1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራቡ ዴሞክራሲ እና  ቀኝ ፅንፈኞች

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ መስከረም 15 2010

የትናንቱ የጀርመን ምርጫ የኮንራድ አደናወር፤ የሔልሙት ኮል እና የአንጌላ ሜርክሉ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ CDU ዝቅተኛ ዉጤት ያገኘበት፤ እነ የቪሊ ብራንት፤እነ ሔልሙት ሽሚት እና እነ ጌርሐርድ ሽሮደሩ የበቀሉ፤ የመሩ እና ሐገር ሕዝባቸዉን ያሳደጉበት የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (SPD) ከፍተኛ ሽንፈት የተከናነበት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2kgIr
Bundestagswahl | Elefantenrunde Gruppenbild
ምስል picture alliance/dpa/G. Breloer

የምዕራቡ ዴሞክራሲ እና ቀኝ ፅንፈኞች

የብሪታን ቀኝ አክራሪዎች ታላቅ ሐገራቸዉን ከታላቁ ሕብረት ነጥለዉ፤ በፀረ ስደተኛ ጎዳና፤ ምናልባት ስኮትላንድን በማስገንጠል ጠርዝ ለትንሽነቷ ሲያካልቧት፤ የዩናይትድ ሕዝብ ቀኝ ፅንፈኛዉን ነጋዴ ዶናልድ ትራምፕን መሪዉ አድርጎ በመምረጡ የዓለም መሪዋን ሐገር ከቲዊተር አጣብቀዉ ከዓለም ለመነጠል እያስጋለባት ነዉ።የፈረንሳይና የሆላንድ ምርጫ ዉጤት ፓሪስ እና ዘሔግን እንደ ለንደን እና ዋሽግተን በቀኝ አክራሪዎች ከመማረክ  ቢያድንም የአክራሪዎቹን ሥጋት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አልቻለም።ትናንት ጀርመን በተደረገዉ የምክር ቤት አባላት ምርጫ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራያዊ ሕብረት (CDU) የመሪነቱን ቦታ አስከብሯል።አማራጭ ለጀርመን (AFD በምሕፃሩ) የተሰኘዉ ቀኝ ፅንፈኛ የፖለቲካ ማሕበር ያገኘዉ ከፍተኛ ድጋፍ ግን ጀርመን ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ አይታዉ የማታዉቀዉ አይነት ነዉ።የጀርመን ምርጫ ዉጤትን ከምዕራቡ ዴሞክራሲ የቀኝ ጉዞ ጋር አሰባጥረን እንቃኛለን ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

                                 

የዋና አስተማሪዋ እንደ ብዙዎቹ የክፍሏ ልጆች ሁሉ ከማማዉ ላይ እንድትዘል ጠየቋት።ማማዉ ላይ ወጣች።ቁል ቁል ኩሬዉን አየች።ለረጅም ጊዜ ቆመች።አልዘለለችም።በወጣችበት መሰላል ተመልሳ ወረች።«ምነዉ» ጠየቋት  አስተማሪዋ።«እርግጠኛ አይደለሁም።» መለሰች የ12 ዓመቷ አንጌላ።በቀጣዩ የዋና (የስፖርት) ክፍለ ጊዜ ከባልጀሮቿ ተሽቀዳድማ ማማዉ ላይ ወጣች።እርግጠኛ ሆናለች ማለት ነዉ።ወደ ዉሐዉ ተወረወረች።ወሰነች ማለት።

የጠንካራዉን ወግ አጥባቂ የመሐል-ቀኝ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት (CDU)ን የመሪነት ሥልጣን የያዙት በ2000 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።እንደ ፖለቲካዉ ወግ በ2002 በተደረገዉ ምርጫ ፓርቲያቸዉን ወክለዉ ለመራሔ መንግስትነት መወዳደር ነበረባቸዉ።ይሁንና እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ሥላልነበሩ-አንድ፤የፓርቲዉን ነባር ፖለቲከኞች ከጠንካራዉ መርሔ-መንግሥት ከጌርሐድር ሽሩደር ጋር አላትመዉ ለማሳጣት-ሁለት፤በወንዶች  በጣሙን ከምዕራብ በተጠራቀሙት ወንድ ፖለቲከኞች ዘንድ ያላቸዉን ዝቅተኛ ተቀባይነት አስልተዉ-ሰዎስት፤ ለመራሔ መንግስትነቱ ሳይወዳደሩ አሩ።

Deutschland Bundestagswahl | Elefantenrunde
ምስል picture-alliance/dpa/G. Breloer

የCDU እሕት ፓርቲ የምትባለዉ የክርስቲያን ሶሻሊስት ሕብረት (CSU) መሪ ኤድሙድ ሽቶይበር ለመራሔ መንግስትነት ተወዳድረዉ የተጠበቀዉን ሽንፈት ተጎናፅፉ።የሜርክል ባንድ ድንጋይ ሰወስት ወፍ የመግደል ሥሌት ግቡን መታ።ከ2005 ጀምሮ ጀርመንን የመሩት አንጌላ ሜርክል በጀርመኖች ዘንድ «ሙቲ» (እማማ እንደማለት ነዉ) በዉጪዉ የፖለቲካ ተንታኝ ዘንድ የአዉሮጳ ሕብረት ተዘዋዋሪ መሪ የሚል ሙገሳ-አድናቆ አትርፈዋል።

በትናንቱ ምርጫም መሪነታቸዉን እንዳስከበሩ እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ እንደሚለዉ ግን የሜርክል ፖለቲካዊ ጡንቻ የእስካዛሬዉ ዓይነት ጥንካሬ አይኖረዉም።

                              

የቀድሞዋ ምዕራብ ጀርመን የመጀመሪያ መራሔ-መንግሥት ኮንራድ አደናወር ከዘግናኙ ጦርነት ለሁለት ተገምሳ የተረፈችዉ ምዕራብ ጀርመን ተሰሚነት እንዲኖራት ማስላት፤መናገር፤መከራከር የጀመሩት  መንግሥት ባቆሙ ማግስት ነበር።በ1949።

ያኔ እሁለት የተገመሰችዉ ጀርመን የጦርነት ትቢያዋን በቅጡ አላራገፈችም።እሁለት ከገመሷት የኮሚኒስት ካፒታሊስት ተቀናቃኝ ኃያላን መንግስታት ቁጥጥር ገና ነፃ  አልወጣችም።የናዚ ቅሪቶች ከፀረ-ናዚዎቹ ፖለቲከኞች አልተለዩም።ሌላ ቀርቶ አደናወር ቦን ላይ የመሠረቱት ቅኝ ዘመሙ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት (CDU) መንግሥት በሁለት እግሩ አልረገጠም።በዚሕ መሐል ሽማግሌዉ ፖለቲከኛ «ጭቅላ» ሐገራቸዉን ከፍከፍ ለማድረግ መሞከር መጣራቸዉ ከዉጪም ከዉስጥም «አቅሙን አያዉቅ» ለሚል ዓይነት ትችት ዳርጓቸዉ ነበር።

የወቀሳ-ትችቱ  ነበልባል በ1951 «ለብለብ» ሲያደርጋቸዉ እዉቅ የሚሏቸዉን ግን በቅርብ የሚያዉቋቸዉን ጋዜጠኞች «ሻሒ እንጠጣ ብለዉ ጋበዟቸዉ» ይላሉ የሕይወት ታሪካቸዉ ፀኃፊ ሐንስ ፔተር ሽቫርዝ።

«ዳግም ታላቅ መንግሥት መሆን ከፈለግሁ» አሉ አደናወር ለጋዜጠኞቹ «እኛ ጀርመኖች ደግሞ ይሕን ማድረግ ይገባናልም» አከሉ ሻሒያቸዉን እየማጉ «ሥለዚሕ ካሁኑ እንደ ታላቅ መንግሥት እራሴን ማቅረብ አለብኝ» እቅጩን አፈረጡት።

የሽማግሌዉ ሩጫ አልተገታም።ሌሎችም ይከተሏቸዉ ገቡ።ጀርመን በተለይ ምዕራቡ ከዩናይትድ ስቴትስ፤ ከብሪታንያና ከፈረንሳይ ቀጥታ ተፅዕኖ ባጭር ጊዜ ተላቀቀች።ምጣኔ ሐብቷ ዓለምን ባስደነቀ ፍጥነት አደገ።ቀዝቃዛዉ ጦርነት በርሊን ላይ ተጀምሮ የበርሊን ግንብ ሲደረመስ አበቃ።ጀርመን ዛሬ የዓለም አራተኛ፤ የአዉሮጳ አንደኛ ሐብታም ሐገር ናት።ለአዉሮጳ ሕብረት ከፍተኛዉን በጀት የምትቆርጥ፤ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዩናይትድ ስቴትስና ከጃፓን ቀጥሎ ሰወስተኛዉን ከፍተኛ ወጪ የምትሸፍን ሐገር ናት።

Bundestagswahl 2017 | AfD Symbolbild
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

በቅርቡ የተመሠረተዉ የቀኝ ፅንፈኞቹ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ (AFD) መሪ አሌክሳንደር ጋዉላንድ ትናንት እንዳሉት ግን ሐገር እና  ሕዝባችዉን ተቀምተዋል።

                 

“ወዳጆቼ ሆይ! በምክር ቤት ውስጥ ሶስተኛው ጠንካራ ፓርቲ እንሆናለን፡፡ቀጣዩ መንግስት በደንብ ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት፡፡ ወይዘሮ ሜርክልንም ሆነ ማንኛውንም ከመታገል አንመለስም፡፡ ሀገራችን እና ሕዝባችንን መልሰን እንረከባለን።”

የትናንቱ ምርጫ ጀርመን ከ1949 ጀምሮ የተጓዘችበትን ታሪክ የቀየረ ነዉ።የኮንራድ አደናወር፤ የሔልሙት ኮል እና የአንጌላ ሜርክሉ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ CDU ዝቅተኛ ዉጤት ያገኘበት፤ እነ የቪሊ ብራንት፤እነ ሔልሙት ሽሚት እና እነ ጌርሐርድ ሽሮደሩ የበቀሉ፤ የመሩ እና ሐገር ሕዝባቸዉን ያሳደጉበት የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (SPD) ከፍተኛ ሽንፈት የተከናነበት ነዉ።

እርግጥ ነዉ ሁለቱ አንጋፋ ፓርቲዎች አሁንም የመጀመሪያና የሁለተኛነቱን ደረጃ እንደያዙ ነዉ።ግን ሁለቱ ትላልቅ ፓርቲዎችም ሆኑ አጋሮቻቸዉ ስደተኛን ለሚጠላዉ፤ የጋራ ስምምነቶችን ለሚቃወመዉ፤ የአዉሮጳ ሕብረትን ለሚንቀዉ፤ ፓርቲ ለAFD ዘጠና አራቱን የምክር ቤት መቀመጫ መልቀቅ ግድ ነበረባቸዉ።

ዶናልድ ትራምፕ ዋሽግተን ላይ «አሜሪካ ትቅደም» ሲሉ፤ ኔግል ፋራጅ ለንደን ላይ የለኮሱት የቀኝ ፅንፈኞች አስተሳሰብ ብሪታንያን ከትልቁ የአዉሮጳ ሕብረት አባልነት አግልሎ ምናልባት እስኮትላንድን ከብሪታንያ ለማስገንጠል ዳርዳር እያለ ነዉ።ፈረንሳይና ኔዘርላንድስ ዉስጥ የተጠናከሩት ቀኝ ፅንፈኞች እንደ ለንደን ዋሽግተኖች ድል አለማድረጋቸዉ ለነባሩ የምዕራብ ዴሞክራሲ እፎይታ ነዉ።

በትናንቱ የጀርመን ምርጫ ቀኝ ፅንፈኞች ማሸነፍ አይደለም ፈረንሳይና ኔዘርላንድስ ዉስጥ የነበራቸዉን ዓይነት ድጋፍ እንኳ አላገኙም።ያገኛሉ የሚል ግምትም አልነበረም።ያገኙት ዉጤት ግን ከምርጫዉ በፊት ከነበረዉ ግምት የበለጠ ነዉ።ለንደን እና ዋሽግተን ላይ ድል ያደረገዉ፤ፓርስ እና ዘሔግን ያሰጋዉ የቀኝ ፅንፈኞች ትንሳኤ በርሊንም መደገሙ የምዕራቡን ዴሞክራሲ ከስጋት ቅርቃር ከትቶታል።

Infografik BUWA 2017 Wahlergebnis EN Preliminary official results NEW!

                                  

ለቅኝ ፅንፈኞቹ ማንሰራራት ወይም የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘታቸዉ እንደምክንያት የሚጠቀሱት ብዙ ናቸዉ።የስደተኞች መብዛት፤የምጣኔ ሐብት ድቀት፤የሥራ አጡ መበራከት የነባሩ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ መዳከም፤የመገናኛ ዘዴዎች አስፈሪ ዘገባ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት ምክንያቶች ናቸዉ።

ነባሩን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እናራምዳለን የሚሉት ወይም እራሳቸዉ ዴሞክራት የሚሉት ኃይላት ለረጅም ጊዜ ያለመ ጥልቅ ፖለቲካዊ መርሕ የሚያራምድ ወይም ራዕይ ያለዉ መሪ ማጣታቸዉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ምናልባት የድክመቱ ሁሉ ዋና ድክመት ሳይሆን አይቅርም።እንዲያዉም አንጌላ ሜርክል ትናንት እንዳሉት ቀኝ ፅንፈኞቹ  በሕዝብ ዘንድ ያላቸዉን ተቀባይነት ለማሳጣት ነባር የሚባሉት ፖለቲከኞች ቀኝ ፅንፈኞቹ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ መስጠትን ዋና ሥልት ሳያደርጉት አልቀረም።

ለዘብተኛ ወይም ዴሞክራት የሚባሉት ነባር ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የቀኝ ፅንፈኞቹን ዓላማ ካራመዱ ከፅንፈኞቹ በምን ተለዩ ነዉ?።ነጋሽ መሐመድነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ