1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማብቂያ ያጣ ጦርነት

ሰኞ፣ ነሐሴ 28 2010

የሳዓዳዉ ጥፋት አነጋግሮ ሳያበቃ ምዕራባዊ የመን ዉስጥ በአዉቶብስ ይጓዙ የነበሩ ሰላሳ ሰላማዊ  ሰዎች በተባባሪዎቹ ሐገራት የአዉሮፕላን ጥቃት ተገደሉ።22ቱ ልጆች፤ አራቱ ሴቶች ነበር።አንድ የአካባቢዉ ባለሥልጣን እንዳሉት ሰዎቹ ከነአዉቶብሱ አመድ ነዉ የሆኑት።

https://p.dw.com/p/34EAv
Jemen Beerdigung von Opfern eines Luftangriffs in Saada
ምስል Reuters/N. Rahma

የመን፤ የእልቂት ምድር

ዩናይትድ ስቴትስ ከ2001 (ዘመኑ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ዓለምን አስከትላ በድፍን ዓለም የዘመተችበት አሸባሪ ቡድን አልቃኢዳ ባሁኑ ወቅት ጠንካራ ኃይል ያለዉ የመን ዉስጥ ነዉ።አልቃዳ በይፋ እንደሚታወቀዉ የዩናይትድ ስቴትስ፤የሳዑዲ አረቢያ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሌሎችም መንግሥታት «ጠላት» ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የሳዑዲ አረቢያ፤ የአረብ ኤሚሬቶች የቅርብ ደጋፊ፤አስታጣቂ፤ አማካሪም ናት።ሳዑዲ አረቢያ የአረብ፤የእስያና የአፍሪቃ መንግሥታትን አስከትላ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን የየመን አንሳር አላሕ ወይም የሁቲ አማፂያንን ትወጋለች።የመን የሸመቀዉ የዩናይትድ ስቴትስ ቀንደኛ ጠላት አል ቃኢዳ፤ ዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጅ ሳዑዲ አረቢያ ከምትመራዉ ጦር ጋር አብሮ ሁቲን ይወጋል።ወዳጅ እና ጠላት፤አሸናፊ እና ተሸናፊ፤ ማብቂያ እና መፍትሔ ያልየበት ጦርነት ሕፃን ከአዛዉንት፤ ሲቢል ከወታደር ሳይለይ ሺዎችን ይፈጃል።ለምን?

 የሳዑዲ አረቢያ መሥራች ንጉስ አብዱልአዚዝ አብድል ረሕማን ኢብን ፈይሰል አል-ሳዑድ «ግዛቴ» የሚሉትን አካባቢ የየመን ጦር ወረረዉ ማለትን ሲሰሙ «ንሳ» አሉ-አሉ የጦር አዛዣቸዉን «በላቸዉ» አከሉ።መጋቢት 1934 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።የያኔይቱን ደሐ፤ ሰፊ በረሐማ ሐገርን በአዲስ ዘዉዳዊ አስተዳደረዉ በማዋቀር ላይ የነበሩት የ59ኝ ዓመቱ ንጉስ ከሳባዉያን እስከ አዩቢዶች፤ ከቱርኮች እስከ እንግሊዞች የመን እየዘመቱ የመን እንደቀሩ  ሳያዉቁት አልቀረም።

Krebspatienten im Jemen
ምስል Reuters/K. Abdullah

ጦራቸዉን ባዘዙ በ3ኛ ሳምንቱ ግድም ባለሥልጣኖቻቸዉን ወደ ሰነዓ ላኩ።

ንጉስ አብዱልአዚዝ ለየመን (ሰሜን) ኢማም ለያሕያ መሐመድ ሐሚድ አ-ዲን የላኩት መልዕክት ጥቅል ይዘት በወንድማማቾች መካከል ብዙ ደም እንዳይፈስ መጠንቀቅ አለብን የሚል ነበር።ኢማም ያሕያ መልዕክቱ ሲደርሳቸዉ የሁለቱ ሐገራት ወታደሮች ጂዛን፤አሲር፤ናጅራት እና አል ሁዴይዳሕ ላይ ዉጊያ ገጥመዉ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ የየመን ኢማም ጦራቸዉን  ከሰወስቱ ትናንሽ ግዛቶች ለቅቆ እንዲወጣ ሲያዙ፤የሳዑዲ ንጉስ ደግሞ ጦራቸዉ አልሁዴይዳሕን ለየመኖች እንያስረከብ አዘዙ።ሁለቱም ዘየዱ።ጦርነቱም ቆመ።ሰኔ 1934።የፖለቲካ ተንታኝ እና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የመን «የዘመተባት የማይመለስባት ሐገር ናት ትባላላች።

 ቢን ሠልማን፤ቢን ዚያድ፤ አብዱረሕማን ረቦ መማር ቢፈልጉ ኖሮ የሩቆቹን የአዩቢድንን ዘዴ፤ የሐዲም ሱሌያማን ፓሻ ዘዴ፤ የስታፎርድን ስሕተት ለማጥነት ሳይደክሙ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸዉ ብልጠት፤ከነናስር ጥፋት ብዙ በተማሩ ነበር።አልፈለጉም።መጋቢት 2015 ጦር ሲያዘምቱ እኒያን ደሐ፤ወታደራዊ ሥልጠና፤ ትጥቅ፤ የሌላቸዉን ከቋጥኝ ቋጥኝ የሚዘሉ የሁቲ ሸማቂዎችን ከያሉበት መንጥሮ ለማዉጣት ከወራት በላይ ጊዜ አያስፈልግም ብለዉ ነበር።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲሕ አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ብቻ ከዩናይትድ ስቴትስ በ8 ቢሊዮን ዶላር፤ ከብሪታንያ በ3,8 ቢሊዮን ፓዉንድ በገፍ የሸመተችዉን ጄት፤ መድፍ፤ ቦምብ፤ሚሳዬል ደሐይቱ ሐገር እና ሕዝብ ላይ ዘርግፋዋለች።የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ ምርጥ ወታደራዊ አሰልጣኞች የሳዑዲ አረቢያ እና የተባባሪዎችዋን ወታደሮች ያሰልጥናሉ።የአሜሪካ ሰላዮች ለሳዑዲ አረቢያ እና ለተከታዮቿ መረጃ፤የአሜሪካ የጦር ባለሙያዎች ምክር፤ የአሜሪካ ጄቶች የአየር ላይ ነዳጅ ይሞላሉ።

Krebspatienten im Jemen
ምስል Reuters/K. Abdullah

መከላከያ ሚንስትር ጂም ማቲያስ መንግስታቸዉ በሚዝቀዉ ገንዘብ እንደሚደሰቱ ሑሉ ባደረገዉ ድጋፍም ይኩራራሉ።«የሰጠናቸዉ ሥልጠና እየጠቀመ ነዉ።አየር ላይ ያሉ ፓይለቶች (እንዲተኩሱ) ታዘዉ እንኳን የተሰጣቸዉን ተልዕኮ አደገኛነት ሲረዱ፤(ቦምቡን) የማይጥሉ አሉ።ሆስፒታሎች እና ትምሕርት ቤቶች አካባቢ ተኩስ እንዳይከፈት የሚከለክል መመሪያ እንዳለ አይተናል።»

እዉነቱ ግን ያዩ እና ያጠኑ እንደሚሉት ተቃራኒዉ ነዉ።በአሜሪካኖች የሚረዳ፤የሚሠለጥነዉ የተባባሪ ሐገራት ጦር ቦምብ ሚሳዬሉን ሠላማዊ ሕዝብ ላይ ያዝነበዋል።ከሰወስት ሳምንት በፊት ሰዓዳ ዉስጥ 52 ታዳጊ ወጣት ተማሪዎችን ከነአዉቶብሳቸዉ የጨፈለቀዉ የአሜሪካዉ መከላከያ ሚንስትር ሆስፒታል እና ትምሕርት ቤቶች አይነካም ያሉት ጦር ነዉ።በየመን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ሊዛ ግራንዴ የጦርነቱ ዘግናኝ ዉጤት ብለዉታል።

የሳዓዳዉ ጥፋት አነጋግሮ ሳያበቃ ምዕራባዊ የመን ዉስጥ በአዉቶብስ ይጓዙ የነበሩ ሰላሳ ሰላማዊ  ሰዎች በተባባሪዎቹ ሐገራት የአዉሮፕላን ጥቃት ተገደሉ።22ቱ ልጆች፤ አራቱ ሴቶች ነበር።አንድ የአካባቢዉ ባለሥልጣን እንዳሉት ሰዎቹ ከነአዉቶብሱ አመድ ነዉ የሆኑት።

 «ይሕ ጦርነት፤ ይሕ ወንጀል ሰዎችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ያለመ ነዉ።መኪናዉ ዉስጥ የነበሩት (ተጓዦች) በሙሉ አልቀዋል።ከአመድ በስተቀር የቀረ ምንም ነገር የለም።»

የሰወስት ዓመት ከመንፈቁ ድብደባ ከ10 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሕዝብ ፈጅቷል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩትን አካለ ጎደሎ አድርጓል።ሚሊዮኖችን ለረሐብ እና በሽታ አጋልጧል።ጥንታዊቱን ሐገር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እየለወጣት ነዉ።የተባባሪዎቹ ሐገራት ጦር  በቀጥታ ከሚያደርሰዉ ጥፋት በተጨማሪ የምግብ፤ የዉሐ፤ የሕክምና እና የመፀዳጃ አግልግሎት ተቋማትን በማዉደሙ ኮሌራ እና ረሐብ ሚሊዮኖችን እየፈጀ ነዉ።የጂዳዉ ወኪላችን ነቢዩ ሲራክ እንደሚለዉ ዕድል ቀንቷቸዉ ሳዑዲ አረቢያ የገቡ የመኖች ስለየመን የሚተርኩት ዘግናኝ ነዉ።

                                 

የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት አጥኚ ቡድን ባለፈዉ ሳምንት እንዳስታወቀዉ አብድረቦ መንሱር የሚመሩት የየመን መንግሥት፤ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ የሁቲ አማፂያንም የየመንን ሕዝብ እየፈጁት ነዉ።የአጥኚዉ ቡድን ተወካይ እንዳሉት የየመንግሥቱ እና የቡድኑ አባላት የጦር ወንጀል ሳይፈፅሙ አይቅርም።«በየመን መንግሥት እና ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ የተባባሪዎቹ ሐገራት መንግሥታት ባለሥልጣንት (ግለሰቦች) (የጦር ዒላማዎችን) ከሌላዉ የመለየት፤የኃይል ተመጣጣኝነትን፤እና የጥንቃቄ መርሆችን ጥሰዉ ጥቃት አድርሰዋል።ይሕ ከጦር ወንጀልኝነት እኩል ሊቆጠር ይችላል።»

Jemen Beerdigung von Opfern eines Luftangriffs in Saada
ምስል Reuters/N. Rahma

የሪያድ እና የአቡዳቢ ገዢዎች በሰወስት ወር ሊያጠናቅቁት የፎከሩት ጦርነት በሰወስት ዓመት ከመንፈቁም የድል ጭላንጭል አላዩም።የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ደግሞ አንድም ሁነኛ ከተማ እንኳን አልተቆጣጠሩም።

                              

የየመን በተለይ የአደን ዉበት፤ ሐብት እና  ሥልታዊነት ያማለላቸዉ የብሪታንያ ቅኝ ገኝ ገዢዎች በ1839 ካፒቴን ስታፎርድ ቤትስዎርዝ ሐይነስ የሚመሩት ባሕር ኃይል አካባቢዉን እንዲቆጣጠር አዘመቱ።ለዘመኑ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀዉ የሐይንስ ጦር መናኛ መሳሪያ የታጠቁትን የአካባቢዉን የጎሳ ታጣቂዎች ባፍታ እንደሚደፈልቅ ዝቶ አደን እና መዳራሻዎችዋን ይቀጠቅጥ ያዘ።

ብዙ የመን አለቀ።እንግሊዞች ግን አላሸነፉም።ለጎሳ መሪዎቹ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከፍለዉ ድርድር ተቀመጡ።ሽምግልና።የሪያድ እና የአቡዳቢ ገዢዎች በጦርነቱ እንደማያሸንፉ በትክክል ሲያዉቁ ግን  በዓለም አቀፍ አሸባሪነት የሚያወግዙትን አልቃኢዳን ሳይቀር በተዘዋዋሪ ከጎናቸዉ አሰለፉ።

በአብዛኛዉ ደቡባዊ የመን ዉስጥ የሰፈሩት የአልቃኢዳ ሸማቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ከሚታዘዘዉ ከአብድረቦ መንሱር ሐዲ መንግሥት ጦር ጋር ተባብረዉ የሁቲ አማፂያንን እየወጉ ነዉ።ከአስር ቀን በፊት ማሪብ በተባለችዉ ግዛት ከየመን መንግስት ጦር ጎን  ሆኖ ሁቲዎች ይወጋ የነበረዉ የአልቃኢዳ ሚሊሺያ  አዛዥ ጋሊብ አል ዛይዲ ተገድሏል።

አል ዛይዲ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2017 የመን ዉስጥ የሸመቀ የአልቃኢዳ ቡድን አዛዥ ነዉ በሚል ማዕቀብ የጣለበት ሸማቂ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ጂም ማቲያስ እንደሚሉት መንግሥታቸዉ በየመኑ ጦርነት አይሳተፍም።ግን ለሳዑዲ አረቢያ እና ለተከታዮችዋ የሚሰጠዉን የጦር ድጋፍ አያቋርጥም።ደሞም አልቂዳን ይዋጋል።

                                               

«በጥቅሉ እኛ በየመኑ ጦርነት አንገባም።እኛ የምናተኩረዉ በአረብ  ልሳነ ምድር ISIS እና  አልቃኢዳን በማሸነፍ ላይ ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስ አልቃኢዳን ትወጋለች።ሳዑዲ አረቢያ እና ተባባሪዎችዋን ታስታጥቃለች።ሳዑዲ አረቢያ እና ተባባሪዎችዋ የአብድረቦን መንግሥት ጦር ያስታጥቃሉ፤የአብድረቦ መንግሥት ጦር አልቃኢዳን ያስታጥቃል።ሁቲዎች አልቃኢዳን ይወጋሉ።ግራ አጋቢ ትብብር።ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግራ አጋቢዉ ትብብር ቀይ ባሕርን ተሻግሮ አፍሪቃም ቀድም ደርሷል።

Jemen Meerenge Bab al-Mandab
ምስል Getty Images/AFP/S. Al-Obeidi

                                   

ግራ አጋቢዉ፤ አሳሳቢዉ ትብብር፤ አሳዛኙ ጦርነትም እንደቀጠለ ነዉ።በገፍ የሚዛቀዉ የነዳጅ ዘይት ዶላር፤የአሜሪካኖች ረቂቅ ምክር፤ ምርጥ ጦር መሳሪያም ቱጃሪቱን አረባዊት ሐገር በጦርነቱ ጢስ ጠለስ ከማስነጠስ አላዳናትም።

                                

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጥኚ ቡድን ባልደረባ እንደሚሉት የየመኑ ጦርነት ባጭር ጊዜ ይቆማል የሚል ተስፋ የለም።በቡድኑ ባልደረባ አገላለፅ ከዋሻዉ ማዶ የሚታይ ብርሐን የለም።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ