1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መናር እና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ችግር በኢትዮጵያ 

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 28 2010

በኢትዮጵያ በተለይም በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታየው የሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት እንዳማረራቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መንግስት ከወሰደው የ15 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በገበያው ላይ የሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶችና አለመረጋጋቶች ሊኖሩ ቢችሉም ችግሩ ከቀጥጥራችን ውጭ አይደለም ይላል።

https://p.dw.com/p/2qRYV
Äthiopien Market in Mekele
ምስል DW/Y. G. Egziabher

የዋጋ ንረት

ገዥው ኢሕአዴግ 11 በመቶ የምጣኔ ሃብት ዕድገት አስመዝግበናል ህዝባችንም በቀን 3 ጊዜ በልቶ የሚያድርበት ስልት ነድፈናል የሚል መግለጫ ቢያስተጋባም ዛሬም ሃገሪቱ ከችግር አዙሪት ቀለበት ውስጥ አለመውጣቷ ነው የሚነገረው። የተፋጠነ እድገት ለማስመዝገብ እና የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ምንም እንኳ መንግስት አንዳንድ የልማት እንቅስቃሴዎችን ቢያከናውንም ሙሰኝነት ብልሹ አስተዳደር የአቅም ማነስ እና የስራ አፈጻጸም ችግሮች የሸቀጦች ዋጋ መናር እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡ ድክመት ከህብረተሰቡ ወርሃዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ እና አሁን ከሚታየው የኑሮ ውድነት ጋር አለመጣጣሙ ጋር ተደማምሮ ቅሬታ እና ብሶትን ማስከተሉ አልቀረም ::

በኢትዮጵያ የሸቀጦች ምርት ብቻ ሳይሆን የትራንስፖርት የህክምና የቦታ እና የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ እና ግዥ እንዲሁም የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎቱም የዋጋ ንረት ከሌሎች በማደግ ላይ ያሉ የአፍሪካ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር አሳሳቢ መሆኑ ነው የሚጠቀሰው። ገንዘባችንም ቢሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙ እየደከመ ሄዷል።  ኑሮ እጅግ ከመጠን በላይ ከብዷል:: እናም አስቸኳይ መፍትሄ እና አንድ እልባት ሊበጅለት ይገባል ይላሉ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጭዎች።

Äthiopien Bewohner von Addis Abeba
ምስል Imago/Schreyer

የኑሮ ውድነት ጧት እና ማታ የሚንጠው ማህበረሰባችን ቦግ እልም እያለ በፈረቃ በሚዳረሰው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ሥርጭቱም ላይ ቅሬታ አለው :: በተለይም ህዝባዊ ተቃውሞዎች በተቀሰቀሱ ቁጥር ወትሮውንም ዝቅተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎቱ ጨርሶ ለቀናት እና ለወራት ደጋግሞ የመቋረጡ ጉዳይ ያስተዳድረኛል በሚለው መንግስት ላይ ቅሬታን ቢፈጥር የሚፈረድበት አይሆንም :: በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የድህረ ፈቃድ ኢኒስፔክሽን እና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በየነ ግን በቅርቡ መንግስት ከወሰደው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በአገልግሎት አሰጣጡ እና በገበያው ላይ የሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶች እና አለመረጋጋቶች ሊኖሩ ይችላሉ :: ያም ቢሆን ግን ችግሩ ከቀጥጥራችን ውጭ አይደለም በተቻለ መጠን ገበያውን ለማረጋጋት እየሰራን ነው ይላሉ።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሠ