1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ግጭት

ሐሙስ፣ ሰኔ 21 2010

መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶችና አደጋዎች በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሙከራዎች ይላቸዋል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ደግሞ ምክንያቱ ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ።

https://p.dw.com/p/30UxA
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

የኢትዮጵያ ግጭት፣ መንስኤ እና መፍትሄው

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ልዩ ልዩ አደጋዎች እና ግጭቶች መድረሳቸው ቀጥሏል። መንግሥት ካለፈው ቅዳሜው የመስቀል አደባባዩ የቦምብ ጥቃት በኋላ የፀጥታ ስጋት መኖሩን አስታውቆ ኅብረተሰቡም ከፀጥታ ጠባቂዎች ጎን እንዲቆም ጠይቋል። ስለ አደጋዎቹ እና ግጭቶቹ መንስኤዎችና መፍትሄዎች ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ እና የፀጥታ ጉዳዮች ተንታኞች መንስኤዎቹ የተለያዩ መሆናቸው ገልጸዋል። መፍትሄውንም ጠቁመዋል። ያነጋገረቻቸው ኂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች። 
በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም የሚነሱት ግጭቶች ቀጥለዋል። በግጭቶቹ የሰዎች ሕይወት እያለፈ የአካል ጉዳትም እየደረሰ ነው። ንብረት ይወድማል፣ ይዘረፋል። ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀያቸው በኃይል የሚፈናቀሉ አለያም በስጋት የሚሸሹት ብዙ ናቸው። ባለፈው ሰሞን በደቡብ እና በኦሮምያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የደረሱት ግጭቶች ነበሩ ጎልተው የሚሰሙት። በዚህ ሳምንት ደግሞ በአሶሳ ተመሳሳይ ችግር ደርሷል። በአፋርም እንዲሁ ተቃውሞዎች ይሰማሉ። አደጋዎችም እየደረሱ ነው። መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶችና አደጋዎች በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሙከራዎች ይላቸዋል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ደግሞ ምክንያቱ ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ እና የፀጥታ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ የችግሩ መንስኤ ናቸው ያሏቸውን በሦስት ይከፍሉዋቸዋል።
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሠ መንግሥት የፀጥታ ስጋቱን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ተገቢ ነው ይላሉ። ችግሮቹ በርሳቸው አስተያየት ውስብስብ ናቸው። በተለየ የብሔር የሚባሉት ግጭቶች ደግሞ አዲስ አይደሉም። አሁን የተነሱበት ምክንያት ግን ከቀድሞው ይለያል።  ሆኖም የችግሮቹን መንስኤዎች መርምሮ በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ከምንም በላይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንደ አቶ ሃሌሉያ ። ችግሮቹ ውስብስብ ናቸው የሚሉት አቶ ቻላቸውም በመፍትሄ ፍለጋው ሂደት የአሁኑ የኢትዮጵያ  ለውጥ አካሄድ መጤን እንደሚገባው ያሳስባሉ። ሌሎች መፍትሄ ያሏቸውንም ዘርዝረዋል። በአቶ ቻላቸው አስተያየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፌደሬሽን እና የክልል ምክር ቤቶችን የመሳሰሉ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ማጠናከር ሌላው ጠቃሚ እርምጃ ሊሆን ይችላል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ