠበቀ መልኩ በጸሎት በዝማሬ እና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ መርሃግብሮች በተከናወነው የሰላም እና አንድነት ጉባኤ የሁለቱ ሲኖዶስ መዋሃድ በአገር ውስጥም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተክርስቲያኒቱ በምልዓት እንድትጠናከር ይረዳል ሲሉ የዕምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል። ከአንድ ሲኖዶስ መመሪያ እየተቀበለች አገልግሎቷን እንድታስፋፋ እና ምዕመናኑም ሳይከፋፈሉ በሁሉም አብያተ ክርስትያናት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ስለሚያግዝ በውህደቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል የጉባኤው ታዳሚዎች።

በፈቃዱ የሰበሰበንን ፈጣሪ አምላክ ልናመሰግነው አገርን እና ቤተክርስቲያንንም እየጠበቅን ልንተጋ ይገባል ሲሉ ለዕምነቱ ተከታዮች መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት የመጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ነበሩ። የጉባኤው ተሳታፊዎች የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ለማስጠበቅ እና የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት ለምዕመናኑ ለማበርከት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተግተው በጋራ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ልደት አበበ