1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦ የኢትዮ-ኤርትራ አዲስ ግንኙነት ተስፋና ተግዳሮት

እሑድ፣ ሐምሌ 15 2010

የኢትዮ-ኤርትራ አዲስ ግንኙነት አብዛኛዎቹ ቢደግፉትም፤ በኢትዮጵያውያን በኩል የድንበር አከላለሉ፤ በድንበር አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ የወደፊት ኑሮ ፤ዋስትናስ ምንድን ነው የሚሉ አሉ። ኤርትራውያን በበኩላቸዉ የኢትዮጵያዉ ዓይነት ለውጥ ኤርትራ ዉስጥም ካልተካሄደ በሕገ መንግሥት፤ በፍርድ ቤት ስርዓት ካልተመራን፤ ስምምነቱ ዘላቂ አይሆንም ይላሉ።

https://p.dw.com/p/31ryX
Äthiopien und Eritrea Frieden Logo
ምስል DW/S. Fekade

ውይይት፦ የሁለቱ ሃገራት መሰረታዊ ችግር መፈተሽ ይኖርበታል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ስልጣን ከያዙ ሐምሌ 4፣ 2010ዓ.ም 100 ቀን ሞላቸዉ። በዚህ ጊዜ ዉስጥ በኢትዮጵያ በርካታ ለዉጦች አድርገዋል። የፖለቲካ እስረኞች ጋዜጠኞች ተፈተዋል፤ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ መገናኛ ዘዴዎችን ክስና የአሸባሪነት ፍረጃ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቷል፤  ሌሎች በርካታ ርምጃዎችም ተወስደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከኢትዮጵያ አልፈዉ ከአጎራባች ሃገራት በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበረዉን ግንኙነት ለማሻሻል የወሰዱት ርምጃ ጥሩ ዉጤት እያሳየ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈዉ ሐምሌ1 እና 2 አስመራን ጎብኝተዋል። ሳምንት ሳይሞላቸዉ የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ከሐምሌ 7 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ኢትዮጵያን ጎብኝተዉ ከደማቅ  አቀባበል እና መስተንግዶ በኋላ ተሸኝተዋል። ይህም ሁለቱ ሃገራት በጠላትነት ከመተያየት ወደ ወዳጅነት መሸጋገራቸውን የሚያመላክት ነዉ ተብሏል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያዉ ጉብኝታቸዉ ባሰሙት ንግግር «ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት ሕዝቦች ናቸዉ ብሎ የሚያስብ ሃቁን የማያዉቅ ነዉ፤ እኛ አንድ ነን» ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ ከተመለሱ በኃላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የመጀመርያዉን የመንገደኞች አዉሮፕላን መደበኛ በረራ ጀምሮአል። የአሰብ ወደብ አፋጣኝ አገልግሎት የሚጀምርበት ሁኔታ እንዲመቻች ሁለቱ ሀገራት ዝግጅት ጀምረዋል። የኢትዮጵያና ኤርትራን አዲስ ግንኙነት አብዛኛዎቹ ዜጎቻቸው ቢደግፉትም አንዳንድ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ወገኖች አልጠፉም። ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በሁለቱ ሃገራት መካከል ድንበር የለም ቢሉም በኢትዮጵያውያን በኩል የድንበር አከላለሉ፣ በድንበር አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ የወደፊት ኑሮ ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዋስትናስ ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ይሰማሉ።  ኤርትራውያን ደግሞ የኢትዮጵያዉ ዓይነት ለውጥ ኤርትራ ዉስጥም ካልተደረገ፤ ሃገሪቱ፤ በሕገ መንግሥት፤ በፓርላማ፤ በፍርድ ቤት ስርዓት ካልተመራች፤ አሁን የሚደረገዉ ስምምነት ረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አይሆንም ሲሉ ጥርጣሪያቸዉን ይናገራሉ። በዛሬዉ እንወያይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን አዲስ የወዳጅነት ጉዞ ተግዳሮቶቹ እና ተስፋውን እንመለከታለን። በዉይይቱ እንዲሳተፉ የጋበዝናቸዉ አቶ ዩሱፍ ያሲን ፣የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ እና ደራሲ፣ አቶ ደሳለኝ በረከት፤ ብራይት ፊዮቸር የተሰኘ የኤርትራ ወጣቶች ንቅናቄ ቃል አቀባይ እና ከፔን ኤርትራ መስራቾች አንዱ፤ አቶ ብርሀነ መዋ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንት ናቸው።

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ