1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ሕዝብ ተቃዉሞ

ሰኞ፣ ጥር 6 2011

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን የፖለቲካ አመራር ለዉጥ ካልተደረገ መፍትሔ የለም ባይ ናቸዉ። የፖለቲካ ተንታኞችም የ29ኝ ዓመቱ የአልበሽር አስተዳደር የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አልቻልም ይላሉ።የምጣኔ ሐብት አዋቂ አል ተግኒ አል ጠይብ እንደሚሉት ደግሞ መንግስት «ካንሰርን በአስፒሪን» ለማዳን እየሞከረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3BXEi
Jemen. Sanaa: Sudanesische Demonstranten protestieren gegen Präsidenten Omar al-Bashir
ምስል Reuters/K. Abdullah

የቀጠለው የሱዳን ተቃውሞ

የኮሎኔል መንግሥቱ «ጎማ የማስተፈስ» ዕቅድ-ዛቻ፣ የቃዛፊ ግልምጫ፤ የዴቢ ቁንጥጫ፤ የሙሳ ቬኒ ጡጫ የጋራንግን ደካማ ክንድ አፈርጥሞ የካርቱሙን «ዋርካ» መወዝወዙ አልቀረም።የአዲስ አበባና የትሪፖሊ ዛች ገላማጮች ተሽንቀነጠሩ እንጂ ደፋሩ ጄኔራል አልተደፈሩም።ወዳጆቻቸዉ ጠላት ሆነዉ ኢሳያስ በጦር፤ መለስ በዲፕሎማሲ ሴራ ቀጥቅጠዋቸዋል። ቀጥቃጮቹ እርስ በርስ ሲቀጣቀጡ ሰዉዬዉ «እጄ ጣላችሁ» ዓይነት ሳይነከተከቱ አልቀረም።ዑመር ሐሰን አሕመድ አልበሽር።የክሊንተን የሚሳዬል በትር፤የምጣኔ ሐብት ዕቀባ፤የቡሽ የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ ወጥመድ፤ የፍርድ ቤት ዋራንት ዳርፉር ላይ ጥፍራቸዉን፤ ጁባ ላይ ጥርሳቸዉን መሸራረፉ ሐቅ ነዉ።የካርቱም መንበራቸዉን ግን አልነቀነቀዉም።29ኝ ዓመት።ዘንድሮ ሕዝባቸዉ ተነሳባቸዉ።አልበሽር።አቡድን፣ኑሜሪን፣ወይስ ማንን ይሆኑ ይሆን? ላፍታ እንጠይቅ።

 የአፍሪቃ-አሜሪካ፣ የአይሁድ-አረብ-አዉሮጳ ጠላት-ባላንጦቻቸዉን ግፊት፣ ጫናና ሴራ ኖረዉበታል።ሰበብ ምክንያቱንም ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።ደግሞ በተቃራኒዉ ሲያዳልጥ-ሲያሟልጣቸዉም ሕዝባቸዉን ከጀርባቸዉ ለማስከል ተጠቅመዉበታል።ባለፈዉ ሳምንትም ደገሙት።«ሱዳንን ዒላማ ማድረግ ስንል ለየትኛዉም አቋም፣ችግር ወይም እጥረት ፍትሐዊ ማረጋጋጪያ መስጠታችን አይደለም።እዉነት ነዉ።የሰይጣን ዛቢያ ብለዉናል።ያልተገራ መንግስት ተብለናል።መጥፋት አለባቸዉ ከተባሉ መንግስታት ዝርዝር ዉስጥ ነበርን።ሴራ ነዉ።አሁንም ቀጥሏል።ለ21 ዓመት ማዕቀብ ተጥሎብን ነበር።አሸባሪነትን የሚያራምዱ ከሚባሉ መንግስታት መሐል ነበርን።ሱዳን እና ሕዝቧ ያልተወነጀሉበት አንድም አጋጣሚ አልነበረም።»

Sudan Rede von Präsident Omar al-Bashir
ምስል Getty Images/AFP/A. Shazly

ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አል በሽር።በርግጥም የአል በሽር መንግስት ለኦስማ ቢል ላደን ከለላ በመስጠቱ ሰበብ የሱዳን የመድሐኒት ፋብሪካ በአሜሪካ ክሩዝ ሚሳዬል ጋይቷል።ነሐሴ 1998 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)።የያኔዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ቢን ክሊንተን ያኔ እንዳሉት ጦራቸዉ መድሐኒት ፋብሪካዉን ያወደመዉ የመርዛማ ነጥረ ነገር ኬሚካል ማምረቻ ነዉ-ብሎ ነዉ።«ዛሬ ጦር ኃይላችን፣ አፍቃኒስታንና ሱዳን ዉስጥ የሚገኙ ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸዉን ተቋማት እንዲመታ አዝዣለሁ።ሱዳን የሚገኘዉን የአሸባሪዎች የኬሚካል ማምረቻን መትተናል።ዒላማችን የአሸባሪዎች የዘመቻ ሠፈርና ተቋም ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስ ከዓመት በኋላ በሱዳን ላይ አጠቃላይ የምጣኔ ሐብት ማዕቀብ ጥላለችም።የምዕራብ ዳርፉር ጦርነት በጋመበት በ2007 ደግሞ የያኔዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ  መንግስት በሱዳን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥሏል።ሌላ እርምጃ ለመዉሰድ ዝተዋልም።

«ስለዚሕ ባለፈዉ ሚያዚያ ባስታወቅሁት መሠረት መስተዳድሬ ዛሬ እርምጃዎችን ለመዉሰድ ወስኗል።መጀመሪያ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት በሱዳን ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ያጠናክራል።በዚሕ መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን መግሥት ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ይበልጥ ገቢራዊ ለማድረግ ጠንካራ እርምጃዎችን ትወስዳለች።»

ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥታ ድብደባ፤ ማዕቀብ፣ ዲፕሎማሲዉ ጫና በተጨማሪ ከሱዳን ጎረቤቶች እስከ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍርድ ቤት፤ ከአሜሪካ የፊልም ተዋኞች እስከ ዓለም የመብት ተሟጋቾች በሱዳን ላይ የተደረገዉ ግፊትና ጫና ፕሬዝደንት አል በሽርን በጦር ወንጀለኝነት እስከ ማስክሰስ የደረሰ ጠንካራ ተፅዕኖ አሳድሯል።

አልበሽር፣ ደቡብ ሱዳኖች ነፃ መንግስት እንዲያዉጁ የተስማሙትም የኃሉም፣የደካማዉም ጠላቶቻቸዉ   ግፊት እና ጫናዉ በማየሉ ነበር።አልበሽር  የደቡቦችን የመገንጠል ዉጊያ፣ የዳርፉሮችን አመፅ፣ የምሁራንን ተቃዉሞ ለመደፍለቅ የዉጪ ኃይላት ጫና፣ ግፊት እና ሴራን በምክንያትነት እንደተጠቀሙበት ሁሉ ለዳቦዉም-ለፉሉም፣ለመድሐኒቱም-ለነዳጁም-መወደድ የዉጪ ኃይላት ሻጥር ዉጤት ማለታቸዉ ነዉ ያሁኑ ግራ አጋቢ እዉነት።

ደቡብ ሱዳን ስትገነጠል አዲሶቹ የጁባ ገዢዎች ከሱዳን የነዳጅ ዘይት ገቢ ሰወስት አራተኛዉን ይዘዉ ነዉ የሄዱት።ሱዳን ከ2000 ጀምሮ በቀን ከ400 ሺሕ በላይ በርሚል ነዳጅ ዘይት ትሸጥ ነበር።ደቡብ ሱዳን ከተገነጠለች በኋላ ግን ሱዳን ለዉጪ ገበያ የምታቀርበዉ በቀን 140 ሺሕ በርሚል ነዉ።

የረጅም ጊዜ ጦርነት፣ መገለልና የአሜሪካኖች ማዕቀብ የገዘገዘዉ ምጣኔ ሐብት፣ የደጅ ዘይቱ ገቢ ሲቀርበት ተሽመድምዶ ወደቀ።ምጣኔ ሐብታዊዉ ዉድቀቱት ኑሮዉን ያናጋበት ሕዝብ በተለይም ወጣቱ በ2011 የፕሬዝደንት አልበሽርን መንግስት ባደባባይ መቃወም ጀምሮ ነበር።አልበሽር በለመዱት ኃይልን ከጥገናዊ ለዉጥ በቀየጠ ስልታቸዉ ተቃዉሞዉን ደፈለቁት።ባለፈዉ ታሕሳስ እንደገና አገረሸ።

Jemen. Sanaa: Sudanesische Demonstranten protestieren gegen Präsidenten Omar al-Bashir
ምስል Reuters/K. Abdullah

የሱዳን ወጣቶች ለአደባባይ ተቃዉሞ፣ አደባባዮቿ ለተቃዉሞ ምናልባት ለድጋፍ ሰልፍ እንግዳ አይደሉም።ጥር 23 2011 የኡዱሩማኑ ወጣት አል-አሚን ሙሳ አል አሚን እራሱን በእሳት ሲያጋይ፣ ቱኒዚያዊዉ ወጣት መሐመድ ቡአዚዝ ከወር በፊት የከፈለዉ መስዋዕትነት አስተምሕሮ ተብሎ፣ ብዙ ሱዳናዊ ወጣቶችን እንደ ቱኒዞች ላደባባይ ተቃዉሞ አሳድሞ ነበር።

ራቢ ሐሰን አሕመድ ግን ሱዳኖች ተቃዉሞ አመፅን ከቱኒዚያ ተማሩ መባሉን አይቀበሉትም።«አዎ ብዙ ያሳስበኛል» አሉ አሕመድ።ሰባ አንድ ዓመታቸዉ ነዉ።«በጨቋኝ ገዢዎች ላይ ማመፅን የሱዳን ወጣቶች ለሌሎች አስተማሪ እንጂ ከሌሎች አልተማሩም ባይ ናቸዉ።» የዛሬዉ አዛዉንት።በ1960ዎቹ የካርቱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፕሬዝደንት ነበሩ።

የመጀመሪያዉ የሱዳን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይባል የነበረዉን አስተዳደር በ1958 በፈንቅለ መንግስት አስወግደዉ ሥልጣን የያዙት የጄኔራል ኢብራሒም አቡድ አገዛዝ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉ ጭቆና በ1960ዎቹ አብዛኛዉን ሱዳናዊ አንገሽግሾት ነበር።የሕዝቡን ምሬት የተረዱት ራቢ ሐሰን አሕመድና ባልጀሮቻቸዉ የዩኒቨርስቲያቸዉን ተማሪዎች ላባደባባይ የተቃዉሞ አሰለፉት።

የጄኔራል አቡድ መንግስት ተቃዉሞዉን ለመደፍለቅ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የተማሪ መሪዎችን አሰረ፣ የተወሰኑትን ገደሉ።ግን አልቻለም ተሸነፈ።ጄኔራሉ ሥልጣን ለመልቀቅ ተገደዱ።ሱዳን እንደገና «ዴሞክራሲያዊ» የተባለ የሲቢል አስተዳደር መሠረተች።ከአራት ዓመት በላይ አልዘለቀም።

ሌላ መፈንቅለ መንግስት።ኮሎኔል ጀዓፈር መሐመድ አኑሜሪ ሥልጣን ያዙ።1969።የኑሜሪ ወታደራዊ አገዛዝ የሱዳን ሕዝብን በተለይም የወጣቶቹን የዴሞክራሲ ጥያቄና ተስፋ ሲያጨናጉለዉ የዛሬዉ ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አሕመድ አልበሽር ካይሮ-ግብፅ ጦር ሠራዊት ኮሌጅ ሆነዉ ይታዘቡ ነበር።

ኑሜሪ በተደጋጋሚ የተቃጣባቸዉን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አክሽፈዋል።ተቃዋሚዎቻቸዉን በተለይም ኮሚንስታዊ አስተሳሰብ የነበራቸዉን ፖለቲከኞች ገድለዋል፣ አስረዋል፣ አሰድደዋልም።በ1980ዎቹ አጋማሽ የተቀሰቀሰባቸዉን ሕዝባዊ ቁጣ መቋቋም ግን አልቻሉም።1985። ኑሜሪ ተሰናበቱ።

በ1973 አረቦች በተለይም ግብፅ ከእስራኤል ጋር ባደረገችዉ ጦርነት የተዋጉት ዑመር ሐሰን አልበሽር የኑሜሪ አገዛዝ ከስልጣን ሲወገድ እንደ ጥሩ የጦር አዛዥ የደቡብ ሱዳን ተገንጣዮችን የሚወጋዉ ጦር አዛዥ ነበሩ።ብርጌድየር ጄኔራል።ኑሜሪ በህዝባዊ አመፅ ከስልጣን በተወገዱ በአራተኛዉ ዓመት ደግሞ የ1969ኙን ኑሜሪ ሆኑ።

Sudan Khartum Demonstrant im Tränengas
ምስል picture-alliance/AP Photo/Sudanese Activist

የሳዲቅ አል መሕዲን የሲቢል መንግሥት በደም አልባ መፈንቅለ መንግሥት አስወግደዉ የሰፊ፣ደሐይቱን ግን የየዋሕ፣ ደጎቹን ሐገር የመሪነት ሥልጣን ተቆጣጠሩ።በ1985ቱ የተቃዉሞ ሰልፍ የተካፈሉት ኢስማኢል ሐሰን ኻሊል እንደሚሉት ሕዝብ ያመፀበት አገዛዝ ጊዜ ይገዛ ይሆናል እንጂ መፍረሱ አይቀርም።

አልበሽር በ2011 የተነሳባቸዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ አክሽፈዉ እስካሁን መንበረ ሥልጣናቸዉን ማስከበር ችለዋል።ጊዜ ገዙ።ታሕሳስ  ላይ ዳግም የተቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ አመፅ ለመክሸፍም የሱዳን ፀጥታ አስከባሪዎች በትንሽ ግምት 25 ሰዉ ገድለዋል።ብዙ አስረዋል።የዳቦ ዋጋ በመጨመሩ ሰበብ ምጣኔ ኃብታዊ ጥያቄ አንግቦ የተነሳዉ ሕዝብ ግን ጥያቄዉን ወደ ፖለቲካ ቀይሮ አልበሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ መጠየቁን አላቋረጠም።

የአልበሽር መንግሥት የምግብ ዋጋ ንረትን  ለማሻሻል እና ግሽበትን ለመቆጣጠር ቃል ገብቷል።የማስታወቂያ ሚንስትር ዴኤታ ማዕሙን ሐሰን ትናንት እንዳሉት ደግሞ መንግስታቸዉ ችግሮቹን ለማስወገድ «ተገቢ» ያሉትን እርምጃ ይወስዳል።«መንግሥት ችግሮቹ መኖራቸዉን ይቀበላል።ሥለ ችግሮቹ እናዉቃለን።በተለያዩ የምጣኔ ሐብት መርሕ አማካይነት መፍትሔ መስጠት ጀምረናል።ከነዚሕ ዋና ዋና መርሆች አንዱ ምጣኔ ሐብቱን ማረጋጋት ነዉ።ምጣኔ ሐብቱን ለማረጋጋት ደግሞ ወጪን መቀነስ አንዱ እርምጃ ነዉ።»

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን የፖለቲካ አመራር ለዉጥ ካልተደረገ መፍትሔ የለም ባይ ናቸዉ።የፖለቲካ ተንታኞችም የ29ኝ ዓመቱ የአልበሽር አስተዳደር የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ አልቻልም ይላሉ።የምጣኔ ሐብት አዋቂ አል ተግኒ አል ጠይብ እንደሚሉት ደግሞ መንግስት «ካንሰርን በአስፒሪን» ለማዳን እየሞከረ ነዉ።

«መንግስት አሁንም ችግሩ የምንዛሪ ችግር እንደሆነ አድርጎ ይመለከታል።ማለትም በሕጋዊዉ እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለ የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ይመስለዋል።ችግሩ ግን አጠቃላይ የምጣኔ ሐብት አለመመጣጠን በመኖሩ የተከሰተ ነዉ።መንግስት መሠረታዊዉን ያለመመጣጠን ችግር ማስወገድ ካልቻለ አሁን የሚወስደዉ (እርምጃ) ካንሰርን በአስፒሪን ለማከም እንደመሞከር የሚቆጠር ነዉ።»ተቃዉሞ ሰልፈኛዉም የምንሻዉ የሥርዓት «ለዉጥ ብቻ» እያለ ነዉ።የአልበሽር 29ኝ ዓመት ደማቅ ጀምበር ወደ ምዕራብ ትጣደፋለች።የብዙዎች ጥያቄ ትጠልቅ ይሆን-ሳይሆን «መቼ ነዉ» የሚል ነዉ።  

Unruhen im Sudan - Proteste in Khartum
ምስል Reuters/M.N. Abdallah

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋዓለም