1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የአማራ መስተዳድር ሠላምና ፀጥታ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2011

ብዙ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች «ጥቂት» እያሉ የሚያሳንሷቸዉ የቀድሞ ባለሥልጣናት ይሕን ያሕል ጊዜ-ከደቡብ ሞያሌ እስከ ሰሜን ቅማንት፤ ከምዕራብ በኒ ሻንጉል እስከ ምሥራቅ ሶማሌ የሚገኘዉን ሕዝብ ማጋደል፤ ማጋጨት መቻላቸዉ አንዳነጋገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3B081
Äthiopien Brigadegeneral Asamnew Tsige
ምስል DW/A. Mekonnen

MMT Äth.Sicherheit-Interview mit General Asaminew - MP3-Stereo

በአማራ መስተዳድር እና መስተዳድሩን ከተለያዩ መስተዳድሮች ጋር በሚያዋስኑ ድንበሮች ባለፉት ተከታታይ ወራት የሚካሔደዉ ደም አፋሳሽ ግጭት ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን  የመስተዳድሩ የሠላም እና ደሕንነት ኃላፊ አስታወቁ።የአማራ መስተዳድር የሠላም እና ደሕንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጌድየር ጄኔራል አሳምነዉ ፅጌ ትናንት ለDW እንደነገሩት ግጭት እና ሁከቱ ቀንሷል።ይሁንና ግጭቱን የሚመሩ እና የሚያቀነባብሩት ኃይላት ለረጅም ጊዜ የተዘጋጁበት ሥለሆነ አንዱ አካባቢ የተከሰተዉ ሁከት ሲከስም ሌላጋ ሌላ ግጭት ይጭራሉ።ጄኔራሉ አክለዉ እንዳሉት የግጭት አራማጆቹ ሴራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋለጠ እና እየከሸፈ በመሆኑ ግጭቱ እስካሁን በነበረበት ደረጃ አይቀጥልም።ነጋሽ መሐመድ ጄኔራል አሳምነዉን አነጋግሯቸዋል።

ጄኔራል አሳምነዉ እንደሚሉት ብዙ ሥፍራ ብዙ ሕይወት፣ሐብት ንብረት ያጠፋዉ፣ ብዙ ሰዉ ያፈናቀለዉ ግጭት-ሁከት አሁን ቀዝቀዝ ብሏል።ግን አልቆመም።የወልቃይት ጠገዴ የአስተዳደር ጥያቄ-ደም ማፋሰስ ከጀመረ ቆይቷል።ዛሬም ሞቅ-ቀዝቀዝ እንዳለ ነዉ።ራያም እንደ ወልቃይት ጠገዴ-በግጭት እየጋለች-በደም ትቀዘቅዛለች።የቅማንት-አማራ ጎሳ ለተባለዉ ጠብም ምዕራብ ጎንደር ሕይወት እየገበረች ነዉ።
የመሐል አማራ፣ የአማራ-ሱዳን፣ የአማራ-ትግራይ፣የአማራ-በኒ ሻንጉል ድንበር ሁከት ሰሞኑን ቀዝቀዝ ሲል ለወራት ጋብ ብሎ የነበረዉ የአማራ-አፋር ድንበር ግጭት አገርሽቷል።
የአማራንም ሆነ የሌሎች አካባቢዎችን ለሚያብጠዉ ግጭት፣ ጄኔራል አሳምነዉ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
                                    
ጄኔራል አሳምነዉ እንደሚሉት ግጭቱን በየአካባቢዉ የሚለኩሱት ኃይላት የትግራይ ሕዝብንም አግተዉታል። «ሆስቴጅ» አድርገዉታል።ብዙ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች «ጥቂት» እያሉ የሚያሳንሷቸዉ የቀድሞ ባለሥልጣናት ይሕን ያሕል ጊዜ-ከደቡብ ሞያሌ እስከ ሰሜን ቅማንት፤ ከምዕራብ በኒ ሻንጉል እስከ ምሥራቅ ሶማሌ የሚገኘዉን ሕዝብ ማጋደል፤ ማጋጨት መቻላቸዉ አንዳነጋገረ ነዉ።27 ዓመት የተገዛላቸዉን ሕዝብ ማጋደላቸዉ-በተለይ ለሕዝብ ደሕንነት ተቆርቋሪዎች አሳዛኝ ነዉ።የዚያኑ ያክል የፌደራል ይሁን የክልል መንግስታት ግጭት ቆስቋሽ እያሉ በሚያዋግዟቸዉ ኃይላት ላይ  እርምጃ ለመዉሰድ ያቅማሙበት፣ አጥፊዎችን ያሚያስታምሙበት፣ ተጨማሪ ሕይወት እንዲጠፋ የዘገዩበት ምክንያትም ግራ አጋቢ።ጄኔራል አሳምነዉ «ዘግይቷል» የሚለዉን በግል ይጋራሉ።
                                
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግም በወንጀል የሚጠረጠሩ የቀድሞ ባለስልጣናትን ለመያዝ በተለይ ከትግራይ መስተዳድር ትብብር ማጣቱን በቅርቡ ለሐገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታዉቋል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ