1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኖቤል የሰላም ሽልማትን ማን ሊያሸንፍ ይችላል?

ሐሙስ፣ መስከረም 24 2011

ለዓመቱ የኖቤል የሰላም ሽልማት 331 እጩዎች ቀርበዋል። ሽልማቱን የሚሰጠው ኮሚቴ እንዳለው ከሆነ 216 ግለሰቦች ሲሆኑ 115 ቡድኖች ናቸው። የዕጩዎቹ ማንነት በምሥጢር ቢያዝም ሰዎች የየራሳቸውን ግምት ከመናገር ያገዳቸው የለም? አብይ እና ኢሳያስ ሊያሸንፉ ይችላሉ? 

https://p.dw.com/p/35ycF
Saudi Arabien Äthiopien und Eritrea schließen Freundschaftsvertrag
ምስል picture-alliance/AP Photo/SPA

በነገው ዕለት የዓመቱ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ማንነት በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ይፋ ይደረጋል። የዕጩዎች ማንነት እስካሁን በይፋ ባይታወቅም በዓመቱ ለዓለም ሰላም የጎላ አስተዋፅዖ ያበረከቱ እና አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ሰዎች አልጠፉም።

ማን ሊያሸንፍ ይችላል?


ኪም ጆንግ ዑን እና ሙን ጄይ ኢን

በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. ሰሜን ኮሪያ ባደረገቻቸው የኑክሌር እና አኅጉር ተሻጋሪ ተወንጫፊ ሚሳይል ሙከራዎች የሁለቱ ኮሪያዎች ግንኙነት በከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ከዓመት በኋላ ኪም ጆንግ ዑን እና ሙን ጄይ ኢን በፈገግታ ታጅበው በመተቃቀፍ የጀመሩት ግንኙነት የኑክሌር ጦር መሳሪያን ለማስወገድ ወደሚያስችል እርምጃ እንደመራቸው ዓለም አቀፍ ተንታኞች ዕምነት አድሮባቸዋል። ሁለቱ መሪዎች ሽልማቱን ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሎ ተስፋ ቢጣልባቸውም የሰሜን ኮሪያው መሪ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ይፈፅማል እየተባለ የሚወቀስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግን ዕድላቸውን ጠባብ ሊያደርጉት ይችላል። የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያዘጋጀውን ግምገማ መመልከቱ አይቀርም። በርካቶች ግን ሁለቱ መሪዎች ሽልማቱን የማሸነፍ ዕድል አላቸው የሚል ግምት አላቸው። 

Nobelpreis - Medaille für Literatur, Physik, Chemie und Medizin


ራይፍ ባዳዊ 

"የእስልምና እምነትን አንቋሿል" የሚል ክስ የቀረበበት የድረ-ገጽ ጸሐፊ ራይፍ ባዳዊ በአገሩ ሳዑዲ አረቢያ ከታሰረ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ። ጸሐፊው ሰባት ዓመታት እንዲታሰር 1,000 ጊዜ በጅራፍ እንዲገረፍም ተፈርዶበታል። ራይፍ ቢያሸንፍ እንኳ በእስር ላይ ሳለ የኖቤል የሰላም ሽልማት የተበረከተለት የመጀመሪያው የፖለቲካ እስረኛ አይሆንም። ቻይናዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሊዩ ዢያቦ ይኸንንው ሽልማት ሲያሸንፍ እስር ቤት ነበር።

 
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት

ጦርነት እና በመንግሥቶቻቸው የሚፈጸምባቸውን የመብት ጥሰት የሚሸሹ ስደተኞችን በመርዳት ረገድ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ቀዳሚ ሚና ይጫወታል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ይኸንንው ሽልማት አሸንፏል።

የካታላን ፕሬዝዳንት የነበሩት እና በስደት ቤልጅየም የሚኖሩት ካርሎስ ፑጅሞን፣ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቃነ-ጳጳስ ፍራንሲስ ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚል ቅድመ-ግምት ከተሰጣቸው መካከል ይገኙበታል።


ኢሳያስ እና አብይ

በርካታ የጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ደጋፊዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የኖቤል የሰላም ሽልማት ይገባቸዋል የሚሉ መልዕክቶችን ሲያንሸራሽሩ ከርመዋል። ሽልማቱን እንዲያሸንፉ ድምፅ ይስጡ የሚሉ ሐሰተኛ መረጃዎች ይሰራጩም ነበር። ለሽልማቱ ብቁ የሆኑ እጩዎች የመለየት እና የመምረጥ ሥልጣን ያለው ግን የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው በኖርዌይ ፓርላማ የተሾሙ አምስት አባላት አሉት። 
ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የፖለቲካ ልሒቃን ቁርሾ መቋጫ ያበጁት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ይኸው ሽልማት ይገባቸዋል የሚሉ ግን አልጠፉም።
ሁለቱ መሪዎች በተደጋጋሚ ተገናኝተው ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች የሕዝብ ለሕዝብ እና የንግድ ግንኙነት መነቃቃት ጀምሯል። መሪዎቹ በአገራቱ መካከል ሰፍኖ የቆየው የጦርነት ሁኔታ አብቅቶ አዲስ የሰላም ምዕራፍ መከፈቱን አብስረዋል። ከአንዴም ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ግንኙነት መጀመሩን ያበሰሩባቸውን ሰነዶች ፈርመዋል። ሁለተኛው ሰነድ በሳዑዲ አረቢያዋ ጅዳ ሲፈረም የተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ እና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ተገኝተው ነበር። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች ዕርቅ ለማውረድ ግንኙነት መጀመራቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ተቋማት፤ በፖለቲከኞች እና አገራት ዘንድ ሙገሳን አግኝቷል።

African Roots Nelson Mandela
ምስል Comic Republic

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተሳክቶላቸው ከተመረጡ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያሸነፉ አፍሪቃውያንን ቁጥር ወደ 12 ከፍ ይላል። 
የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት «ANC»ፕሬዝዳንት የነበሩት አልበርት ሉቱሊ በጎርጎሮሳዊው 1960 ዓ.ም. ሽልማቱን በመቀዳጀት የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ነበሩ። የግብጹ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት፣ ደቡብ አፍሪቃውያኑ ዴዝሞንድ ቱቱ፣ ኔልሰን ማንዴላ እና ፍሬድሪክ ዊሌም ደ ክለርክ ከአሸናፊዎቹ መካከል ይገኙበታል። 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ