1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልሎችን የተመለከተው የሰመጉ ዘገባ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 2010

የሰብአዊ  መብቶች ጉባኤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢዎች የተካሄደውን ግጭት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም አሳሰበ። በግጭቱ እና የመብትጥሰቱ በሁለቱ ድንበር የብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ጉባዔው ትናንት ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/32RrJ
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ መስተዳድሮች አዋሳኝ አካባቢዎች ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የሚካሔደዉን ግጭት እና የቀጠለውን የሰብአዊ  መብት ጥሰት የኢትዮጵያ መንግሥት  እንዲያስቆም  የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) አሳሰበ። ሰመጉ ይህን ማሳሰቢያ ያሰማው ትናንት ግጭቱን በተመለከተ ዝርዝር ዘገባ  ባወጣበት እና  ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ርዳታ ማስተባበሪያ መሥሪያ ቤት፣ በምህጻሩ ከኦቻ ጋር  በጋራ  መግለጫ በሰጠበት ጊዜ ነው። ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የድርጅቱ ተጠባባቂ  ዳይሬክተር አቶ ብያንያም አባተ እንደተናገሩት፣ የሰመጉ ዘገባ ሁለቱን ክልሎች በሚያዋስነው ድንበር ከጥር 2009 እስከ ጥር 2010 ዓም ድረስ ብቻ በነበረዉ ጊዜ የታየውን ግጭት፣ ምክንያቱን  እና መዘዙን ነው የሸፈነው። በተባለው አንድ ዓመት በግጭቶች በብዙ መቶዎች መገደላቸውን አቶ ብንያም  ተናግረዋል።
ይሁንና፣ በአቅም ውሱኑነት እና በፀጥታ ምክንያት የጉባኤዉ ባለሙያዎች ያጣሩት የተወሰኑ አካባቢዎችን ብቻ ስለሆነ ዘገባው የደረሰውን ጉዳት ሙሉ ለሙሉ የሚያሳይ አለመሆኑን አቶ ብንያም አክለው በማስረዳት፣  የሟቾቹ ቁጥር ከተጠቀሰዉ መብለጡ እንደማይቀር ገልጸዋል።
ጉባዔው ከሁለቱ ክልሎች መረጃ ለማግኘት ቢጠይቅም  የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ባለስልጣናት መረጃ ሊሰጡት እንዳልቻሉ አስታውቆ፣ በዘገባው ያካተተው በመስክ ምርመራ ወቅት በክልሉ ተንቀሳቅሶ ያገኛቸውን የመብት ጥሰት ዓይነቶች፣ ብዛት እና ዝርዝሩን ብቻ መሆኑን አቶ ብንያም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ መሠረት ፣ በኦሮሞና በሶማሌ ክልሎች በብሔር ተኮር ግጭቶችና ጥቃቶች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ እጅግ ብዙ ንብረት ተዘርፏል ወይም ወድሟል። 
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የሰመጉን ዘገባ በተጨማሪ መሠረት በማድረግ ማስተካከያ ርምጃዎችን እንዲወስድ አቶ ብንያም አባተ ጠይቀዋል።

Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ