1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ላይ ያተኮረ ጥናት ይፋ ሆነ

እሑድ፣ ጥር 5 2011

በሳተላይት የተደገፉ መረጃዎችን በማሰባሰብ የኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ሥነ-ምድራዊ እንቅስቃሴ ላይ ሲካሄድ የቆየው የጥናት ውጤት ይፋ ሆነ። በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ በመካከለኛው የመሬት ክፍል ውስጥ የሚገኘው የእሳተ ጎሞራ ቅልጠት መጠን ቀስ በቀስ ወደላይ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ እንደሚገኝ በጥናት መረጋገጡ ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/3BUaJ
Äthiopien Konferenz in Hawassa zum East African Rift Valley
ምስል DW/S. Wegayehu

የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ላይ ያተኮረ ጥናት ይፋ ሆነ

መነሻውን መካከለኛው ምሥራቅ ሶሪያ ያደረገው የምድራችን ታላቁ የስምጥ ሸለቆ መስመር ቀይ ባህርን ሰንጥቆ እሰከ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛንቢክ እንደሚዘልቅ ይነገርለታል ፡፡  የምስራቅና ደቡባዊ ኢትዮጲያ መልካምድርን ለሁለት ገምሶ የሚቋርጠው ታላቁ የስምጥ ሸለቆ የሰው ልጅን ጨምሮ በውስጡ ለሚኖሩ ፍጥረታት ትሩፋትም ሥጋትም ሥለመሆኑ የስነ ምድር ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ 

የተለያዩ አለምአቀፍ የከርሰ ምድር ተማራማሪዎች የተሳተፉበትና በዚሁ የስምጥ ሸለቆ ስነ ምድራዊ ባህሪያት ላይ ያተኮረ የምርምር ጉባኤ አዚህ ሀዋሳ ላይ ተካሂዷል፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድርና የስነ ህዋ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አታላይ አየለ ለዲ ደብሊው አንዳሉት በምርምር ጉባዔው በኢትዮጲያ የስምጥ ሸለቆ ስነ ምድራዊ እንቅስቃሴ ላይ የተካሄደ የምርምር ውጤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የብርቴኒያ ብሄራዊ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ላለፉት አራት ዓመታት በጋራ በካሄዱት በዚሁ ጥናት በስምጥ ሸለቆው ባህሪያት ዙሪያ ጠቃሚ መረጃዎች መገኘታቸውን ዶክተር አታላይ ገልጸዋል ፡፡ በተካሄደው ጥናት ከሀዋሳ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ኮርቤቲና አሊቶ በተባሉ ሥፍራዎች ያለው የእሳተ ጎሞራ ቅልጠት መጠን ቀስበቀስ ወደላይ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ እንደሚገኝ በጥናቱ መረጋገጡን ዶክተር አታላይ ተናግረዋል፡፡ 
ይህም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚታየው የመሬት ንዝረት ፤ መንሸራተትና መሰንጠቅ በታችኛው የመሬት ክፍል ከሚገኘው የእሳተ ጎሞራ እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡ 

የምርምር ቡድኑ አስተባባሪ ካትሪን ዌላ ‹‹ ላለፉት አራት ዓመታት ለጥናቱ የሚያግዙ በርካታ የመረጃ ግበዓቶችን ለማግኘት ችለናል ፡፡ በተለይም የቁሳዊና የንጥረ ነገረ ናሙናዎችን በማሰባሰብ በጥልቀት ፈትሸናል፡፡ የጥናቱ ሂደት የተከናወነው የመሬት ውስጥ የርቀት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን የመትከልና ከህዋ የሳተላይት ቅኝት ማድረግን ያከተተ ነው፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረትም በመካከለኛው የመሬት ክፍል በሚገኘው የቀለጠ የአሳተ ጎሞራ አለት ዙሪያ ቀደምሲል የነበረንን ዕውቀት ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ እንዲሁም የቀጣይ ስነ ምድራዊ ባህሪውን ለመለየትና ሊስከትል የሚችለውን አካባቢያዊ ተፅኖ አስቀድሞ ለመረዳት ያስችላል ›› ሲሉ ተናግረዋል። ለሶስት ቀናት በተካሄደው ዓለምአቀፍ የስምጥ ሸለቆ ምርምር ጉባዔ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ተማራማሪዎችን ጨምሮ ከአውሮፓና ፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ ፤ ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካ አገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ