1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለው የሱዳን ቀውስ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27 2011

የሱዳን ዜጎች ካለፉት ሳምንታት ወዲህ በፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺር አንጻር ተቃውሞ ቀጥለዋል። ፕሬዚደንቱ አንዳንድ የተቃዋሚዎችን ጥያቄዎችን መልሰዋል። ይሁንና፣ተቃውሞው ብዙም ያላስጨነቃቸው ነው የሚመስሉት። ምክንያቱም፣ መንግሥታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ  ዋና ሚና ይዟል ብለው ስለሚያስቡ፣ ከስልጣን ሊወገዱ የሚችሉ አልመስላቸውም።

https://p.dw.com/p/3B3Kq
Sudan Demonstrationen Proteste
ምስል Reuters/M. N. Abdallah

ቀውስ በሱዳን

በሱዳን ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ የቀጠለው ተቃውሞ ደም አፋሳሽ ነበር። ሱዳናውያን ከታህሳስ ወር መጀመሪያ አንስተው ነበር በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች ተቃውሞ  ለማሰማት አደባባይ መውጣት የጀመሩት። የተቃውሟቸው ምክንያት ፕሬዚደንት ሀሰን ኦማር ኤል በሺር የሚመሩት መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ሃገሪቱ የገጠማትን ደካማ የምንዛሪ ተመን እና ከፍተኛውን የዋጋ ግሽበት ለመታገል በሚል በነዳጅ እና በዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ያወጣው እቅድ ነው። በተለያዩ ግዛቶች የተደረገው ተደጋጋሚ ግጭት፣ የዉጪ ማዕቀብ እና ብልሹ አስተዳደር የሃገሪቱን ምጣኔ ሀብት አብዝቶ ጎድቶታል።  የምግብ ሸቀጦች እና የመድሀኒት ዋጋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዉስጥ በሶስት እጥፍ ጨምሯል።
ባለፉት ቀናት እንደታየው ግን፣ የሱዳናውያኑ ተቃውሞ በዋጋው ንረት ላይ ብቻ ተወስኖ የቀረ ሳይሆን፣ ሃገሪቱን ካለፉት ሶስት አሰርተ ዓመታት ወዲህ  በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በመምራት ላይ ባሉት ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺር አንጻርም አነጣጥሯል። አንዳንድ ተቃዋሚዎች በገዢው የብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ የሚገኝበትን ህንጻ በእሳት ሲያጋዩ፣ ሌሎች ደግሞ በሺር ከስልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል። ተቃዋሚዎች ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊው ታህሳስ 19፣ 2018 ዓም እንደገና አደባባይ በወጡበት ጊዜ የፀጥታ ኃይላት በጦር መሳሪያ ርምጃ ወስደው፣ በመንግሥቱ ዘገባ መሰረት፣ 19 ሰዎች ተገድለዋል፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል  የሟቾች ቁጥር 34 እንደሚደርስ ነው የተናገረው። ይኸው የፀጥታ ኃይላቱ ርምጃ በመላይቱ ሃገር ብርቱ ቁጣ አፈራርቋል። 
የተቃዋሚው ኡማ ተሀድሶ ፓርቲ ሙባራክ ኤል ፋደል ምንግሥት በወቅቱ የሚታየውን ቀውስ  መፍትሔ ሊያገንለት እንደማይችል በመዲናይቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀው ፣ ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የሚለውን ጥያቄአቸውን አጠንክረው አቅርበዋል።
« የሀገሪቱ መንግሥት በወቅቱ የሚታየውን የኤኮኖሚ ቀውስ ለማብቃት አቅሙ እና ችሎታው የለውም። ምክንያቱም፣ የኤኮኖሚያዊው  ቀውስ መነሻ ፖለቲካዊው ቀውስ ነው። ስለዚህ  መፍትሔው ፖለቲካዊ በመሆኑ፣ አዲስ መንግሥት ሊቋቋም ይገባል። »
ፖለቲካዊውን እና ኤኮኖሚያዊውን ችግር ሊያበቃ የሚችለው፣ እንደ ኤልፈደል አስተያየት፣  የሱዳንን ህዝብ እምነት የሚያገን አዲስ መንግሥት ብቻ ነው።    ፕሬዚደንቱ ለህዝቡ ጥያቄን ለመመለስም ሆነ አስፈላጊውን መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አንድም ርምጃ ባለመውሰዳቸው ተቃውሞው ተጠናክሮ ከቀጠለ በኋላ፣ ተቃውሞውን ለማብቃት መንግሥት የወሰደው ርምጃ  የሰው ህይወት መጥፋትን አስከትሏል። በዚሁ ጊዜ  22 የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዚደንት በሺር ከስልጣን እንዲወርዱ እና  በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ስልጣናቸውን ለአንድ ነፃ ምክር  ቤት እና የሽግግር መንግሥት እንዲያስረክቡ  ባለፈው ማክሰኞ ጠይቀዋል።  ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ከመንግሥት ጋር ጉድኝት የነበረው የተቃዋሚው የኡማ ተሀድሶ ፓርቲ ይገኝበታል። የኡማ ተሀድሶ ፓርቲ አባል ሙባራክ ኤል ፋደል ይህን በማውገዝ የህዝቡ ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል።
« ደም መፋሰስን ለማስወገድ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ለማስገኘት የጦር ኃይሉ ከህዝቡ ጎን እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን። »
የለውጥ እና ተሀድሶ ፓርቲ የተባለው የለውጥ እና የተሀድሶ ፓርቲ የተሰኘው ቡድን ሊቀ መንበር ጋዚ ሳለህ አልዲን  የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀ መንበር ጋዚ ሳለህ አልዲቡድን የኃይሉን ርምጃ በመቃወም  ከጥምሩ መንግሥት መውጣቱን አስታውቀዋል።
« በማንኛውም የመንግሥት አካል ውስጥ ያለውን የፓርቲያችንን ውክልና ለማቋረጥ ወስነናል። ከዚህ በተጨማሪም ህዝብ ሀሳቡን በነፃ የሚገልጽበት አሰራርን መሰረታዊ መብት አድርገን ለማስከበር እንደምንሰራ ሊታወቅ ይገባል። »
ይህን ተከትሎ ነበር በሺር አንድ በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ጉዳዩን የሚመለከት ኮሚሽን ለማቋቋም ዝግጁ የሆኑት።   ይሁንና፣ የሱዳናውያኑ ተቃውሞ እስካሁን በምዕራባውያኑ መንግሥታት  ያን ያህል ትኩረት አላገኙም በሚል የተቃዋሚው የሱዳን ኮንግረስ ፓርቲ አባል መሀመድ ሁሴን  አራቢ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
«ዓለም አቀፉ ፖለቲካ ከጥቅም ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን፣ ተቃዋሚዎቹ ንዑሱን ድጋፍ ብቻ ያገኛሉ ብለን ነበር የጠበቅነው። የሱዳን መንግሥት የራሱን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችልበት አካባቢያዊ መረብ ዘርግቷል። ይህን፣ በተለይ፣  በሕገ ወጥ ፍልሰት አንጻር በጀመረው ትግል አማካኝነት እውን አድርጓል፣  ስደተኞች እና ተገን ፈላጊዎች ከአፍሪቃ እንዳይወጡ ለማከላከል ይሞክራል። ከዚህ ጎንም፣ በፀረ ሽብርተንነቱ ትግል ላይ በሰፊው ይተባበራል። በምላሹ፣ አውሮጳውያን የሱዳን መንግሥት ይፈጽመዋል የሚባለውን ጭቆና፣ የተበላሸ አሰራር እና ሙስናን እንዳላዩ ያልፋሉ።»
እርግጥ፣ ሱዳን በፖለቲካው መድረክ አሉታዊ አመለካከት ነው ያተረፈችው።  ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በዘር ጭፍጨፋ እና በጦር ወንጀል በከሰሳቸው ፕሬዚደንት በሺር ላይ የእስር ማዘዣ አስተላልፎባቸዋል። በዳርፉር እና በኑባ ተራሮች ከሚንቀሳቀሱ ዓማፅያን ጋር ውዝግቡ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች  በነዚሁ አካባቢ ለሚታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ለተጓደለው የህዝብ ነፃነት መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ይወቅሳል። 
ይህም ቢሆን ግን ፕሬዚደንት በሺር አሁንም ስልጣን እንደያዙ መቆየት ችለዋል። ለዚህም  የሱዳን መንግሥት እና የብዙ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጥቅም የተያያዘበት ድርጊት ምክንያት መሆኑን DW ያነጋገራቸው ሊባኖሳዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አሚን ቃሙሪያ ፣ በየመን በሳውዲ መራሹ ጦር መሪነት በሚካሄደው ጦርነት ላይ ብዙ የሱዳን ወታደሮች  መሰማራታቸውን  እንደ ምሳሌ በመጥቀስ  አስረድተዋል። ከዚሁ ተጠቃሚ የሆነችው ሳውዲ ዐረቢያ፣ ይላሉ ቃሙሪያ፣  ሱዳን ወታደሮቿን ከየመን እንድታስወጣ አትፈልግ ። ግብፅም ብትሆን የደቡባዊ  ጎረቤቷ ሱዳን መረጋጋት እንዲደፈርስ  አትፈልግም፣ ምክንያቱም፣ ቀውስ በቀጠለባት ሊቢያ ውስጥ የሚዘዋወረው  እና በሱዳን በኩል ይገባል የምትለው ብዙ የጦር መሳሪያ ሊቢያ እንዳይደርስ ከፕሬዚደንት በሺር መንግሥት ጋር በመተባበር ለማከላከል  ሙከራዋን ቀጥላለች። ከዚህ ሌላም ምዕራቡ ዓለም፣ ለምሳሌ  ዩኤስ አሜሪካ ሱዳንን እንደምትደግፍ የተቃዋሚው የሱዳን ኮንግረስ ፓርቲ አባል መሀመድ ሁሴን አራቢ ይናገራሉ።
«   ዩኤስ አሜሪካ ፣ በተለይ፣ ጦሯን ከሶርያ ለማስወጣት ወስናለች። ይኸው ውሳኔዋ የፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈንም ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በሶርያ ለማሰማራት እየሞከረች ነው፣  ይህን ጥረቷን በማሳካቱ ላይ እስካሁን የሱዳንን ያህል ቅጥረኛ በርካሽ የሚያቀርብ አንድም መንግሥት የለም።  »
የአውሮጳ ህብረት አባል መንግሥታትም፣ በተለይ፣ ከምሥራቅ አፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ሕገ ወጥ ፍልሰት በማከላከሉ ረገድ ከበሺር ጋር ጥሩ ትብብር  እንዳላቸው  በርሊን የሚገኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ እና የሱዳን ጉዳይ አጥኚ አኔተ ቬበር ያወጡት አንድ ጽሁፍ ያሳያል። በዓለም አቀፉ ፀረ ሽብርተኝነት ትግልም ላይ ምዕራቡ ዓለም እንደ ዋነኛ አጋር የሚመለከታቸው በሺር ፣ በተለይ ህገ ወጥ ፍልሰትን ለማስቆም ለሚያደርጉት ትብብር በምላሹ ከአውሮጳ ህብረት  የገንዘብ ድጋፍ  ይጠብቃሉ።  ምዕራቡ ዓለም የሱዳን ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ችላ ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሃገሪቱ ካለፉት ሳምንታት ወዲህ የቀጠለው ተቃውሞ ዓለም አቀፍ ትኩረት ሳያገኝ ነው የቀረው።  ይህን የተገነዘቡት ፕሬዚደንት በሺርም  ዓለም አቀፍ ጥቅምን እስካስጠበቁ ድረስ ፣ የምዕራባውያኑን ዝምታ በስልጣናቸው ለመቆየት እንደ ፖለቲካ ዋስትና ተመልክተውታል።    

Türkei Ankara - Sudans Präsident - Omar Bashir
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Ozbilici
Sudan, Brot
ምስል picture-alliance/M.Elshamy

አርያም ተክሌ/ኬርስተን ክኒፕ

እሸቴ በቀለ