1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰደድ እሳት  እና የኢትዮጵያ ደን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 11 2010

የደን ይዞታን ከሚያመናምኑ ነገሮች አንዱ በደን አካባቢዎች የሚነሳ እሳት ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥመዉ የሰደድ እሳት በደረቅ የአየር ሁኔታ፣ ለእርሻ እና ለመኖሪያ ሲባል እንዲሁም በንዝህላልነት ሊነሳ እንደሚችል ነዉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።

https://p.dw.com/p/2ueui
Äthiopien Wald
ምስል Dr. Adefris Worku

ደረቅ የአየር ሁኔታ የሚያስከትለው እሳት ይበዛል፤

የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ በቄለም ወለጋ ዉስጥ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ያለዉ ደን በእሳት ተያይዞ ዛፎች እንደወደሙ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ጥቆማቸዉን አድርሰዋል። ስለተፈጠረዉ ስማቸዉ እንዳይገለፅ የጠየቁ ከነዋሪዎቹ አንዱ «የተቃጠለው ወለል ነው፤ ወለል ተራራ። የተቃጠለዉ መከላከያ የሚባል ሠራዊቶች ናቸዉ ያቃጠሉት የኦነግ ሠራዊት እዚያ ይኖራል ከነጫካዉ እናቃጥላለን ብለዉ ነው። 250 ሄክታር ይሆናል የተቃጠለው።»

ከዚህ ጥቆማ በመነሳት ሁኔታዉን ለማጣራት ጉዳዩ ወደሚመለከታቸዉ ኃላፊዎች በስልክ ለሰዓታት ካደረግነዉ ሙከራ በኋላ የኦሮሚያ የደን እና የዱር አራዊት ድርጅት ዳይሬክተርን አገኘን። ጉዳዩን ለማጣራት ጥቂት ጊዜ የወሰዱት አቶ ጢዳ ድሪባ በተባለዉ ተራራ ላይ የሚገኘዉ ደን ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም እሳት ተነስቶበት እንደሚያዉቅ ነዉ ያስረዱት።

 «ከሁለት ሳምንት በፊት ነዉ እሳቱ የነበረዉ እዛ ወለል ተራራ ላይ። እዛ ብቻ አይደለም አልፎ አልፎ ሌላ ቦታም ይከሰታል እሳት። አሁንም ኤሉባቡር ዉስጥ የሆነ ቦታ ተከስቷል፤ ይከሰታል ደረቅ ስለሆነ አየሩ።»

እንዲያም ሆኖ የአካባቢዉ ነዋሪ በደኑ ዉስጥ ታጣቂዎች አሉ በሚል ሆን ተብሎ የተለኮሰ ነዉ ስለሚለዉ መረጃ የሚያዉቁት እንደሌለ አፅንኦት ሰጥተዉ ገልጸዋል። በተጨማሪም 250 ሄክታር የሚሆን ደን ተቃጥሏል የሚለዉም ቢሆን የተጋነነ እንደሆነ ነዉ ያመለከቱት።

Äthiopien Wald
ምስል Dr. Adefris Worku

ኢትዮጵያ ዉስጥ የበጋዉን የአየር ጠባይ ተከትሎ ደረቅ የአየር ሁኔታ ባለባቸዉ የደን አካባቢዎች የሰደድ እሳት መነሳቱ የተለመደ መሆኑን ነዉ አቶ ዲዳ የሚያስረዱት። በተለይም ከታኅሳስ እስከ የካቲት ባሉት ጊዜያት። በኢትዮጵያ የደን አካባቢዎች እሳት እንዲነሳ ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች ይታወቁ ይሆን?

«አንዱ ወቅቱ ለእሳት የተመቻቸ ጊዜ ነው። ነፋሻማ እና ደረቅ የአየር ሁኔታ ነዉ ያለዉ አሁን። ስለዚህ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የራሳቸዉን ማሳ ለማጽዳት የሚለኩሱት እሳት ከእጃቸዉ ይወጣል፤ አንዳንድ ጊዜም መንገደኛም ሲጋራ አጭሶ አለአግባብ የሚጥል ከሆነ መነሻ ይሆናል አንዳንዴ ደግሞ ማር ለማዉጣት ብለዉ ለምሳሌ ወለል ተራራ ማር ያለበት ቦታ ነዉ ትልቅ ተራራ ነው። ለማርም ብለው ያወጡ እና እሳቱን በአግባቡ አያጠፉትም። ከዚያ በኋላ ይነሳል። ተቀጣጣይ ነገር አለ፣ ኃይለኛ ንፋስ አለ፣ ኃይለኛ ድርቀት አለ፤ ስለዚህ ይቃጠላል።»

ወለል ተራራ ኅብረተሰቡ ማር የሚያገኝበት አካባቢ መሆኑ ነዉ የኦሮሚያ የደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት ዳይሬክተር የገለፁት። ከሰሞኑ 16 ሄክታር አዳረሰ የተባለዉ የእሳት አደጋ ያደረሰዉ የጉዳት መጠንም በስፍራዉ ተገኝቶ ማጣራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። ሆኖም እሳቸዉ እንደሚሉት እንዲህ ባሉ አካባቢዎች በእሳት የሚጎዳዉ ደን ቶሎ ያገግማል።

Äthiopien Mädchen beim Wasserholen
ምስል picture alliance/Ton Koene

«በስፍራዉ ተገኝቶ ኢንቨንተሪ ማካሄድ ያስፈልጋል። እንደዚህ አይነት ቦታ ላይ ያሉ ዛፎች ቶሎ ያገግማሉ። ያንን ቃጠሎ የሚቋቋሙበት የራሳቸዉ የተፈጥሮ አዳፕቴሽን የሚባል ነገር አላቸዉ። ከፍተኛ የሚሆነዉ የተከልነዉ ባህር ዛፍ ምናምን ላይ ቢሆን ነዉ፤ እሱ ቶሎ ይቃጠላል። እነሱ ይጎዳሉ። የተፈጥሮ ደኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ራሱን የማገገም ባህሪ አለዉ።»

አያይዘዉም ደን በእሳት አደጋ  ከሚደርስበት ጉዳት ይልቅ በምንጣሮ ይበልጥ ሊጎዳ እንደሚችል ነዉ የሚያስረዱት።

በአዉሮጳም በሰሜን አሜሪካም በየዓመቱ የደን የእሳት ቃጠሎ የሚጋጥማቸዉ ሃገራት መኖራቸዉ ይታወቃል። የዩናይትድ ስቴትስ ደረቃማ አካባቢ እና የአዉስትራሊያ የሰደድ እሳት የዓለምን የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ከሚስቡት መካከል ይጠቀሳሉ። አቶ ጢዳ እንደሚናገሩት ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ የደን የእሳት ቃጠሎ የሚያጋጥመው ከአየር ሁኔታዉ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ይናገራሉ።

Äthiopien Wald
ምስል Imago/blickwinkel

ይህ በሁሉም አካባቢ በአንድ ጊዜ እንደማይሆን ነዉ ያመለከቱት። ደረቁ የአየር ሁኔታ ተራዝሞ እስከ ሚያዝያ የሚደርስ ከሆነም ሊያስቸግር እንደሚችልም ገልጸዋል። በዚህ ሁኔታ ከተከሰቱትም ከፍተኛ ያሏቸዉን የደን ቃጠሎዎች ያጋጠሙበት ወቅት እንዲህ ዘርዝረዋል።

የሀገሪቱን የደን ይዞታ በማሻሻል ረገድ የኅብረተሰቡ ግንዛቡ ከበፊቱ አሁን የተሻለ እንደሆነ፤ በመንግሥት በኩልም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማቋቋምን ጨምሮ የተሻሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸዉን ነዉ አቶ ጢዳ የገለፁልን። ደንን ያለአግባብ የሚያጠፋ የሚዳኝበት ጥሩ ሕግ መኖሩን፤ ግን ደግሞ አፈጻጸሙ ላይ አሁንም ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል። ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በተገናኘም የእርሻ ቦታ፤ እንዲሁም የማገዶ ፍላጎቱ ከፍ ማለቱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ