1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የሁለቱ ወገኖች አተካሮ ኢትዮጵያ የውጭ ባለወረቶች ለመሳብ የምታደርገውን ጥረት ይጎዳል

ረቡዕ፣ ሰኔ 21 2009

የከፋ ፖለቲካዊ ተቃዎሞ ያስተናገደው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ያሳለፈው ውሳኔ ከናይጀሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ የስሚንቶ ፋብሪካ ጋር አቃቅሮታል። የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ያሳለፈው ውሳኔ ኩባንያው ከተሰጠው የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፈቃድ ጋር ይጣጣም ይሆን? ልዩነቱስ ከመካረሩ በፊት ለምን አልተፈታም?

https://p.dw.com/p/2faK8
Frankreich Paris - Aliko Dangote
ምስል picture-alliance/dpa/C. Petit Tesson

የኢትዮጵያና የዳንጎቲ ሲሚንቶ ፋብሪካ አተካራ

ናይጄሪያዊው ባለጠጋ አሊኮ ዳንጎቴ የኢትዮጵያ የስሚንቶ ፋብሪካቸውን ልዘጋ እችላለሁ ሲሉ የሰጡት ማስጠንቀቂያ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና የፌድራል መንግሥት ባለስልጣናትን አስቆጥቷል። የዳንጎቴ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢድዊን ዴቫኩማር በገበያ እና ንግድ ላይ ለሚያተኩረው ብሎምበርግ መፅሔት በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ፣ በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ለፋብሪካው የስሚንቶ ምርት የሚያስፈልጉትን የፑሚስ አሸዋ እና የሸክላ ግብዓቶች የተደራጁ የአካባቢው ወጣቶች እንዲያቀርቡ ፣ አለበለዚያ ለሚፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት እንዲወስዱ መጠየቃቸውን ተናግረዋል። ብሎምበርግ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር የፃፈውን ደብዳቤ መመልከቱን ትክክለኛነቱንም ማረጋገጡን ፅፏል። ኢድዊን ዴቫኩማር የዳንጎቴ ኩባንያ ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ ከሆነችው የናይጀሪያዋ ሌጎስ ሆነው በሰጡት አስተያየት የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር እርምጃ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰጣቸውን የማዕድን ቁፋሮ ፈቃድ ይጥሳል ሲሉ ወቅሰዋል። 

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ይኸው የተሰነዘረው አስተያየት አዲስ አበባ ከሚገኘው ቢሮ ይልቅ ከዋና መሥሪያ ቤቱ መደመጡ አልተዋጠላቸውም። የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር የአካባቢው ወጣቶች ለስሚንቶ ምርት አስፈላጊ ግብዓቶችን ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ በሚል ያሰማው ጥያቄ የኩባንያውን መብት አይነካም የሚሉት አቶ አዲሱ የዳንጎቴ ሰዎች ጥያቄውን ተስማምተው ተቀብለውት እንደነበር ይሞግታሉ። አንድ ኩባንያ ሲቋቋም ትርፍ የማግኘት አላማ እንዳለው ሁሉ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ትሩፋት ማምጣት ይገባዋል የሚሉት አቶ አዲሱ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ጥያቄ ''ምንም መብታቸውን የሚነካ ነገር የለውም'' ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አዲሱ አረጋ እንዳሉት ፣ በእርግጥ የአሊኮ ዳንጎቴ ኩባንያ የቀረበለትን ጥያቄ ተስማምቶ ስለመቀበሉ ማረጋገጥ አልተቻለም። የዳንጎቴ ስሚንቶ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ዲፕ ካማራ ለዶይቸ ቬለ እንዳሉት፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ መሥጠት የሚችሉት የኩባንያው ባለቤት አሊያም ዋናው መሥሪያ ቤት ናቸው። ሌጎስ የሚገኘው መሥሪያ ቤት በበኩሉ በኢ-ሜይል ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ነፍጓል።  

Afrika Klinker-Werk der Firma HeidelbergCement
ምስል HeidelbergCement

የዳንጎቴ ስሚንቶ ሥራ አስፈፃሚ ኢድዊን ዴቫኩማር የኢትዮጵያውን ማምረቻ ከመዝጋታቸው በፊት የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደሚጽፉ ለብሎምበርግ ነግረውታል። አቶ አዲሱ አረጋ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ጥያቄ የፋብሪካውን መብት የሚነካ አይደለም ይበሉ እንጂ ፣ ዳንጎቴ ከክልሉ ቀድሞ ከተሰጣቸው የመዋዕለ-ንዋይ እና የንግድ ፈቃድ ጋር ስለመጣጣሙ ግን የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ጥያቄ አላቸው። ''መጀመሪያ የመዋዕለ-ንዋይ እና የንግድ ፈቃድ በሚሰጣቸው ሰዓት እንዲያከናውኑት ከተሰጣቸው እና በይዞታነት እንዲያስተዳድሩት፤በምርት ሒደታቸውም አስገብተው እንዲሰሩትም መግባባት ላይ ከተደረሰበት በንግድ ፈቃዳቸው እና በመዋዕለ-ንዋይ ፈቃዳቸው ውስጥ ከተጠቃለለ ሒደት ውጪ የሆነ ነገር ነው'' 

የውጭ ባለወረቶች በሥራ ላይ እንዲሰማሩ የማስተዋወቁን ፍላጎታቸውን ሲያሳዩም የመመዝገብ እና ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እጅ ይገኛል። የውጭ ኩባንያዎች አሊያም ባለወረቶች 'ቢዝነስ ላይሰንስ' ተብሎ የሚጠራውን የመስሪያ ፈቃድ የሚያገኙት በሚሰማሩበት ክልል ነው። ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም። 

የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር በአካባቢው ስሚንቶ በማምረት ላይ የተሰማሩት የአሊኮ ዳንጎቴ እና የሜድሮክ ደርባን የመሳሰሉ ፋብሪካዎች የፑሚስ ማምረቻዎቻቸውን ለአካባቢው ወጣቶች አሳልፈው እንዲሰጡ የጠየቀው ባለፈው መጋቢት ወር ነበር። በወቅቱ የዳንጎቴ ኩባንያ የአስተዳደሩን ጥያቄ የመቀበል አዝማሚያ አሳይቶ ነበር። ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው የብሎምበርግ ዘገባ የዳንጎቴ የስሚንቶ ፋብሪካዎች ኃላፊ ኦነ ፋን ደር ዊይጅድ የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ጥያቄ በግብዓቶቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ እና የጥራት ጉድለት እስካላስከተለ ድረስ ኩባንያው የቀረበለትን ውል ለመፈረም ፈቃደኛ መሆኑን መናገራቸውን አስነብቦ ነበር። ኦነ ፋን ደር ዊይጅድ አስተዳደሩ "ሊያስገድደን አይገባም" ሲሉ መናገራቸው ግን አልቀረም። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የዳንጎቴ ስሚንቶ ፋብሪካ የቀረበውን ስምምነት ፈርሟል ሲሉ ይናገራሉ።ኹከት የቀላቀለ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ወጣቶች ላይ ለበረታው ሥራ አጥነት መፍትሔ ሲያማትር እነሆ ወራት አልፈዋል። ለወራት በዘለቀው ተቃውሞ የዳንጎቴ ስሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ የመንግሥት እና የባለወረቶች ተቋማት እና ንብረቶች ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ ካደረገ በኋላ በተለይ በተቃውሞው ለተሳተፉ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ተፍ ተፍ ሲል ይታያል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የስሚንቶ ምርት ግብዓቶችን ጨምሮ የማዕድን ማውጫዎችን ነጥቆ ለወጣቶች በመስጠት ከ45,000 በላይ የሥራ እድል መፍጠሩን አቶ አዲሱ ይናገራሉ።

Derba Cement Factory
ምስል DW

በኦሮሚያ ክልል ሙገር አደበርን ወረዳ የሚገኘው የዳንጎቴ ስሚንቶ ፋብሪካ ማምረት ከጀመረ ሁለት አመታት አልፈውታል። 1,000 ሰራተኞች የቀጠረው ፋብሪካው በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ስሚንቶ የማምረት አቅም አለው። ምርቱን ኬንያን ወደ መሰሉ የጎረቤት አገራት እስከ መሸጥ የደረሰው የናይጀሪያዊው ባለጠጋ ፋብሪካ በኢትዮጵያ አለቅጥ ተወዶ የነበረውን የስሚንቶ ዋጋ በማረጋጋቱ ረገድ ከፍ ያለ ሚና እንደተጫወተ ይነገርለታል። የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም አሁን የተፈጠረው መቃቃር የስሚንቶ ፋብሪካውን መዘጋት እንዳያስከትል ያሰጋቸዋል። 
 በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና በአሊኮ ዳንጎቴ ኩባንያ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አተካሮ አገሪቱ የውጭ ባለወረቶችን ቀልብ ለመሳብ የምታደርገውን ጥረት ክፍኛ እንደሚጎዳ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። የኤኮኖሚ ባለሙያው በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከዚህ ደረጃ መድረሱ በራሱ አስገርሟቸዋል።  "እኛ ሕገ-መንግሥቱን የሚጥስ አንድም ነገር አናደርግም" የሚሉት አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ባለሐብቶች ነፃነት ተሰምቷቸው እንዲሰሩ እንሻለን ብለዋል። 

እሸቴ በቀለ 
አርያም ተክሌ