1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃዉያን ስደኞች ሞትና እንግልት በየመን

ዓርብ፣ የካቲት 16 2010

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /UNCHR/ ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ ባለፈዉ ጥር ወር መጨረሻ ብቻ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያና  የሶማሊያ ስደተኞች ወደ የመን ባህረ ሰላጤ ተጉዘዋል። በዚህ የባህር ላይ ጉዞ በደረሰ አደጋም 30 ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል።

https://p.dw.com/p/2swLR
Jemen afrikanische Migranten in Harad
ምስል DW/Saeed Al soofi

Flucht in den krieg - MP3-Stereo

በዚህ መንገድ በርካታ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ወደ የመን ጉዞ ያደርጋሉ ።ነገር ግን በሀገሪቱ በሚካሄደዉ የርስበርስ ጦርነት ሳቢያ የደረሰዉ ሰብዓዊ ቀዉስ እነዚህን ስደተኞች በህገ ወጥ የሰዉ አዘዋዋሪወች እጅ እንዲወድቁ እያደረጋቸዉ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። የመንንና ሶማሊያን የሚለየዉ የኤደን ባህረ ሰላጤ በዓለማችን ትልቁ የባህር ንግድ መስመር ነዉ።በእስያና በአዉሮጳ መካከልም ትልቁ  መገናኛ  ነዉ።ይህ የንግድ መስመር በአፍሪቃ ቀንድና በአረብ ባህረ ሰላጤ መካከል የሚደረገዉን ስደትም ያስተናግዳል። 
በዚህ  መንገድ በተለይ ወደ ሳዉዲ አረቢያ የሚደረገዉ ስደት የቆየና የተለመደ መሆኑን ከዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት ካትሪን ኖርዚንግ ያብራራሉ።
« ይህ በፍጹም አዲስ ልማድ አይደለም።ከጅቡቲና ከሶማሊያ ተነስተዉ ኢትዮጵያዉያንና ሶማሊያዉያን ባህር አቋርጠዉ ወደ የመን መጓዝ የተለመደ ነዉ።በተለይ ወደ ሳዉዲ አረቢያ ለመሸጋገር ።በታሪክ በርካታ ኢትዮጵያዉያንና ሶማሊያዉያን ከጦርነቱ በፊትም የመን ይኖራሉ።ይህ ፍጹም አዲስ ነዉ ብዬ ልናገር አልችልም።ነገር ግን ግጭት በሰፈነባት የመን ስደተኞች አሁንም ድረስ መምጣት መቀጠላቸዉ አስገራሚ ነዉ ብዬ አስባለሁ።»
በነዳጅ ዘይት የበለጸጉት ሳዉዲ አረቢያና ሌሎች ሀብታም የባህረ ሰላጤው መንግስታት በአንድ በኩል በአፍሪቃ ቀንድ ለአመታት በዘለቀ የርስበርስ ጦርነት የደቀቀችዉ የዓላማችን ድሃዋ ሀገር ሶማሊያ በሌላ በኩል ፣በመሃል ደግሞ  በጦርነት የምትታመሰዉ የመን ትገኛለች።ይች ሀገር ታዲያ ከ 2014 ጀምሮ በሚካሄደዉ የርስበርስ ጦረነት ሳቢያ በሺ የሚቆጠሩ የሀገሬዉ ዜጎች ለሞት ሚሊዮኖች ደግሞ ለስደት መዳረጋቸዉን መረጃወች ያሳያሉ ።ያም ሆኖ ግን የአፍሪቃ ቀንድ ስደተኞች አሁንም ወደዚች ሀገር መጓዛቸዉን አላቋረጡም።
እንደ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት /IOM/ በዚህ ሁኔታ  ሞትና እንግልት እያጋጥማቸዉም ቢሆንም ባለፈዉ ዓመት ብቻ  ወደ 87 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ ባህር አቋርጠዉ ወደ የመን ጉዞ አድርገዋል።በዚህ ጉዞም በርካቶች ህይወታቸዉን አጥተዋል።

Jemen afrikanische Migranten in Harad
ምስል DW/Alsoofi

«በጀልባዉ ላይ ግርግር ተነሳ »ይላሉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ዊሊያም ስፔንሰር  ባለፈዉ ጥር ወር መጨረሻ  የደረሰዉን የአደጋ ሁኔታዉ ሲገልጹ «በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአብዛኛዉ ከሶማሊያና ከኢትዮጵያ የሆኑ ጀልባዉ ላይ ነበሩ። እናም ጀልባዉን የሸጡት ህገወጥ የሰዉ አዘዋዋሪወች መንገደኖቹን በድንገት ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቅ ጀመሩ።የተወሰኑት ሲከፍሉ ሌሎቹ ግን መክፈል አልቻሉም ወይም ተቃወሙ።በዚህ ጊዜ የህገወጥ ደላሎቹ ባልከፈሉ ሰዎች ላይ መተኮስ ጀመሩ።እናም ግርግር ተነሳና ጀልባዋ ወደ አንድ ጎን ማዘንበል ጀመረች።በዚህ ጊዜ ብዙ ሰዎች ሰጠሙ።ቢያንስ 30 ሰዎች ሞተዋል።»
ይላሉ ስፔንሰር ከአደጋዉ ከተረፉ ሰዎች ሰማሁ ብለዉ እንደገለጹት።እንደእሳቸዉ ገለጻ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ያም ሆኖ ግን ሰዎች ምርጫ ስሌላቸዉ  አሁንም ድረስ ይሰደዳሉ ሲሉ ያክላሉ።ብዙዎቹም ከጦርነትና ከድህነት ሸሽተዉ የመጡ በመሆናቸዉም ወደ ሀገራቸዉ መመለስ አይፈልጉም ሲሉ ያብራራሉ።
«ሰዎች ህይወታቸዉን አደጋ ዉስጥ ከተዉ ወደስደት የሚያመሩበት ምክንያት ምርጫ ስሌለላቸዉ ነዉ ።ምርጫ ካለ ማንም እዚህ አደጋ ዉስጥ አይገባም።በርካታ ሰወች የሚሰደዱት ድህነትን በመሸሽ የተሻለ የኢኮኖሚና የስራ ዕድል ፍለጋ ነዉ።ሌሎች ደግሞ በጦርነት ፣በግጭት፣በስቅይትና በሰብዓዊ መብት ረገጣ የተነሳ ነዉ።»
ሶማሊያዉያን በየመን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በኩል  በስደተኝነት መመዝገብ ይችላሉ ።ነገር ግን በሀገሪቱ ያለዉ ጦርነት ሁኔታዉን አስቸጋሪ አድርጎታል።በዚህ የተነሳ በርካታ ስደተኞች ለእንግልት፣ ለጥቃትና  ለእስራት የተጋለጡ መሆናቸዉ ይነጋራል።ሌሎች ደግሞ ለጉዞ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት አደንዛዥ ዕፅ  በሚመረትባቸዉ  ማሳዎች ለመስራት ይገደዳሉ። ከዓለም ዓቀፉ የስደት ድርጅት ካትሪን ኖርዝ እንደሚሉት ሁሉም አልሳካ ሲላቸዉ አንዳንድ ጊዜ ወደ ሀገራቸዉ እንድንመልሳቸዉ ይጠይቃሉ ይላሉ። 

Jemen afrikanische Migranten in Harad
ምስል DW/Saeed Al soofi

በዚህ ጊዜ ደህንነታቸዉ በተጠበቀ ሁኔታ ለመመለስ እንሞክራለን።ነገር ግን አብዛኛዎቹ የህገ ወጥ ደላሎችን በመተማመን ህይወታቸዉን ለእነሱ አሳልፈዉ ይሰጣሉ ሲሉ ነዉ ኖርዝ የሚናገሩት።
ዊሊያም ስፔንሰር ግን  ለስደተኞች ህጋዊ መንገዶችንና አማራጮችን ልናሳያቸዉ ይገባል ሲሉ ይሟገታሉ።

«እናም ለዚህ ነዉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNCR ሰዎች በጥንቃቄ  ደህንነታቸዉ ተጠብቆ እንድጓዙ ስለ ህጋዊ የደህንነት አማራጮች የሚሟገተዉ። ስደተኞችን መልሶ በማስፈር ፣ቤተሰብን እንደገና በማገናኘት፣ለስደተኞች የተማሪዎች ቪዛ መፍቀድ እና ሌሎች ህጋዊ መንገዶችን  በመጠቀም  ሰዎች በዚህ መንገድ ህይወታቸዉን አደጋ ላይ መጣል ሳያስፈልጋቸዉ እንድጓዙ ማድረግ ይቻላል።እነዚህን አሳዛኝ ታሪኮችም በዚህ መግታት ይቻላል።»

 ማሪቲና  ሽዋስኮቭሲኪ /ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ