1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳርሲስ ቀባሪዎች

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2010

በየሁለት ዓመቱ የተመድ የሚያወጣዉ ዘገባ በዓለም 250 ሚሊየን ትዉልድ ሀገሩን ትቶ የፈለሰ ስደተኛ እንዳለ ትናንት የዓለም የፍልሰት ቀን ሲታሰብ ጠቁሟል። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም ወዲህ ደግሞ በ49 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/2peOs
Zarzis  Tunesien  Chemseddine Marzoug vom Roten Halbmond Migrantenfriedhof
ምስል DW/S.Mersch

በባህር ሰምጠው የሚሞቱት ስደተኞች የመጨረሻ ማረፊያ

የስደት መንገድ ሁሌም አልጋ በአልጋ አይሆንም እና በያመቱ በሜድትሬንየን ባህር ሰምጠው ከሚሞቱት ስደተኞች መካከል የብዙዎቹ አስከሬን ተገፍቶ ደቡባዊ ቱኒዝያ ይደርሳል። አንድ የቱኒዝያ ዜጋ ታዲያ እነዚህን በሕይወት ሳሉ ክብር የተነፈጋቸውን ስደተኞች በክብር ለመቅበር ይሞክራሉ።
ቱኒዝያዊ  ቸምሰዲን ማርሱግ ሁለት ጠርሙስ ውኃ ይዞ ከአንድ የቆሻሻ ማከማቻ አቅራቢያ ወደሚገኘው እና ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች መካነ መቃብር የሚል በብዙ ቋንቋዎች የተጻፈ ምልክት ወደሚታይበት ቦታ ይሄዳሉ።  ባለፈው ዓመት በዚሁ ቦታ ከ350 የሚበልጡ  ስደተኞች አስከሬኖች ተቀብረዋል።  በተያዘው ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም እዚህ የተቀበሩት 74 ናቸው። ማርሱግ ይኸው ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለው ሰግተዋል። ምክንያቱም  በክረምቱ ወራት ከምሥራቅ የሚመጣው ነፋስ በሚያይልበት ጊዜ ፣ ያኔ ባህሩ ብዙ አስከሬኖችን ወደ  ሳርሲስ ባህረ ሰላጤ መግፋቱ አይቀርም። በቱኒዝያ ደቡባዊ የባህር ጠረፍ ላይ የምትገኘዋ ትንሿ የሳርሲስ ከተማ ወደ አውሮጳ ለመምጣት የሚፈልጉ ስደተኞችን ያሳፈሩ ጀልባዎች ከሚነሱበት የሊቢያ ድንበር 50 ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገናለች።  እነዚህ ማርሱግ «የሞት ጀልባዎች» ብለው የሚጠሯቸው ጀልባዎች አዘውትረው የመስመጥ ችግር ያጋጥማቸዋል። ተሳፋሪዎቹ  ዕድለኞች ከሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም ያካባቢው ሃገራት የባህር ኃይላት ይደርሱላቸውና  ከመሞት ይድናሉ። ያልታደሉት ደግሞ መጨረሻቸው ሳርሲስ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።  
የ52 ዓመቱ ማርሱግ ማንነታቸው በማይታወቁት ሰዎች መቃብር መካከል እየሄዱ፣ አልፎ አልፎም ተከዝ ብለው ይቆማሉ፣ ጎንበስ ብለውም አፈር የተከመረበት መቃብር ላይ የተከሉትን አበባ ውኃ ያጠጣሉ። በሁለት ሕፃናት መቃብርም ላይ ሌጎ ወይም የሚገጣጠሙ እና ትናንሽ መጫወቻ መኪኖች አስቀምጠዋል። ምንም እንኳን የሟቾችን ስምም ሆነ ትውልድ ቦታ ባያውቁም  በግብረ ሰናዩ የቱኒዝያ ቀይ ጨረቃ ድርጅት በፈቃደኝነት የሚሰሩት ማርሱግ እያንዳንዱ መቃብር የራሱ ታሪክ አለው ይላሉ።  በአንዱ መቃብር ላይ ብቻ ግን  ቁጥር ተጽፎ ይታያል፣ የአንድ ማንነቷ የታወቀች ሴት መቃብር መሆኑን ማርሱግ ገልጸዋል።
« እዚህ የተቀበረችው ሮዝ ሜሪ ትባላለች። የ 28 ዓመት ናይጀሪያዊት አስተማሪ ነበረች። ባለፉት የፀደይ ወራት ነበር ሰምጣ ሕይወቷን ያጣችው።  የቱኒዝያ ባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከአደጋው የተረፉትን 126 ስደተኞች ወደዚችው ከተማ አምጥተዋቸዋል። የሮዝ ሜሪም ወዳጅ እዚህ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይኖራል። ከትናንት ወዲያ አበባ ይዞ ወደ መቃብሯ መጥቶ ነበር። »
ቸምሰዲን ማርሱግ ዓሣ አስጋሪ ነበሩ። ከጎርጎሪዮሳዊው1990 መጨረሻዎቹ ዓመታት ወዲህ እሳቸውና አቻዎቻቸው በዓሣ ፈንታ ወጥመዳቸው ውስጥ የሚያገኙት አስከሬኖች እና የሰውነት አካላት ሆነ።  ያኔ ከመስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር አስከሬኖችን የመቅበሩን ስራ ማከናወን ጀመሩ፣ ግን የውጭ ዜጎች አስከሬን  በመብዛቱ ለሀገሬው ሰው ቦታ የለም ሲሉ የሳርሲስ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ። በዚህም የተነሳ የከተማይቱ አስተዳደር የስደተኞቹ አስከሬን በከተማይቱ ዳር ነዋሪዎቹ ቆሻሻ ለመጣያ በሚጠቀሙበት ቦታ እንዲቀበር ማዘዙን ማርሱግ አስታውሰዋል።
« እነዚህ ሰዎች በትውልድ ሀገራቸው እና ሊቢያ ውስጥ በደል ይደርስባቸዋል፣ ከፊሎቹ በበረኃ ወይም ለሞት በሚያጋልጡ ጀልባዎች አደገኛውን ጉዞ ሲያደርጉ ሕይወታቸው ያልፋል። እና ቢያንስ በክብር ሊቀበሩ ይገባል ባይ ነኝ። »
ይህ ሥራቸው ቀላል ባይሆንም እንደተቀበሉት ማርሱግ ገልጸዋል። ምክንያቱም፣ ሞት ፊት ሁሉም ሰው እኩል ነው ብለው ስለሚያምኑ። የሰው ልጅ አሁን በምድራችን የቀረውን ንዑሱን ስብዕና ለመጠበቅ ካልሞከረ በስተቀር በቅርቡ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊፈነዳ እንደሚችል ማርሱግ በስጋት ገልጸዋል።

Zarzis  Tunesien  Chemseddine Marzoug vom Roten Halbmond Migrantenfriedhof
ምስል DW/S.Mersch
Zarzis  Tunesien  Chemseddine Marzoug vom Roten Halbmond Migrantenfriedhof
ምስል DW/S.Mersch

አርያም ተክሌ/ሳራ ሜርሽ

ሸዋዬ ለገሠ