ተቃዋሚዎች ተጓዦችን አስወርደው አራት አውቶቡሶችን ደብድበዋል
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19 2010የቁልቢ ገብርኤልን አመታዊ በዓል የሚከብሩ ምዕመናን አሳፍረዉ ከአዲስ አበባ ወደ ቁልቢ በመጓዝ ላይ በነበሩ አውቶቡሶች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል ተባለ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሰራተኞቹ ባሰራጨው የጸጥታ ማስጠንቀቂያ ማስታወሻ እንደገለጠው አውቶቡሶቹ በተቃዋሚዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው ጭሮ አቅራቢያ በምትገኘው አርባረከቴ ከተማ አዉራ መንገድ ላይ ነው።
ተቃዋሚዎቹ መንገደኞቹን በማስወረድ አራቱን አውቶቡሶች በድንጋይ መደብደባቸውን እና የአብዛኞቹ መስታወቶች መውደማቸውን ማስታወሻው ገልጧል። በመረጃው መሰረት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ተቃዋሚዎቹ አውቶቡሶቹን በእሳት ከማጋየታቸው በፊት ወታደራዊ ኃይል ደርሶ እንደበተናቸውም አትቷል።
አውቶቡሶቹ በወታደራዊው ኃይል ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል ተብሏል።ሰላም ፤ ስካይ እና ኢትዮ ባስ ከተባሉት ውጪ ሌሎች በነፃነት ይጓዙ እንደነበር ይኸው ማስታወሻ አትቷል። ሶስቱ የሕዝብ ማመላለሻ ኩባንዮች የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት ንብረቶች ናቸው በሚል ለጥቃት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሰራጨው ማስታወሻ የመረጃ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ አትቷል።
ቁልቢ ደርሶ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰዉ ባልደረባችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር እንደሚለዉ ደግሞ አዲስ አበባን ከሐረር እና ድሬዳዋ ጋር የሚያገናኘዉ መንገድ ዛሬም ዉጥረት እና ሥጋት እንደሰፈነበት ነዉ። ነጋሽ መሐመድ ዮሐንስን ዛሬ ከቀትር በኋላ በስልክ አነጋግሮት ነበር።
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ