1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ እና እንዲበተን ተጠየቀ

ሰኞ፣ ነሐሴ 14 2010

ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምኒስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ ነው ያለውን የሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል የፌደራል መንግሥት ትጥቅ እንዲያስፈታ እና እንዲበተን እስካሁን ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሞት እና አካል መጉደል ተጠያቂ የሆኑት የልዩ ኃይሉ አመራሮችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀ ::

https://p.dw.com/p/33RYP
Logo von Amnesty International

M M T/ Somalia reion special police crimes Against Humanity - MP3-Stereo

የእንግሊዙ  ዘ ጋርዲያን ዴይሊ ቴሌግራፍ እና ሌሎች የመገናኛ አውታሮች " ለክልሉ ሰላም እና ልማት ማጠናከሪያ " በሚል መርሃግብር በጭካኔ ተግባሩ ለሚከሰሰው ለሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል  ስልጠና እና ድጋፍ የሚውል 15 ሚልዮን ፓውንድ የገንዘብ ልገሳ አድርጓል ያሉትን የእንግሊዝ  መንግሥት ክፉኛ ወቅሰዋል :: በአምኒስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጉዳይ ተመራማሪ ክሌር ቤስቶን በበኩላቸው እ.ኤ.ኣ በ 2013 ዓ.ም የብሪታንያ መንግሥት ከዚህ ኃይል ስልጠና ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ መገለጹ  እውነት ከሆነ አሳሳቢ ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃኑ ተናግረው ነበር :: በአምኒስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ፍሥሐ ተክሌም እስካሁን ድርጅታቸው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያረጋገጠው ነገር እንደሌለ ገልጸውልናል::

በአዲስ አበባ የብሪትሽ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ለዶቼቨለ በላኩት የጹፍ ማብራሪያ " የእንግሊዝ መንግስት የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይልን ከማሰልጠን አልፎ አስታጥቋል ተብሎ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተሰራጩ ዘገባዎች የተሳሳቱ ናቸው በማለት አስተባበለዋል:: በሶማሌ ክልል እ.ኤ.አ ከ 2013 እስከ 2015 ድረስ ብሪታንያ ያደረገችው ድጋፍ ህፃናትና ሴቶች ተኮር ለሆነ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ስልጠና መሆኑንም መግለጫው ያትታል። በአካባቢው የትምህርት የጤና እና የንፁሕ የመጠጥ ውሀ አቅርቦትን ማሻሻል እንዲሁም የክልሉን ልማት እና ሰላም ማጠናከርም ሌላው የመርሃግብሩ አካል ነበር :: ፕሮግራሙ በ 2015 ዓ.ም ያበቃ ሲሆን ድጋፉ ሲደረግ የነበረው በእንግሊዝ ዓለማቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (DFID ) በኩል እንደነበርም አስታውቋል ::

 ሽብርተኞችን ይዋጋል ተብሎ የተደራጀው የሶማሌው ልዩ ፖሊስ እራሱ ዜጎቹን የሚያሸብር የአካባቢው የሥጋት ምንጭ ኃይል እየሆነ መቷል ሲሉ ብዙዎች ይወቅሳሉ :: ሰሞኑን እንኳ በክልሉ በተከሰትው አለመረጋጋት የዜጎች በሕይወት የመኖር፣ ንብረት የማፍራት፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እና የሃይማኖት ነፃነት መብቶች ጭምር ጥያቄ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ፍሥሐ ተክሌ በበኩላቸው ልዩ ኃይሉ ትጥቅ ፈቶ እንዲበተን እና ትዕዛዝ የሚሰጡት አካላትም በአስቸኳይ ልፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል::
 

በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን የበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት በግፍ የቀጠፈ እና አያሌ ንብረት ያወደመ አለመረጋጋት ለመቆጣጠር ምንም እንኳ መንግሥት መከላከያ ሰራዊቱን በመላክ እና ኮማንድ ፖስት በማቋቋም አጥፊዎቹ ተጣርተው በህግ ይጠየቃሉ ቢልም ሰሞኑን በጅጅጋ በድሬዳዋ እና በኦሮምያ ክልል ጭምር በደረሰው አሰቃቂ የሰብዓዊ እልቂትና የንብረት ውድመት የፌደራል መንግስቱ ሰራዊት እዛው ሶማሌ ውስጥ ካምፖች ውስጥ ሰፍሮ እያለ ፈጥኖ እርምጃ እንዲወስድ አላደረገም የሚል ትችት እየቀረበበት ነው።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ኂሩት መለሰ