1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚሊዮኖቹ ተፈናቃዮች ዕጣ ፈንታ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2011

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እስከ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። ከተፈናቃዮች የተወሰኑት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንደተመለሱ ቢነገረም በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች መፈናቀሉ ቀጥሏል። አሁንም በመጠለያ ያሉ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቀናትን እየገፉ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/3B9uz
Äthiopien ethnische Minderheit der Gedio
ምስል DW/Shewngizaw Wegayehu Aramdie

የሚሊዮኖቹ ተፈናቃዮች ዕጣ ፈንታ

በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን ቆሎጂ መንደር ስር ባለ ቦታ በርካታ ሴቶች እና ህጻናት ይታያሉ። የተወሰኑቱ በአካባቢው ካለ ቧንቧ ውሃ ለመቅዳት ይሻማሉ። በስፍራው የሚታዩት ብዙዎቹ ሰዎች የአካባቢው ነዋሪዎች አይደሉም። የሶማሌ ተወላጆች የሆኑት በሺህዎች የሚቆጠሩት እነዚህ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው ወደ ቆሎጂ የመጡ ናቸው። ተፈናቃዮቹ በቆሎጂ ከኮረብታ ስፍራ ስር ባለ የተንጣለለ ሜዳ ላይ መጠለያዎችን ቀልሰዋል። ችምችም ብለው የተደረደሩት አብዛኞቹ ትናንንሽ መጠለያዎች በላስቲክ የተሰሩ ሲሆን የአካባቢውን ባህላዊ የቤት አሰራርም የተከተሉ ናቸው። 

በእንደዚህ አይነት መጠለያዎች በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩት ተፈናቃዮች ቁጥር 80 ሺህ እንደሚደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከተፈናቃዮቹ አንዷ ያሉበትን አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ እንዲህ ትገልጻለች። “ጥቃት ሲደርስብን ከብቶቻችን እና ሌሎችንም ነገር ትተን ነው የወጣነው። ባሎቻችን እና ልጆቻችንን አጥተናል። እዚህ ያለው የኑሯችን ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ምንም የለንም” ትላለች። 

Äthiopien Flüchtlinge vor ethnischer Gewalt
ምስል DW/J. Jeffrey

እንደ እርሷ ሁሉ ከቀያቸው የተፈናቀሉ አንድ ጎልማሳ በአካባቢያቸው በኦሮሞ እና ሶማሌ ማህበረሰቦች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ሰዎች መሞታቸውን ይናገራሉ። “በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል በነበረ ውጊያ ምክንያት አካባቢውን የለቀቅሁት የዛሬ ሁለት ዓመት ነው። የተወለድኩት በኦሮሚያ ሲሆን ቤተሰቦቼም በዚያ ለክፍለ ዘመናት ኖረዋል። ሁለት ወንድሞቼን እና ሁሉንም ከብቶቼን አጥቻለሁ” ሲሉ ለዩሮ ኒውስ ጣቢያ ባልደረቦች ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት የተፈናቃዮች ብሶት እና እሮሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተደጋግሞ የሚደመጥ ሆኗል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እዚህም እዚያም በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት ከተወለዱበት፣ ካደጉበት እና ለዓመታት ከኖሩበት ስፍራ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። የተፈናቃዮች ቁጥር ከሺህዎች ተሻግሮ እንደ ዋዛ ወደ ሚሊዮኖች አሻቅቧል። 

ከዓመት በፊት በሶማሌ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የተፈናቃዮቹ ቁጥር አንድ ሚሊዮን ገደማ መሆኑ ሲገለጽ ብዙዎችን አስደንግጧል። ለተፈናቃዮቹ እርዳታ ለማሰባሰብ እና በተለያዩ አካባቢዎች ለማስፈር ሰፊ እንቅስቃሴ ሲካሄድም ቆይቷል። የተወሰኑትንም ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስም ተሞክሮ ነበር። በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ይህ የሰብዓዊ ቀውስ ቁስሉ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠግግ ነበር በስተደቡብ አቅጣጫ በሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ያፈናቀለ ግጭት የፈነዳው። 

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌዶ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች በተቀሰቀሰው በዚህ ግጭት ከቀያቸው የሸሹ ሰዎች ብዛት ቀደም ሲል በሌሎች አካባቢዎች ከተከሰቱት ጋር ተዳምሮ የተፈናቃዮችን ቁጥር ወደ ሶስት ሚሊዮን አድርሶታል። ይህም ኢትዮጵያን በተፈናቃይ ብዛት በዓለም የመጀመሪያው ረድፍ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል። ምጸታዊው ጉዳይ ደግሞ በእርስ በእርስ ጦርነት በሚታመሱት ሶሪያ እና የመን ያሉት ተፈናቃዮች እንኳ በኢትዮጵያ ያሉትን ያህል አለመሆኑ ነው። 

Äthiopien Mitiku Kassa, the State Minister of Food Security
ምስል DW/Getachew Tedla

በኢትዮጵያ የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ የተፈናቃዩ ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው 2.8 ሚሊዮን ወደ 1.85 ሚሊዮን መቀነሱን ይናገራሉ። በለውጥ ጊዜ እንዲህ አይነት ችግሮች የሚጠበቁ ቢሆንም የተፈናቃዩ ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠር መሆኑ “አስደንጋጭ ነው” ይላሉ። ኢትዮጵያ ከሶሪያ እና የመን የተነጻጸረችበትን አካሄድን ከህዝብ ቁጥር አኳያ መመልከት እንደሚያሻም ያስረዳሉ።  

ኮሚሽነር ምትኩ የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ችግር ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል ይላሉ። ችግሩ ከስር መሰረቱ ለመፍታትም የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ኡጋዞች እና እናቶችን ያካተቱ የሰላም ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን እና ዘመቻዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ቢልም በሀገሪቱ እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተፈናቀሉት ባለፈው አንድ አመት ተኩል ባለው የጊዜ ወሰን ውስጥ መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ይበልጥ እንደሚያጎላው እና ወደ ሰብዓዊ ቀውስ የመለወጥ አዝማማሚያ እንዳለው የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲያስጠንቅቁ ቆይተዋል። 

ከብዙዎቹ መፈናቀሎች ጀርባ ያለው የብሔር ተኮር ግጭት ከመብረድ ይልቅ መልኩን እየቀያየረ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰት መቀጠሉም ብዙዎች መጪውን ጊዜ በስጋት እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ከኦሮሚያ እስከ ደቡብ፣ ከቤንሻንጉል እስከ ሶማሌ ባለፉት ወራት የተከሰቱ ግጭቶችም ስጋቱ ስጋት ብቻ እንዳልነበር በተጨባጭ አሳይተዋል። ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በኦሮሚያ ክልል እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን ሸሽተው በየመጠለያዎቹ የሰፈሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ መጨመሩን ከአካባቢው ባለስልጣናት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ግጭቱ በጠናበት በምዕራብ ወለጋ ዞን የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 34 ሺህ ገደማ የነበሩ ሲሆን አሁን ቁጥራቸው 94 ሺህ መድረሱን የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ተመስገን ይናገራሉ። ተፈናቃዩቹ በየጊዜው እርዳታ ቢያገኙም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ይገልጻሉ። 

Äthiopien ethnische Minderheit der Gedio
ምስል DW/Shewngizaw Wegayehu Aramdie

ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን እስካሁንም ተጠልለው ያሉ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ በዞኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግስቱ ገዛኸኝ ገልጸዋል። እንዲህ አይነት የእርዳታ አቅርቦት ማዋዠቅ የሚያጋጥመው በግጭት ምክንያት በየጊዜው የሚፈናቀለው ሰው ቁጥር ስለሚቀያየር እንደሆነ ኮሚሽነር ምትኩ ያስረዳሉ።  

ለተፈናቃዮች በየጊዜው እርዳታ ለማድረስ ሌላው እንቅፋት የሆነው በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር መሆኑን ሲገለጽ ቆይቷል። ካለፈው መስከረም ወዲህ በግጭት ውስጥ የሰነበተው የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪም ይህንን ያስተጋባሉ። የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት እርዳታ ለማቅረብ መቸገሩን ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ይገልጻሉ። ሆኖም ይህ ችግር በቅርቡ ይቃለላል የሚል ዕምነት አላቸው። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

አርያም ተክሌ