1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ኬንያ መሰደዱ አልቆመም

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2010

ከኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ህዝቡ ዛሬም ወደ ኬንያ መሰደድ መቀጠሉን የዓይን ምስክር ለዶቼቬለ ተናገሩ። እኚሁ የአካባቢው ነዋሪ በሞያሌ ከተማ  ትናንት ማታ አንድ ሰው ሞቶ መገኘቱን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2uKWd
Äthiopien vertriebene Moyale-Bewohner in der Oromia-Region
ምስል privat

ከሞያሌ መሰደዱ ቀጥሏል

ባለፈው ቅዳሜ በመከላከያ ሠራዊት ጥቃት 10 ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉባት እና 12 የቆሰሉባት የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬም ወደ ኬንያ መሰደዳቸው መቀጠሉ ተገልጿል። ሰዎቹ የሚሰደዱት ደግሞ ከሞያሌ ከተማ ብቻ ሳይሆን ከገጠር ቀበሌዎች ጭምር መሆኑን አንድ የዓይን ምስክር ለዶቼቬለ ተናግረዋል። እንደ ዓይን ምስክሩ ከሞያሌ የተሰደደው ህዝብ ቁጥር ብዙ ነው። ወደ ኬንያ የሚሰደዱትም በተለያዩ አቅጣጫዎች ነው።
«ሞያሌ ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት የለም። ሰዉ በጣም እየተሰደደ ነው። ዛሬም ማታ አካባቢም እየወጣ ነው። ከገጠር ቀበሌዎችም የተሰደዱ አሉ። አሁን ራሱ እዛ ሄጄ ነው የመጣሁት። ብዙ ህዝብ ነው እዛ ተሰዶ ያለው። በተለይ ህጻናት እና ሴቶች ሽምግሌዎች ብዙ ናቸው ተሰደው እዛ ያሉት።» 
ስደተኞቹ ያሉበት ቦታ ደርሰው መመለሳቸውን የተናገሩት እኚሁ የዓይን ምስክር ወደ ኬንያ ተሰዷል የሚሉት ነዋሪ ቁጥር በርሳቸው ግምት እስከ 50 ሺህ ይደርሳል። ዶቼቬለ ትናንት ያነጋገራቸው የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበር ተጠሪ አባስ ጉሌት ግን ቁጥሩ ምናልባት ማምሻውን እስከ 6 ሺህ ይድረስ አይድረስ እናያለን ሲሉ፣ ብዙ ሰዎች ወደ ኬንያ እየመጡ ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ሞያሌ ፣ኬንያ ከገቡት ስደተኞች ያገኙት መረጃ ጠቅሰው ተናግረው ነበር። ሚስተር ጉሌት እንደሚሉት ስደተኞች አሁን ኬንያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ነው የሚገኙት። በተለይ በአንድ አካባቢ ቁጥራቸው በጣም እየጨመረ ነው። 
«ስደተኞቹ በሶሎሎ ንኡስ ወረዳ 3 ቦታዎች ነው የሚገኙት። በሞያሌ ደግሞ በ4 ቦታዎች ነው ያሉት።ስለዚህ ድንበር አቋርጠው ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ነው የሚመጡት። በኬንያም ኬንያ ሞያሌ ከገቡት ይልቅ በሶሎሎ ገጠር አካባቢዎች የሚገቡት ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው።»
በሌላ በኩል ከተማዋ አለመረጋጋትዋን የሚናገሩት የዓይን ምስክር ትናንት ማታ አንድ ሰው ተገድሎ ተገኝቷል ብለዋል። ይህም ነዋሪዎችን ፍርሀት ውስጥ መክተቱን ገልጸዋል። 
«ትናንት እና ማታም ሰው ሞቶ ነው የተገኘው። መነኻሪያ አካባቢ ነው። ማን እንደገደለው አይታወቅም። ማታ ሰው እየሞተ ነው። ሰዉ በጣም ፈርቶ ነው የሚሰደደው። ባለፈውም ሞቷል። እሱንም እኛ ነን የቀበርነው። አንቀው እየገደሉ ነው ያሉት በቃ አይታወቅም።»
በአሁኑ ጊዜ በሞያሌ ከተማ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት እንደሚገኝ አልፎ አልፎም ሰዎች እንደሚታሰሩ የዓይን ምስክሩ ተናግረዋል። ህዝቡ በከተማዋ ባለፈው ቅዳሜ እና ከዚህ ቀደምም የንፁሀንን ህይወት ያጠፉ ለፍርድ ይቀርቡ የሚል ጥያቄ አቅርቧል። ወደ ኬንያ የተሰደዱትም ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት አንድ ቅድመ ሁኔታ ሲሟላ መሆኑን ተናግረዋል እንደ ዓይን ምስክሩ።
«ኮማንድ ፖስቱ ከተነሳ ነው እኛ የምንመለሰው ነው የሚሉት ሰዎቹ። ሰዉ እነሱን ካየ ይሸሻል። እነርሱ ደግሞ 3 ሆነew አራት ሆነው ውስጥ ለውስጥ ይሄዳሉ። ማታ አካባቢ አሥራ ሁለት አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ። ሰዉ ደግሞ ህዳናቱ እነርሱን ካዩ ይሸሻሉ።ወይ ወደ ግቢ ይገባሉ።ወይም ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ።»
ኬንያ ለተሰደዱት የኢትዮጵያ ሞያሌ ነዋሪዎች የኬንያ ቀይ መስቀል በራሱ ተነሳሽነት በሰብዓዊነት  ምግብ እያቀረበ መሆኑን ሃላፊው ጉሌት ለዶቼቬለ ተናግረዋል። የሞያሌው ነዋሪ ግን ሰዎቹ ለልዩ ልዩ ችግሮች መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
«በጣም ችግር ውስጥ ነው ያሉት።ህጻናት ይበዛሉ። ሴቶች ይበዛሉ።የሚበላ ነገር የለም። ውሐ ራሱ የለም። የውሐ እጥረት አለ። ማደሪያ ራሱ የለም። ትምሕርት ቤት ውስጥ ነው ያሉት። በጣም ችግር ውስጥ ነው ያሉት።»
ካለፈው ቅዳሜ አንስቶ ወደ ኬንያ ስለ ሚሰደዱት የሞያሌ ነዋሪዎችም ሆነ ትናንት ሞቶ ተገኝቷል ስለተባለው ሰው ጉዳይ የሞያሌ ከተማ  ከንቲባን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ልናገኛቸው አልቻልንም።

Äthiopien vertriebene Moyale-Bewohner in der Oromia-Region
ምስል privat

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ