1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምርጫ ሥርዓቱ ላይ የጀመረዉ ድርድር አልተቋጨም፤

ረቡዕ፣ ጥቅምት 8 2010

በገዢዉ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎችየሚያደርጉት ድርድር በኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት ላይ ዉይይቱን ለመቀጠል ቀጠሮ ይዟል። በትናንቱ ድርድርም ኢህአዴግ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት፤ ተቃዋሚዎች ተመጣጣኝ ዉክልና የሚል ሃሳብ ቢያቀርቡም፤ «ቅይጥ ትይዩ» የሚለዉ ሃሳብ በገዢዉ ፓርቲ መነሳቱን በድርድሩ የሚካፈሉት የመኢአድ ዋና ጸሐፊ ለዶቼ ቬለ አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/2m6wm
Äthiopien Verhandlungsrunde zwischen Regierung und Opposition
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

የምርጫ ሥርዓቱን የተመለከተዉ ድርድር ቀጥሏል፤

በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና በ16ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ትናንት የተካሄደዉ ድርድር ዋነኛ ትኩረት የሀገሪቱ የምርጫ ሥርዓት እንደነበር ከተደራዳሪዎቹ ፓርቲዎች አንዱ የመኢአድ ዋና ጸሐፊ እና የሕዝብ ግንኙነት አቶ አዳነ ጥላሁን ይናገራሉ። 
«ኢህአዴግ ያቀረበዉ ቅይጥ ትይዩ ዉክልና የሚል ነዉ። በዚያም መሠረት እና 12 ፓርቲዎች በአንድ ሆነን ነዉ፤ ድርድሩን የምናካሂደዉ እኛ ያዉ ተመጣጣን ዉክልና የሚል ነዉ ያቀረብነዉ፤ ኢህአዴግ ያለዉን ለመቀበልም ወይም ደግሞ እኛ በራሳችን ለመሄድም መጀመሪያ እስኪ ፐርሰንት እናስቀምጥ ብለነዉ 10 ፐርሰንት ለተመጣጣኝ ዉክልና ዘጠና ፐርሰንት ደግሞ ያዉ ለአብላጫ ድምጽ አድርጓል፤ እኛ ደግሞ ሃምሳ ፐርሰንት ለአብላጫ ድምጽ ሃምሳ ፐርሰንት ለተመጣጣኝ ዉክልና በሚል በዚህ ላይ ሳንስማማ እስኪ ጊዜ ስጡኝ ስላለ ጊዜ ሰጥተን ለቅዳሜ ልንቀጥል በዚህ ነዉ የተለያየነዉ። ይኼ ነዉ እንግዲህ የትናንቱ ዉሏችን።»
«መጀመሪያ ደረጃ ላይ አሁን በየ ወረዳዎቹ በአብላጫ ድምጽ የሚሰጠዉ ይሰጣል፤ ከዚያ በኋላ፤ አሁን ምንድነዉ ኢህአዴግ መቶ ፐርሰንት ያደረገዉ ማሸነፍ ትንሽ ወደ ሕዝባዊነት ስላላመጣለት እና አንዳንድ እንትኖች ስላደረጉ፤ እኛ ባቀረብነዉ ማለት ነዉ ሃምሳ ፐርሰንት በአብላጫ ድምጽ ዉድድሩ ተካሂዶ በቀሪዎቹ ደግሞ ያዉ በሬሾ ለምሳሌ አንድ ወረዳ ላይ የተወዳደረ አንደኛዉ በአብላጫ ድምጽ ቢሄድ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በሆኑት ደረጃ ላይ ፓርቲዎች ዉክልና እንዳያጡ ለማለት ነዉ።»
ይህም ሆኖ በጉዳዩ ላይ ገና ከስምምነት እንዳልተደረሰም አስረድተዋል። 
«እኛስ እራሱ መች ተስማማን ነገርኩሽ እኮ፤ እኛ ያቀረብነዉ ተመጣጣኝ ዉክልና የሚል ነዉ። እና አሁን እዚያ ላይ ዲስቶርትድ እንዳትሆኑ ስለፈለኩኝ ነዉ፤ እና ያቀረብነዉ ምንድንነዉ ለኢህአዴግ፤ አንደኛ ይሄ ቅይጥ ትይዩ የሚለዉ የሚባለዉ ነገር ለእኛ አዲስ ነዉ፤ ስለዚህ በፐርሰንት ደረጃ ስንት ፐርሰንት ሊያስቀምጥ ፈልጎ ነዉ? አጀንዳዉ የእርሱ ስለሆነ፤ ይህን አስቀምጥ እና የሚስማማን ከሆነ እኛ ለህዝብ የሚጠቅም ከሆነ ወደሙሉ ድርድር እንመጣለን የማይጠቅም ከሆነ ደግሞ ያዉ ባስቀመጥነዉ የድርድር ሕግ መሠረት በልዩነት ሃሳባችንን ሰጥተን እንሄዳለን በሚል አስር ፐርሰንት አስቀምጧል እኛ ደግሞ ሃምሳ ፐርሰንት አስቀምጠናል።  ገና አጀንዳ መች ተቋጨና ስምምነት እንደርሳለን አልደረስንም።»

Äthiopien Verhandlungsrunde zwischen Regierung und Opposition
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ቅይጥ ትይዩ የሚለዉ አብላጫ ድምጽ ሲደመር የተመጣጣኝ ዉክልና ማለት መሆኑን የገለጹት የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ፤ እንዲህ አይነት የምርጫ ስርዓት የሚከተል ሀገር እንዳለ ለቀረበላቸዉ ጥያቄም ተከታዩን ብለዋል። 
«እንግዲህ በእኛ በኩል ይሄንን እንደዉም በእኛም በኩል ትናንትም አቅርበናል በዚህ ደረጃ ላይ እንደዉም ስልጠና ሊሰጥ ይገባል ከምን እንዳነሳችሁት ሁሉ የሚል አለ። ለአሁኑ ግን ያዉ ዴሞክራሲን ኤክሰርሳይስ ለማድረግ እና በተለይም የሕዝቡን ዉክልና እያንዳንዱ ፓርቲዎች በተቃዉሞ ደረጃም ቢሆን የተወሰነ የሰዉ ኃይል አባል ስላላቸዉ ፤ ያላቸዉን የአባላት ፍላጎት ላለመዝጋት በዚህ መልክ መሄድ አለብን የሚል ነዉ። እኛም ጠይቀናል ስልጠና ሊሰጥ ይገባል፤ ዞሮ ዞሮ ግን  ያዉ ለሀገር ሰላም እስካመጣ ድረስ በዚህ መልክ መሄድ አለበት የሚል ነዉ እንግዲህ።»
ካለፈዉ ዓመት አንስቶ ወራት ያስቆጠረዉ የድርድር ሂደት እስካሁን አጀንዳ አንድ ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ አዳነ ጥላሁን፤ በርካታ የመደራደሪያ አጀንዳዎች ያሉት የፓርቲዎቹ ዉይይት ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል ብሎ ከወዲሁ መገመት እንደማይቻልም አስረድተዋል። በእሳቸዉ ግምትም አጀንዳ ሦስት ሰፋ ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል።
«አሁን ገና እኮ አጀንዳ አንድ ላይ ነዉ ያለነዉ፤ ያቀረብነዉ አጀንዳ በጣም በርካታ ነዉ። አሁን በተለይ በሦስተኛ ደረጃ የፀረ ሽብር ሕጉ አለ፤ በዚያ ላይ እንደተቃዋሚ የምናነሳቸዉ በርካታ እንትኖች አሉ፤ በዴሞክራሲ ደረጃ የምናነሳቸዉ በጣም በርካታ ነገሮች አሉ። እንግዲህ እስካሁን በቆየንባቸዉ ድርድሩ በጣም ሰፍቶ እና አሰልቺ እስከመሆን ደረጃ ደርሶ ገና በምርጫ ሕግ እና በምርጫ ዙሪያ ላይ ባሉ  ሕጎች ላይ ነዉ ገና እየተወያየን ያለነዉ።» 
እንዲያም ሆኖ አቶ አዳነ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ አንድ ለመሆን በመግባባት ድርድሩ አሰልቺ እንዳይሆን የማድረግ ሃሳብ መኖሩንም አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ