1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የአዲስ አበባ ወጣቶች ይፈቱ»ና ሚንሥትሮቹ

ዓርብ፣ ጥቅምት 9 2011

በጦላይ በረሃ ታስረው የቆዩ የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲፈቱ የተደረገው ዘመቻ እና የወጣቶቹ መፈታት በማኅበራዊ መገኛ አውታሮች ሰፊ መነጋገሪያ ኾኗል። በአንጻሩ ሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶች መታሰራቸው ቁጣን አጭሯል። በኢትዮጵያ የሚንሥትሮች ሹመትም ሌላው መወያያ ርእስ ነበር። 

https://p.dw.com/p/36nVs
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

«ፍትኅ ለአዲስ አበባ ወጣቶች» በሚል ለሦስት ቀናት የቆየው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በተጠናቀቀ ማግስት ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች ለእስር ተዳርገው ከቆዩበት ጦላይ በረሃ መፈታታቸው ተሰምቷል። የወጣቶቹ መፈታት ግን በሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶች እስር መተካቱን በርካቶች ከቀድሞው ስርአት ያልተለየ የእስር «መተካካት» ሲሉ ተችተዋል። የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት የሚንሥትሮች ሹመት በሀገር ቤት እና ከሀገር ውጪ ሁለት መልክ ይዞ መነጋገሪያ ኾኗል። በውጭ ሃገራት የሚገኙ ነዋሪዎች እና የመገናኛ አውታሮች ከተሿሚ ሚንሥትሮች ግማሾቹ ሴቶች መኾናቸው ላይ በስፋት አተኩረው ዘግበዋል፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም በስፋት ተወያይተውበታል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን የሚንሥትሮቹ ሹመት ለየት ባለ መልኩም ታይቷል።  

የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዲፈቱ የሚጠይቅ የማኅበራዊ መገና ዘዴዎች የሦስት ቀን ዘመቻ የዘለቀው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ማለትም ከጥቅምት 5 እስከ 7 ቀን 2011ዓም ድረስ ነበር። በማግስቱ ፖሊስ ከአንድ ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች መፈታታቸውን ይፋ አደረገ። ፖሊስ ጊዜያቸውን ጨርሰው ነው የተፈቱት ቢልም በርካቶች የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ዘመቻው የፈጠረው ተጽንዖ ነው ብለዋል።

ፖሊስ ወንጀል መሥራቱ ያልተረጋገጠን ግለሰብ የማሰር ሥልጣን ማን ሰጠው? የሚል ጥያቄም ተበራክቶ ቆይቷል። ሚኪያስ ትዊተር ላይ ባሰፈረው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ፦ «ፖሊስ ግለሰቦችን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ወስዶ ምክር እና ስልጠና የመስጠት ሕጋዊ ሥልጣኑን ከየት ነው ያገኘው?!» ብሏል።

Äthiopien Zeynu Jemal
ምስል DW/T. Getachew

«በሕገወጥ መንገድ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ታጉረው ለወር ግድም የቆዩ ከአንድ ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች አሁን ተፈትተዋል»፣ ያለው የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን አባል አጥናፍ ብርሃኔ፦ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ወጣቶቹ ሥልጠናቸውን ስለማገባደዳቸው የተጠቀሙበትን ቃል አጽንዖት ሰጥቶበታል።  «ሥልጠናውን በተመለከተ "Brainwashing" የሚል ቃል ነው የተጠቀሙት» ብሏል። የቃሉ የአማርኛ አቻ ትርጉም  «ጽኑዕ በኾነ መልኩ በግዳጅ የፖለቲካ ወይንም የእምነት አመለካከትን ማስቀየር» እንደማለት ነው።

ዘሩባቤል ጌታቸዉ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «የአዲስ አበባ ወጣት ለምን ያለ ፍትህ ታሰረ? ብለን ስንጠይቅ "ቄሮን ወደ ከተማው አላስገባም ብሎ ነው" የሚሉ ሰዎች አሉ» ሲል ጽሑፉን ይጀምራል። «ያሳዝናልሲልም ይቀጥላል። «የአዲስ አበባ ወጣትኮ ቄሮ መስቀል አደባባይ ሲያደር "ይርባቸዋል" ብሎ ውሃና ምግብ ተሸክሞ የሄደ ወጣት ነው የአዲስ አበባ ወጣትኮ ደብረዘይት ድረሰ ሄዶ ኢሬቻ የሚከበርበትን ቦታ ያፀዳ ትሁት ወጣት ነው ሲልም አክሏል።

ሸሪፍ ሸሪፍ በበኩሉ፦ «ኦሮሞነትን አዲሳበቤው ላይ ለመጫን በማን አለብኚነት የሰው ቤት የኦነግን ባንዲራ ቀለም በመቀባት አያገባችሁም አዲሳባ የኛ ናት በሚል ጭፍን እሳቤ ይዘው የመጡትን ቄሮዎች በመቃዎማቸውና ስለ እኩልነት በመታገላቸው አዲሳበቤዎች ወንጀለኛ ተብለው ታፍሰው ሲታጎሩ ያለ ሕግ አግባብ መብታቸው ሲጣስ ገብተው የበጠበጧትና ያተራመሷት ንፁህ አየር ይተነፍሳሉ!!! አዲሱ ለውጥ አሰራር እንዲህ ከሆነ ለፊተኞቹ መልሱላቸው» ብሏል።

በለጠ አበበ ደግሞ፦ «ለምን እንደተከፈላቸው ጠ/ሚሩ መረጃ ካላቸው ከፋዮቹን መንካት ምን አስፈራቸቸው። ሁል ጊዜ ከኃላ ሆነው ግፊት የሚያደርጉ አሉ ሲሉ እንሰማለን ግን የሚሏቸው እንማንን እንደሆነ ግልፅ ሲያደርጉ ወይም እርምጃ ሲወስዱ አይታዩም። ድምፃዊዉ ወሬ ብቻ እንዳለው ሆነብኝ» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል።

ከዚህ ቀደም በፍትኅ እጦት ይሰቃዩ ለነበሩ ግለሰቦች የሽብር ወንጀል ክስን በነጻ ጥብቅና ያገለግል የነበረው ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሚካኤል መላኩ መታሰርም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ቁጣን አጭሯል። ቃልኪዳን ደርብ፦ «አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ትሁን» በሚል ርእስ ነው ጽሑፉን የሚጀምረው። «አዲስ አበባ በአዲስ አበቤዎች ትመራ ማለት የሚያሳስር ከሆነ እወነትም ሕግም የለም፤ መንግስትም የለም። እኛ ግን አሁንም አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ትሁን፤ በአዲስ አበቤዎች ትመራ እያልን እንጮሀለን» ብሏል።

Äthiopien Addis Abeba verhaftete Jugendliche freigelassen
ምስል Federal Government Communication Affairs Office of Ethiopia

ዲደብሊው ፌስቡክ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች የሚከተሉት ይገኙበታል። ኃይ ኃይ በሚል የእንግሊዝኛ ስም የቀረበ የፌስቡክ ጽሑፍ መልእክት፦ «የገጠር ሰው አይመራንም ማለት ምኑ ላይ ነው ወንጀሉ?» ሲል ያጠይቃል። ቴዎድሮስ ፈንታ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሚካኤል መላኩ ሐሙስ እለት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከቀረበባቸው ክስ አንዱን በማጣቀስ ቀጣዩን ብሏል። «ድሮ የኤርትራ ተላላኪ አሁን ደግሞ የፍልስጤም! ነገ የአሜሪካ እንደሚሉ አንጠራጠርም።»  ሳሙኤል ተፈራ፦ «‘ከፍልስጤም ኤምባሲ ጋር በመተባበር እስራኤልን መመከት የሚል አጋርነት እና ስልጠና ውስጥ ተሳትፈዋል‘ ምን ማለት ነው። እኛም ሳናውቅ እየሰለጠንን እንዳይሆን» የሚል አስተያየት አስፍሯል።  «ተጠርጣር መያዝና ማሰር ያለ እና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው» ያለው ጤና በየነ ነው። «የአፍሪቃ ፖለቲካ አሁንም እንቆቅልሽ ሆኗል። (አዲስ ታሳሪዎች)» የሚለው ደግሞ ዜድ ላሊበላዊ አስተያየት ነው።

እዛው የዲ ደብሊው የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶች የተስፋዬ ደሳለኝ እንዲህ ይነበባልን፦ «ጦላይ ወስደሃት ከሆነ ጥንቸል ራሷ ፍየል ነኝ ብላ ታምንልሃለች። ያለ ፍርድ ሂደት ጥፋተኛ ተብሎ ሰው ላይ መበየን እንደሚቻልም የሰማነው ከእናንተ ነው።» የሐቢብ ሙሐመድ አስተያየት እንዲህ ሰፍሯል፦ «ግን ቡራዩ ላይ የግድያና ዘረፋ የፈፀሙት ወጣቶች የት ናቸው አልተያዙም እንዴ? በተቃራኒው ሰላማዊ ወጣቶች ይታፈሱ የሚል ሕግ ወጥቷል እንዴ? በበኩሌ የአቶ ዘይኑ ጀማል የተዘበራረቀ ትርጉም የሌለው አነጋገር አልገባኝም።»

Äthiopien Addis Abeba, Unruhen
ምስል DW/B. ze Hailu

ሐዱሽ ገብረየሱስ፦ «ፓሊስ ምን እየሰራ ነው ሕግ አያከብርም እንዴ ስንል ነበር አሁን ደግሞ የሸገር ልጅ መታሰር የለበትም ማለት አንችልም። ላለ መታሰር ሕግ ማክበር የግድ ነው። ሰለሚፈቱ ደስ ይላል» ብሏል።  እሸቱ ሆማ ቄኖ በአጭሩ ያሰፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «ያኛው ኢህአዴግ አፍሶ ያጉር ነበር፣ ይኸኛው ኢህአዴግም አፍሶ አጉሯል።» አንተነህ አምባዬ፦ «ፖሊሥ አንደፈለገ አሥሮ በረሀ ላይ ወሥዶ ወር መረሃ-ግብር የመስጠት ሥልጣን አለው??» ሲል ጠይቋል። ፋሲለደስ እንዳለው ደግሞ የአዲስ አበባ ወጣቶች የተፈቱት፦ «ለጀርመን አቀባበል ነዉ፤ ተቃዉሞዉ አይቀሪ ነዉ» ብሏል።

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በሚመሩት መንግሥት ከተሾሙ 20 ሚንሥትሮች ግማሾቹ ሴቶች መኾናቸው በመላው ዓለም በርካቶችን አስደምሟል። ከ20 የሚንሥትሮች ሥልጣን ዐሥሩ ለሴቶች መሰጠቱ ላይም አተኩረው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተወያይተዋል። ኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በአንጻሩ የሹመት አሰጣጡ በብቃት ወይንስ ለኮታ ማሟያ ሲሉ በተጨማሪ አጠይቀዋል።  

ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ፦ «ለሸገር ከንቲባነት የቀረበች አንዲት የአዲስ አበባ ልጅ ብትገኝ፣ አንስተው ትራንስፖርት ቦታ መደቧት። ጥሩ ብትሮጥም አንደኛ አትወጣም ማለት ይህ ነው» ብሏል።  «መቼም ከሌቦቹ ሳይሻሉ አይቀርም» ያለው ደግሞ ፍጹም ኦስማን ነው «27 አመት ሙሉ በወንድ ተብዬዎቹ ሀገሪቷ ትርምስምሷ ወጣ። ቢያንስ ሴት ለልጆቿ እዝነት ስላላት እንደ ቤቷ ትሰራለች ብዬ አስባለሁ» ብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ