1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሪዎቹ ጉብኝት፣ የብሔር ተኮር ዉጥረት፣ አነጋጋሪዎቹ ሹመቶች

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2011

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የሶማሊያ አቻቸዉ መሐመድ አብዱላሒ እና አስተናጋጃቸዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የአማራ መስተዳድርን ለመጎብኘት ዛሬ ጠዋት ጎንደር ከተማ ገብተዋል።

https://p.dw.com/p/37yZz
Äthiopien President Somalia Mohammed Abdulahi, Eritreas Präsident Isayas Afeworki, Äthiopiens Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

የመሪዎቹ ጉብኝት፣ የብሄር ተኮር ዉጥረት፣ አነጋጋሪዎቹ ሹመቶች

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የሶማሊያ አቻቸዉ መሐመድ አብዱላሒ እና አስተናጋጃቸዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የአማራ መስተዳድርን ለመጎብኘት ዛሬ ጠዋት ጎንደር ከተማ ገብተዋል። ሶስቱ መሪዎች ጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ የአማራ ርዕሠ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ አቀባበል አድርገዉላቸዋል።

የሦስቱ ሀገራት መሪዎች እስከ ማርፈጃዉ ድረስ ጎንደር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን ጎብኝተዉ ለተመሳሳይ ጉብኝት ወደ ባሕርዳር ተጉዘዋል። የአገር ዉስጥ የመገናኛ ዘዴዎች ዘገባ እንደሚያመለክተዉ ከሆነ የጉብኝቱ ዓላማ ሶስቱ መሪዎች ባለፈዉ መስከረም አስመራ ዉስጥ ያደረጉት የሶስትዮሽ ዉይይትን ለማጠናከር ነዉ። በጉብኝቱ ወቅት የሚደረጉት ዉይይቶች ዋና ዐብይ ርዕሥም ሆነ፤ የሚደረግ ሥምምነት ስለመኖር አለመኖሩ ይህ ዘገባ ለአየር እስክ በቃበት ድረስ በይፋ የተባለ ጉዳይ የለም።
ይሄን ጉዳይ ለፌስቡክ ተከታታዮቻችን አጋርተን ነበር። እነሱም የተሰማቸዉን ገልፀዋል። ዘበነ ተጫነ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ስለ አፍሪቃ ቀንድ ሰላምና እድገት ላይ ለመወያየት ስለተገናኛችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ» ብሏቸዋል። ፋንታዉን አወቀም በDW ፌስቡክ ላይ «የሀገር ደህንነት ቅድሚያ ይሰጥ። ሆደ ሠፊ መሆን አያዋጣም። ጓዳችን ለሁሉም ክፍት መሆን የለበትምና» ብለዋል።

በኢንቴርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የአፍሪቃ ቀንድ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ራሺድ አብዲ በትዊተር ገጻቸው ላይ የሚከተለዉን አስተያየት ፅፈዋል። «ሶስቱም የአፍሪቃ ቀንድ አገራት አዲስ የኢኮኖሚክ ትብብር ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የትብብሩ ዝርዝሮች ምን እንደሚመስሉ ግልፅ አይደለም። እንዲሁም የትብብሩ ተግባራዊ ለዉጥ አስመልክቶም በርካታ አሻሚ ጉዳዮች አሉበት። ዛሬ ይህ የበለጠ ግልጽ ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። ጂቡቲ በመጀመሪያ የፕሮጀክቱ አካል እንደነበረች ራሺድ ገልፀዉ ጂቡቲ በዚህ ስብሰባ ላይ አለመገኘቷን ማስታወስ እንደሚያስፈልግም አክሎበታል።

ይሕን ጉዳይ አስመልክቶ ከጉብኝቱ ይዘት ይልቅ የሦስቱንም ሐገር መርዎች የአቀባበል ስረዓትና በተለያዩ ቦታዎች ያደረጉትን ጉብኝት የሚያሳይ የማህባራዊ መገናኛ ዘዴዎች ገፆችን ተቆጣጥሮት ነበር። ምስሎቹን በማስመልከት ብሩክ ብሩክ የሚል የፌስቡክ ስም የያዙ ግለሰብ «መሪዎቹ በዚህ መልኩ ህዝባቸውን ሲመስሉ ይህ የአፍሪካ ቀንድ ህዝብ አይቶ ሚያውቅ አይመስለኝም በታሪኩ» ብለዋል። «ግንብ ከሚገንባ መሪ ይልቅ ድልድይ የሚገንባ መሪ በማግኘታችን በጣም ደሰተኞ ነን። ኢትዮጵያ የሚገባትን መሪ አሁን ያገኘች ይመስለኛል። እኛም ከጀርባህ ነን፣ ክቡርነተዎ» ያለዉ የነዉ ዘገየ አስተያየቱን በምስጋና ደምድመዋል። ተክሌ ሞገስ የተባሉ ግለሰብ ደግሞ «የአፍሪካ ቀንድ መሪዎች የጫጉላ ሽርሽር:- ኢትዮጵያ - ሶማሊያ - ኤርትራ» በማለት ቀልድ ያዘለ አስተያየት ፅፈዋል። በማህባራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚዟዟሩትን የመሪዎቹን ምስል በማስመልከት ሸወግ አሀመድ «ምስሉ ጥቅሙ ለፕሮፖጋንዳ ብቻ ነዉ። የዉስጥ ችግራቸዉን መጀመርያ መፍትሔ ፈልጉለት። መጀመርያ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በብሔር ግጭት ምክንያት ከቀየቸዉ እየተፈናቀሉ ይገኛሉ። በአንድ ግለሰብ ጨቋኝ አገዛዝ ምክንያት ኤርትራኖች አገራቸዉን ጥለዉ እየተሰደዱ ነዉ። ሶማሌዎች ለአመታቶች በእርስ በእርስ ጦርነት ዉስጥ ናቸዉ።

///////////

ሰሞኑን ብሄር ተኮር ግጭቶች፣ የደህንነት ዉጥረት፣ ተቃዎሞዎ በኢትዮጵያ ዉስጥ በአራቱም አቅጣጫዎች በተለያዩ ቦታዎች እየታየ ይገኛል። በአማራ ክልል መተማ ከተማ በሚኖሩ በአማራ እና በትግራይ ተወላጆች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል። የትግራይ መስተዳድር ግጭቱን አስመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ «አንዳንድ» እና «ከፍተኛ» ያላቸዉን የአማራ መስተዳድር ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አድርጓል። ለፍርድ እንዲቀርቡ አሳስቧልም። እዚያዉ ምዕራብ ጎንደር ሸንፋ በተባለችዉ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖሩ የአማራ እና የቅማንት ብሔረሰብ አባላትም ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ሲጋጩ እንደ ነበረ ይታወሳል። በግጭቱ ሰዉ ሞቷል፤ ሐብት ንብረት ወድሟልም። 

ይሕን በማስመልከት አበቡ ረሺድ በፌስቡክ ገጿ ላይ የሚከተለዉን አስተያየት አጋርታለች፣ «በአማራ እና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት አመራሮች መካከል ያለው ልዩነት እና መቃቃር ብሎም ያለመግባባት ወደ ህዝብ ለማውረድ በሁለቱም በኩል እያደረጉ ካሉት ድርጊት ሊቆጠቡ ይገባል። የአማራ ክልል በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦችን ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ብሎም ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የማድረግ ግዴታውን ያለምንም ማወላወል ሊወጣ ይገባል። በክልሉ የሚታየውን ስርዓተ አልበኝነት ሊያስቆም ይገባል። የትግራይ ክልል የማስራሪያ ይዘት ያለውን መግለጫ ማውጣቱንም ቢሆን ሊያቆም ይገባል። በመነጋገር እና በመወያየት እንጂ በማስፈራሪያ የሚለወጥ ነገር አይኖርም።»

«በአማራ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለውን የቃላት ጦርነት የዐብይ መንግሥት በዝምታ ለምን ተመለከተው?» ሲል የሰሜን ወፍ አበባዉ የሚል የፌስቡክ ስም ያለዉ ግለሰብ ጥያቄዉን አቅርበዋል። ሽመልስ ስለሺ ደግሞ «ዶክተር ዐብይ በአማራ እና በትግራይ ክልል ያለውን የህዝብ ፍጅት እንደሚያስቆሙ ተስፋ እንዳለዉ» ገልፀዋል።
በምስራቅ ወለጋ በነቀምት ከተማና አካባቢውም ከፍተኛ ውጥረት እንደነበረ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲጠቁሙ ነበር። የፀጥታ ዉጥረቱም መነሻ ያደረገዉ ከቤንሻንጉል ክልል የመጡ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ነዉ። ይህንን ድርጊት ለመቃወም አደባባይ በወጡት ነዋሪዎች ላይ ፖሊስ ጥቃት አድሮሷል። ሰዎችም ሞተዋል። 

በዚህ ጉዳይ ላይ በ«DW» ፌስቡክ ገፅ ላይ አስተያየታቸዉን ካጋሩን ዉስጥ ናሆም ይገኝበታል። እሱም «በእውኑቱ ኢትዮጲያ ጠንካራ መንግስት አላትን? ሲል ጠይቋል።  ቤክ ገለታ ዳፒላር በበኩሉ «ይችህ ጉዳይ በቀጥታ አቶ ለማን ነዉ የምትመለከተው፣ የታጠቀ ኃይልን ህዝቡ በምን አቅሙ ነዉ በባዶ እጁ ሰላሙን የሚጠብቀዉ? ተመጣጣኝ እርምጃ ያስፈልገል» ሲል ዐብይ ደብሩ ደግሞ «ህወሓት ካልጠፋች ኢትዮጵያ ሰላም የላትም» ባይ ነዉ። 
ድርጊቱ በጣም እንዳሳዘነዉ የገለፀዉ ተስገራ በዳሳ በድንጋይና በእንጨት መንገድ መዝጋት ለችግራችን መፍትሔ አይሆንም፣ የሞቱት ነፍሳቸዉ ይማር፣ ከዚህ በኋላ ሰዉ መሞት የለበትም፣ ችግራችንም በዉይይት እንፍታ የሚል አስተያየቱን ፅፈዋል።

የሶማሊ ክልል ፕሬስዳንት ሙስጣፋ ኦሜር በክልሉ ዉስጥ ያለዉ የፀጥታ ዉጥረትን አስመልክቶም ማስጠንቀቅያ ሰቷል። በፌስቡክ ገፃቸዉ ላይ ባወጡት ፅሁፍ «በጂጂጋ ወይም በሶማሌ ክልል ውስጥ ከዘር ጥላቻ ቦታ የለዉም ብለዋል። በጅግጅጋ ዉስጥ የሶማሊኛ ተናጋሪዎች ተናጋር ያልሆኑት ላይ ጥላቻን የምያናፍሱት ግለሰቦች ከድርግታቸዉ እንድቆጠቡ፤ ካልሆነ በህግ እንደምቀጡ አሳስበዋል። የዘር ጥላቻን እንድ መርህ የያዙት ታዋቅ የዱልሚዲዲ አክትቭስቶችን ከድርግታቸዉ እንድቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።


Äthiopien Shimeles Abdisa
ምስል DW/Yohannes G. Egzihaber

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆኖ ሰሞኑን ተሹመዋል። አዲስ የተቋቋመዉን የፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት እንደመሩ ደግሞ ወ/ሮ ቢልለኔ ስዩም ተመድበዋል።

በነሱ ሹመት አስመልክቶም በ «DW» ፌስቡክ ላይ አስተያየታችዉን ያጋራው መንግስቱ ሜኮንን «ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም፣ ህዝብ እያለቀ ለማን ነዉ የሚሾሙት ያስቃል» ብለዋል። የሱን ሃሳብ የሚጋራዉ አማኑኤል ንጋቱ ሰዎች ከቀያቸዉ እየተፈናቀሉ የሰዎችን ስልጣን መቀያየር መፍቴ አይሆንም። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኦሮሞያ ክልል እየተደረገ ያለዉን መፈናቀልና ሞታ ማስቆም አለባቸዉም ብለዋል።

ኟዧ ጿቛ የሚል የፌስቡክ ስም ያለዉ ደግሞ «ዓብይ መንግስታቸውን ወያኔን ቀጥ እንዳይል አድርጎ ያዋቅረዋል፥ በርታ ዐብያችን፥ ምድረ ርሀብተኛ ዘራፊዎችን ማፅዳት ግድ ነው» ብለዋል። ጋድሳ ዳራጄ በበኩሉ በፍት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ አመራሮችን አስመልክቶ ከዝንብ ማር አይጠበቅም የሚባል አባባል እየተቀየረ ነዉ ብለዋል።

መርጋ ዮናስ

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ