1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የላሊበላ መካነ ቅርስ የመፈራረስ አደጋ

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 2010

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት የኢትዮጵያ ቅርሶች አንዱ የሆነዉ የላሊበላ ውቅር መካነ ቅርስ የመፈራረስ አደጋ አንዣቦበታል ተባለ።በጥናት ላይ ያልተመሰረተ ጥገና ቅርሱን ለአደጋ እንዳጋለጠዉ የደብሩ አስተዳዳር ገልጿል።

https://p.dw.com/p/2nhKz
Bet Giyorgi Felsenkirche von Lalibela in Äthiopien
ምስል picture alliance/Robert Harding World Imagery

 የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ ቅርሱን ከአደጋ ለመታደግ ጥናት አጠናቅቄ ወደስራ ልገባ ነዉ  ብሏል።

ከ 800 አመት እድሜ በላይ ያስቆጠረዉ የላሊበላ መካነቅርስን ከተፈጥሯዊና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ  በሚል ከ 10 አመት በፊት በዩኒስኮ በኩል በኢጣሊያናዊ ባለሙያዎች የብረት መጠለያ እንደተሰራለት የደብሩ አስተዳደር ያስታውሳሉ። ይሁን እንጅ ቅርሱን ይታደገዋል ተብሎ የተሰራዉ መጠለያ በቂ ጥናት ያልተደረገበትና  የህንፃዉን ባህሪይ ግምት ዉስጥ ያላስገባ ስለነበር ይህ የዓለም ቅርስ ህልዉናዉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን የደብሩ አስተዳዳሪ አባ ያሬድ ምስጋናዉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። መጠለያዉ ከግዙፍ ብረት በመሰራቱና የተተከለዉም በህንጻዉ የቅርብ ርቀት ላይ  በመሆኑ ቅርሱን ይጎዳዋል የሚል ስጋት በወቅቱ የአካባቢዉ ህብረተሰብ  አንስቶ የነበረ ቢሆንም ሰሚ እንዳላገኜ  አስታዉሰዉ  የመጠለያዉን ተጨማሪ ጉዳት ያብራራሉ። 
መጠለያዉ  ለ5 ዓመታት ያገለግላል ተብሎ እንደተሰራ የገለጹት አስተዳዳሪዉ ያም ሆኖ ግን  ሳይጠገን 10 ዓመት ሆነው። ጊዜዉን ጠብቆ ባለመቀየሩና ባለመጠገኑም የተያያዘበት አለት እየተሰነጠቀ  በመሆኑ በአጭር ጊዜ መፍትሄ  ካልተሰጠ   ይህ ግዙፍ ብረት በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ወድቆ ወደ ፍርስራሽነት ይቀይራቸዋል የሚል ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩንም አብራርተዋል። ያ ከመሆኑ በፊት ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅርሱን  ሊታደግ ይገባል ሲሉ አባ ያሬድ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር በበኩሉ የአካባቢዉ ማህበረሰብ ስጋትም ይሁን በቅርሱ ላይ የተደቀነዉ አደጋ ትክክል መሆኑን ገልጾ የአብያተክርስቲያናቱ አሰራርና ጥበብ በየትኛዉም ዓለም የሌለ በመሆኑ ለጥገና አስቸጋሪ ነበር።መጠለያዉ በዩኔስኮና በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እዉቅና ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶለት የተሰራ ቢሆንም  በወቅቱ ይህንን  አደጋ በጥናት ላይ ተመስርቶ የሚያሳይ የሰለጠነ ባለሙያና ቴክኖለጂ  ባለመግኘቱ  አማራጭ በማጣት የተሰራ  ነዉ ሲሉ በምንስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን ጉዳዩን የሚያጠኑ ባለሙያዎችና ቴክኖሎጅ በመገኘቱና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ነዉ ይላሉ።
ጥገናዉን በተሟላ ሁኔታ ለማካሄድም ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ጠቅላይ ሚንስቴር መስሪያቤት መላኩን አመልክተዋል።ለጥገናዉ 1 ቢሊዬን የሚደርስ ብር ያስፈልገዋልም ተብሏል። ችግሩ ግዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ ሁሉም የድርሻዉን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አቶ ገዛኽኝ  አሳስበዋል።

Lalibela - Orthodoxe Christen
ምስል Reuters/Goran Tomasevic

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ