1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሻሸመኔዉ ግድያ እና የኦሮምያ ክልል ቃል አቀባይ መልስ

ሰኞ፣ ነሐሴ 7 2010

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሻ መኔ ከተማ  በትናንትናዉ እለት ቦንብ ይዟል በሚል ጥርጣሬ  በአሰቃቂ  ሁኔታ አንድ ወጣት መገደሉ  አፀያፊና የሚወገዝ ተግባር ነዉ ሲል የኦሮሚያ ክልልላዊ መንግስት ገለፀ። የክልሉ የኮሚንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለፁት የተፈጸመዉ ድርጊት አሳዛኝ፣ ከባህል ዉጭና አስነዋሪ ነዉ።

https://p.dw.com/p/336WQ
Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

Shashemene/new/ - MP3-Stereo


የክልሉ የፀጥታአካላት በድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ስራ መጀመራቸዉንም  ሃላፊዉ አመልክተዋል።በዕለቱ ተረጋግጠዉ ህይወታቸዉን ላጡ  3 ሰዎችም ሀዘናቸዉን ገልፀዋል።  ሻሻ መኔ ከተማ  የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሀመድንና ሌሎች የቡድኑን  አባላት ለመቀበል በተሰናዳ ዝግጅት ላይ በተፈጠረ  ግግርግርና መረጋገጥ እንዲሁም ቦምብ ተያዘ በሚል ጥርጣሬ  በትናንትናዉ ዕለት  የሰዎች ህይወት መጥፋቱ ሲዘገብ ቆይቷል።የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ  በተለያዩ  አካላት የተለያዬ ቁጥር የተነገረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ባለዉ መረጃ የሟቾች ቁጥር 4 ብቻ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
በትናንትናዉ ዕለት ህይወታቸዉን ላጡ ሰዎች ሀዘናቸዉን የገለፁት ዶክተር ነገሪ፤ ከህዝቡ ብዛትና መጨናነቅ የተነሳ በትናንትናዉ ዕለት ሁለት ሰዎች ተረጋግጠዉ መሞታቸዉን ነዉ የተናገሩት። በዛሬዉ ዕለት ደግሞ በህክምና ላይ የነበረ አንድ ተጨማሪ  ሰዉ ህይወቱ ማለፉን ሀላፊዉ አመልክተዋል።
ከሟቾቹ በተጨማሪ የተጎዱ ሰዎች መኖራቸዉን ገልፀዉ ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ያልሄዱ ሰዎች በመኖራቸዉ ትክክለኛዉን ቁጥር ለመግለፅ አስቸጋሪ ቢሆንም በዕለቱ በርካቶች መጎዳታቸዉንና አንድ የመንግስት ተሽከርካሪ መዉደሙን ተናግረዋል።በመረጋገጥ ህይወታቸዉን ካጡ ሰዎች በተጨማሪም ቦንብ ይዟል በሚል ጥርጣሬ በአሰቃቂ  ሁኔታ አንድ  ወጣት በዕለቱ መገደሉን አመልክተዉ ፤ ጉዳዩን ለህግ አካላት ማቅረብ ሲገባ ፤ ግለሰቦች በራሳቸዉ ፍርድ ሰጥተዉ ሰዉን መግደል ግን ትልቅ ወንጀልና የሚወገዝ  ነዉ ሲሉ  ድርጊቱን ኮንነዋል።
የተፈጸመዉ ድርጊት ከባህል ዉጭና የሚያሳዝን በመሆኑ  ይህንን ወንጀል በመስራት የተጠረጠሩ ሰዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ የፀጥታ አካላት የተወሰኑ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸዉን ዶክተር ነገሪ አስረድተዋል ።ጉዳቱ እንደደረሰ የፀጥታ አካላት ወዲያዉኑ ምርመራ መጀመራቸዉን የገለፁት ሃላፊዉ፤« በገንዘብ ተታለዉ የዉሸት ወሬ በማሰራጨት« ጉዳት አድርሰዋል ያሏቸዉን ሰዎች በፎቶ ጭምር መረጃ በመያዝ በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ቌንቋዎች ባህልና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ያሉባት እንደመሆኗ መጠን ልዩነትን ለሰዉ ልጅ ፍቅር፣ ክብርና እኩልነት  ባለዉ መንገድ  በዉይይትና በህጋዊ መንገድ መፍታት የሚገባ ቢሆንም ከዚህ ተጻራሪ ቆመዋል ያሏቸዉ ሀይሎች ወጣቱን እንደመሳሪያ እየተጠቀሙ በመሆኑ በክልሉ መሰል ድርጊቶችን ለመከላከልና የህግ የበላይነትን ለማስከበር  የክልሉ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነዉ ብለዋል። «ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ አካላት አሉ።ለዉጡንም የሚቃወሙ ብዙዉን ጊዜ ወጣቶችን እንደ መሳሪያ የሚጠቀሙባቸዉ ሁኔታ ነው የሚታየው። ይህ በእኛ በኩል መቆም አለበት። እንዲህ አይነት ህዝባዊ መድረኮችም በዚህ ሁኔታ አላስፈላጊ እንደሆኑ ነዉ የሚታዩንና ከሁሉም የሚቀድመዉ የዜጎቻችን ደህንነት ነዉ። ሰላምነዉ።ስለዚህ አሁን የተገኙት ዉጤቶች የበለጠ ለህዝብ ጥቅም እንዲዉል ከተፈለገ የህግ የበላይነት ለማስከበር ሀላፊነት ስላለብን እንሰራለን።»ነዉ ያሉት።

Ähiopien Regierungssprecher Negeri Lencho
ምስል DW/Y. G. Egziabher
Äthiopien Negeri Lencho
ምስል DW/G. Tedla

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ