1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ

ዓርብ፣ ሐምሌ 6 2010

የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ  ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ሲል የኢትዮጵያ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት  ገለፀ።የፕሬዝዳንቱ  የ3 ቀናት ጉብኝት በሀገራቱ መካከከል የተሟላ ሰላም፤ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የአኮኖሚ ትስስር የሚበሰርበት ታላቅ ምዕራፍ መሆኑን  ፅ/ቤቱ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/31QKo
Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

Eritrea leader Visits Ethiopia on Sturday - MP3-Stereo


ጉብኝቱን የተሳካ ለማድረግም በመንግስት በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉን ፅ/ቤቱ ገልፆ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።ላለፉት 20 ዓመታት ዝግ የነበረዉ የኤርትራ ኢምባሲ በይፋ እንደሚከፈትም ታዉቋል።
በግንቦት 1990 ዓ/ም በተከሰተዉ የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ሳቢያ  ላለፉት 20 ዓመታት ተቋርጦ የቆየዉን የሁለቱ ሀገራት  ግንኙነት ለማደስ ኢትዮጵያ  ያቀረቡችዉን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በኤርትራ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር የተመራ የልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ይታወሳል።በኢትዮጵያ በኩልም  ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያለፈዉ ሀምሌ 1 ቀን 2010 ወደ ኤርትራ አቅንተዉ የሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል።  በነገዉ ዕለት ደግሞ የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ  ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የኢትዮጵያ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ገልጿል።የጽ/ቤቱ ሀላፊ  አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በኤርትራ የነበረዉ በፍቅር የተሞላ አቀባበል በኢትዮጵያ እንዲደገም ለመላዉ ህዝብ ጥሪ አቅርበዋል።
የፕሬዝዳንቱን የ3 ቀናት ጉብኝት የተሳካ ለማድረግ መንግስት በሰላምና በፀጥታ ረገድ አስፈላጊዉን ዝግጅት ማድረጉን የገለፁት ሀላፊዉ፤ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ትስስር የሚጠናክርና የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ንግግር የሚያደርጉበት  «የሰላም ማብሰሪያ» መድረክ እንደሚዘጋጅም አስታዉቀዋል።  ዝግጅቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ለምስራቅ አፍሪቃ ሀገሮች የጋራ ብልፅግና ማብሰሪያም ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ገብረ መድህን ገ/ሚካኤል የመቀሌ ዩቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና በኢትዮ ኤርትራ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ባለሙያ ናቸዉ።እሳቸዉ እንደሚሉት ባለፉት 20 ዓመታት የሁለቱ ሀገሮች ህዝቦችና መንግስታት በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ማግኘት ይገባቸዉ የነበሩ ጥቅሞችን አጥተዉ የቆዩ በመሆናቸዉ የአሁኑ የሰላም ጅማሬ ከመንግስት ለመንግስት ግንኙነት ባሻገር ለሁለቱ ሀጋራት ህዝቦች አንድምታዉ ከፍ ያለ ነዉ ።
እንደ አቶ ገብረ መድህን ገለፃ በመሪዎች ደረጃ የተጀመረዉን ይህን የሰላም ሂደት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በፍጥነት ማሸጋገር ያስፈልጋል።የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ለአካባቢዉ ሀገራት የሚሰጠዉ የዲፕሎማሲ ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑም የሰላም ሂደቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥልም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወጥ በሆነ የህግና የስምምነት መዕቀፍ መመራት እንዳለበትም ይላሉ።
የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኙት በጎርጎሮሳዊዉ 1996 ዓ/ም ሲሆን ነገ የሚጀመረዉን የፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጉብኝት ተከትሎ ላለፉት 20 ዓመታት ዝግ የነበረዉ የኤርትራ ኢምባሲ በይፋ እንደሚከፈት የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት አስታዉቋል።

Eritrea Treffen Abiy Ahmed und Isaias Afwerk  in Asmara
ምስል picture-alliance/dpa/ERITV
Äthiopischer Ministerpräsident Abiy Ahmed beim Staatsbesuch in Eritrea
ምስል Twitter/@fitsumaregaa

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ