1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲካ ታዛቢዎች የኢህአዴግን መግለጫ ተችተዋል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 12 2010

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ስብሰባ እየካሄደ ይገኛል፡፡ ግንባሩ ስብሰባውን አስመልክቶ ትላንት ያወጣውን መግለጫ የተመለከቱ የፖለቲካ ታዛቢዎች «የተሸፋፈነ» እና «አዲስ ነገር የሌለው» ሲሉ ይተቻሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2pmtv
Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Reuters/Tiksa Negeri

የፖለቲካ ታዛቢዎች መግለጫውን ተችተዋል

በኢህአዴግ አደረጃጀት ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ ከፍተኛ የመወሰን ስልጣን ያለው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ 2010 ዓ.ም ከባተ ወዲህ በተደጋጋሚ ስብሰባ ተቀምጧል፡፡ መደበኛዎቹም ሆኑ አስቸኳዮቹ የኮሚቴዉ ስብሰባዎች በተለምዶ በሁለት ሦስት ቀናት የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ረዘም ያለ ጊዜ ፈጅቶ ከተቋጨዉ የህወሓት ስብሰባ በኋላ የተጠራው የአሁኑ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ግን ዛሬን ጨምሮ አስር ቀናትን ወስዷል፡፡

ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚወከሉ 36 የሥራ አስፈጻሚ አባላት ይሳተፉበት የነበረው ስብሰባ ነባር የኢህአዴግ ታጋዮችን ጨምሮ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡ ከአምባሳደር ስዩም መስፍን እስከ አቶ አባይ ጸሐዬ፣ ከአቶ አባዱላ ገመዳ እስከ አቶ አዲሱ ለገሠ፣ ከአቶ ግርማ ብሩ እስከ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ ያሉ የቀድሞ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በስብሰባው ላይ ታድመዋል፡፡ ስብሰባው በኢትዮጵያ ባለው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ ትኩረትን መሳቡን የተረዳ የሚመስለው ኢህአዴግ  ሂደቱን የተመለከተ መግለጫ ትላንት ማምሻውን አውጥቷል፡፡ 

ኢህአዴግ ያወጀውን «በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ እየገመገመ» እንደሚገኝ የጠቀሰው መግለጫው «ተሃድሶው በሚፈለገው ደረጃ  ጥልቀት ያልነበረው በመሆኑ» ወደ አዘቅቱ መመለስ መጀመሩን ጠቅሷል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኢትዮጵያ «ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በፈጠረው ተስፋ እና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች በደቀኑት ስጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባች በትክክል ይገነዘባል»  በማለት መግለጫው ያትታል፡፡ በሀገሪቱ «የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የኢህአዴግ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው እንደሆኑ በሚገባ ይገነዘባል» ሲልም አክሏል፡፡ ስብሰባው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ለችግሮች «የማያዳግምና መሰረታዊ መፍትሄ የሚሰጡ ይሆናሉ» በማለት ቃልም ይገባል፡፡ 

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በብሪታንያ የኪል ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር አቶ አወል አሎ መግለጫው ከዚህ ቀደም ከነበሩት «የተለየ አይደለም» ይላሉ፡፡ መንግሥት ራሱ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንዳለ በግልጽ ማመኑን የሚያነሱት አቶ አወል መግለጫው «ሀገሪቷ ውስጥ እየሆነ ያለውንም ሆነ በፓርቲዎቹ ውስጥ ያለውን ሽኩቻ እውነተኛ በሆነ መልኩ ለህዝብ ያሳወቀ አይደለም» ሲሉ ይተቻሉ፡፡ በመግለጫው የተጠቀሰው «በቂ አይደለም» የሚሉት አቶ አወል «ህዝቡ ከዚያ የተሻለ ነገር መስማት ይፈልጋል» ባይ ናቸዉ፡፡  

ኢህአዴግን እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ አብርሃ ኃይለእዝጊም የገዢው ፓርቲ መግለጫ «የተሸፋፈነ ነው» በሚለው ይስማማሉ፡፡ መግለጫው «ዝርዝር የሌለው፣ አመላካች ያልሆነ እና አዲስ ነገር የሌለው» ሲሉ ይነቅፉታል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈጠሩትን ችግሮች መንስኤ እና ተጠያቂዎቹን በግልጽ የሚያሳውቅ መግለጫ ጠብቀው እንደነበርም ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡  

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚያካሂደዉ ስብሰባ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ በመግለጫዉ ተጠቁሟል። በስብሰባዉ ማብቂያም «ሕዝቡ ላነሳዉ ጥያቄ የተሟላ መልስ ለመስጠት እና የፌደራል ሥርዓቱን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እና አስፈላጊ እርምጃዎችም» እንደሚወስድ አመልክቷል።  

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ