1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብዙኃን አምባገነንነት ስጋት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5 2011

«አሁን የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ሒደት በአሉታዊ መልኩ የሚቀለበስ ከሆነ መልሶ ለማቃናት ከ1997 ወዲህ ከተደረገው ትግል የበለጠ ኃይል የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ደግሞ ለውጡን እየመራው ያለው ቡድን የተሻለ ተቀባይነት ያለው በሕዝብ ብዛታቸው ትልቅ በሆኑት ሁለት እና ሦስት ክልሎች ውስጥ ነው» በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

https://p.dw.com/p/3A63y
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የተዋቀረው በፌዴራል ስርዓት ቢሆንም፥ የፌዴራሉ አባል መንግሥታት ያልተመጣጠነ ጡንቻ ነው ያላቸው። በተለይም ሁለቱ ክልሎች - ኦሮምያ እና አማራ - ተደምረው ከግማሽ በላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን መቀመጫ መቆጣጠር የሚችሉ መሆኑ እና ቀሪዎቹ ሰባት ክልሎች ቢተባበሩ እንኳ የሁለቱን ያክል ድምፅ የሌላቸው መሆኑ፣ በክልል መንግሥታት መካከል ያልተመጣጠነ የኃይል ሚዛን የሚፈጠርበትን ዕድል አስፍቶታል። ከዚህ ቀደም የሕወሓት የበላይነት ከነፍጥ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ በስርዓቱ ውስጥ መስፈኑ ስጋቱን ሸፍኖት ቢቆይም፥ በአሁኑ ወቅት እየተካሔደ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ሒደት የስጋቱን ፍንጭ እየሰጠ ይመስላል።

የቡድን ወይስ የስርዓት ለውጥ?

የለውጥ ሒደቱን ከአንድ ቡድን አገዛዝ ወደ ሌላ ቡድን አገዛዝ የተሸጋገረ ነው በማለት ምንም ልዩነት እንዳላመጣ የሚናገሩ አሉ። በርግጥ የፖለቲካ እስረኞቹ ፍቺ፣ የአፋኝ አዋጆቹ ክለሳ፣ የብዙኃን መገናኛዎቹ እቀባ መነሳት እና ሌሎችም ለውጡ የእውነት ነው ለሚለው መከራከሪያ የተሻለ ሚዛን ይሰጡታል፡፡ ይሁን እንጂ ያለፉት ወራት በጣም ብዙ ኹነት የበዛባቸው እና ነገሮች በፍጥነት የተለዋወጡባቸው በመሆኑ ሒደቱን በመገምገም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት እየሔደ ነው የሚለውን በቅጡ መመለስ አልተቻለም፡፡ ነገር ግን በሙስና እና በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠርጠረው የታሰሩት ሰዎች ጉዳይ እና የፍርድ ሒደቱ፥ ጉዳዩ ገና ከጅምሩ ንቁ ክትትል እንደሚያስፈልገው ያሳሰበ ሆኗል።

በእስር ዘመቻዎቹ ወቅት ከተስተዋሉት ቅሬታዎች ውስጥ አንዱ ‘እስሩ በቀደሙት ዓመታት በእነዚህ ወንጀሎች ይታሙ የነበሩ የገዢው ፓርቲ አባላትን ሁሉንም አለማካተተም፤ የለውጡን ባቡር ተሳፍረዋል በሚል ብቻ የቀድሞ አጋሮቻቸው ሲታሰሩ የቀሩ የወንጀሎቹ ፈፃሚዎች ወይም ተባባሪዎች አሉ’ የሚለው ነው። ይህንኑ መከራከሪያ በመጥቀስ የታሰሩት እና ለእስር እየታደኑ ያሉት፥ ምንም እንኳን የተጠረጠሩበት ወንጀል ፈፅመው ሊሆን ቢችልም እስራቸው ግን ሁሉንም ባለማካተቱ የፖለቲካ ነው። የፖለቲካ ለውጡን ተቀብለናል ብለው ቢያውጁ ኖሮ አይታሰሩም ነበር ብለው የሚከራከሩ አሉ። በተለይም ደግሞ ያለፈውን በደል እና ቅሬታ በይቅርታ አልፈነዋል ተብሎ ከታወጀ በኋላ፥ የእስር ዘመቻ መጀመሩ ‘እስሩ እውን የፖለቲካ ልዩነት ያመጡትን ማግለያ ነውን?’ የሚለውን ብዥታ አባብሶታል። ከዚህም በላይ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩት እና በገዢው ፓርቲ ወገንተኝነታቸው የሚታወቁት መገናኛ ብዙኃን ተጠርጣሪዎቹ ፈፅመዋቸዋል በተባሏቸው ወንጀሎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አንድ ዓይነት የዘገባ ፊልም በተመሳሳይ ሰዓት ማቅረባቸው መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት በስርዓቱ ውስጥ አሁንም እንደቀጠለ ማሳያ ሆኗል። እነዚህ እና መሰል ዝርዝር ሁነቶች ለውጡ የስርዓት ሳይሆን የቡድን ሊሆን ይችላል የሚለውን እያጠናከሩ ነው።

ነገር ግን በአንድ በኩል የተገኙት ተስፋ ሰጪ ድሎች የፈጠሩት የፈንጠዝያ ስሜት፣ በሌላ በኩል ለለውጥ ተነስቻለሁ የሚለውን ቡድን ከማመን ወይም ደግሞ ምናልባት ለውጡ ጥቂቶች ብቻ ከሚደግፉት፣ ብዙኃን ወደሚደግፉት በመሸጋገሩ ምክንያት የጥቂቶቹ ቅሬታ ምንም ያህል አልፏል የምንለው ስርዓት ውስጥ የነበረውን ዓይነት በደል ተፈፅሟል የሚል ቢሆንም አድማጭ አላገኘም።

ማለቂያ የሌለው ዙረት?

የደርግ ስርዓት ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲቆጣጠር፥ ከአሁኑ ጋር ተቀራራቢ የተስፋ ስሜት ተፈጥሮ ነበር። ብዙ የፖለቲካ እስረኞች ተፈትተዋል፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቷል፣ በሰብኣዊነት ላይ ወንጀል የፈፀሙ የቀድሞ ባለሥልጣናት ታስረዋል። ይህንንም ተከትሎ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎች አብበዋል። የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ግን ያው የመንግሥትን ገጽታ መገንባት እና ያለፈውን መኮነናቸውን ቀጥለው ነበር። ይሁንና ያንኛው የፖለቲካ እመርታ በ1997 ኢሕአዴግ በተቀናቃኝ ፓርቲዎች ከተፈተነ በኋላ ተቀልብሷል። የፖለቲካ እስረኞች ዳግም እስር ቤቱን ሞልተውታል፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ሲቪል ማኅበራት እና የፖለቲካ ድርጅቶች በሕግም በተግባርም ታፍነዋል።

አሁንም ተመሳሳይ ሒደት ላይ ነን ማለት ይቻላል። የአሁኑ ለውጥ ከ1997 ወዲህ የተቀለበሰውን አንፃራዊ የተሻለ የዴሞክራሲ ጉዞ ለመመለስ ይመስላል። ይሁን እንጂ ገለልተኛ ብዙኃን መገናኛዎች የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳ መገዳደር ሲጀምሩ፣ ሲቪል ማኅበራት በሁለት እግራቸው ሲቆሙ እና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ገዢውን ፓርቲ ሥልጣን ለመቀማት አቅም ሲደርሱ ነገሮች መልሰው ሊቀለበሱ፣ አገሪቱም ማለቂያ የሌለው አዙሪት ውስጥ መልሳ ልትገባ ትችላለች።

አሁን የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ሒደት በአሉታዊ መልኩ የሚቀለበስ ከሆነ፥ መልሶ ለማቃናት ከ1997 ወዲህ ከተደረገው ትግል የበለጠ ኃይል የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ደግሞ ለውጡን እየመራው ያለው ቡድን የተሻለ ተቀባይነት ያለው በሕዝብ ብዛታቸው ትልቅ በሆኑት ሁለት እና ሦስት ክልሎች ውስጥ ነው። ይህም ለብዙኃን አምባገነንነት በር ይከፍታል። ይህንን ስጋት ሥር ሳይሰድ ለመከላከል የፖለቲካ ተዋናዮች በሙሉ በንቃት መጠበቅ ከቻሉ እና ብቸኛው የጫወታው ሕግ ዴሞክራሲ እንዲሆን ማድረግ ከቻሉ ስጋቱ ቀስ በቀስ ጠፍቶ ኢትዮጵያ ከገባችበት ማለቂያ የሌለው ክብ ልፋት ልትወጣ ትችላለች።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።