1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘመነ-ሙጋቤ እና ፍፃሜዉ

ሰኞ፣ ኅዳር 11 2010

ለጥቁሮች ነፃነት ቆርጦ-በመታገል፤ ማታጋላቸዉ፤ ለፍትሕ-ነፃነት በመፋለማቸዉ በነጮች ተወንጅለዉ ወሕኒ በመወወራቸዉ እንደማንዴላ ናቸዉ።እንደ ማንዴላ አሳሪ-አሰቃዮቻቸዉን ይቅር ባይ ግን አይደሉም።ሥልጣን በቃኝንም አያዉቁም።ማንዴላን አይደሉም።

https://p.dw.com/p/2nxG0
Simbabwe Veteranen fordern Rücktritt von Mugabe
ምስል Getty Images/AFP/J. Nijkizana

ዘመነ-ሙጋቤ እና ፍፃሜዉ

 ጥብቅ ኃይማኖተኛ ናቸዉ።ካቶሊክ።ደሞ በተቃራኒዉ ማርኪሲስት ታጋይ፤ ጥቁር ብሔረተኛ፤ በሳል ፖለቲከኛም።እንደ ሶሻሊስቱ ያንድ ፓርቲ ሥርዓት አራማጅ «ጓድ»ም ናቸዉ።ግን እንደ ካፒታሊስቶቹ የግል ሐብትን ይፈቅዳሉ።ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ።የነጮችን አገዛዝ ባጠቃላይ-የእንግሊዞችን በተለይ አጥብቀዉ ይጠላሉ።የሚወዱት ስፖርት ግን የእንግሊዞች ነዉ። ክሪኬት። ለሐገራቸዉ ነፃነት የፈረሙት ዉል የእንግሊዞች፤ እንግሊዝኛቸዉም የእንግሊዞች ነዉ።ከ1960 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንደ ታጋይ፤ እንደተደራዳሪ፤ እንደ ፓርቲ፤ እንደ ሐገር መሪም ሲጨበጨብ፤ ሲዘፈን ሲፎከርላቸዉ ኖሩ።ባለፈዉ ሳምንት ጦራቸዉ በቁም አሰራቸዉ።ትናንት-የእስከ ትናንት ታዛዥ፤አጨብቻቢዎቻቸዉ-አሽቀንጥረዉ ጧሏቸዉ።አጨበጨቡ-ዘፈኑባቸዉ።በቁን-አሏቸዉ።ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ።ላፍታ እንዘክራቸዉ።

                           

ለጥቁሮች ነፃነት ቆርጦ-በመታገል፤ ማታጋላቸዉ፤ ለፍትሕ-ነፃነት በመፋለማቸዉ በነጮች ተወንጅለዉ ወሕኒ በመወወራቸዉ እንደማንዴላ ናቸዉ።እንደ ማንዴላ አሳሪ-አሰቃዮቻቸዉን ይቅር ባይ ግን አይደሉም።ሥልጣን በቃኝንም አያዉቁም።ማንዴላን አይደሉም።

እንደ ክዋሚ ንኩሩማ የጥቁር ብሔረተኝነትን አራማጅ ናቸዉ።እንዲያዉም የሕይወት ታሪካቸዉ ፀሐፊዎች እንደሚሉት የፖለቲካ ሥልት፤የታጋይነት-ስሜት ጥቁር ብሔረተኝነትን የተማሩት ከክዋሚ ንኩሩማ እና ከንኩርማዋ ጋና ነዉ።የምዕራባዉያንን መርሕ መቃወም-ማዉገዛቸዉን ዛሬም በ93 ዓመታቸዉ አልተዉትም።ባለፈዉ መስከረም ተሰይሞ ለነበረዉ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባደረጉት ንግግር ሌላ አላሉም።

                               

«የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ የተወሰኑ ወገኖች በሌሎች ላይ እንዲፈርዱ መብት የሚሰጥበት አንድም ሥፍራ የለም።ይሕን ዓለም አቀፍ ግዴታ በመወጣቱ ረገድ ደንቡን ለፖለቲካዊ ጥቅም ማዋልን እንቃወማለን።የዘመናችን አስተሳሰብን አንግበዉ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚያስቡ ወገኖችን ሰላባ የሚያደርግ ተፃራሪ መንታ አቋምን እናወግዛለን።»

Flash-Galerie Nelson Mandela
ምስል AP

ማርክሲስት ናቸዉ።ግን የማኦ ዜዱንግን እንጂ እንደ ንኩሩማ የሌኒንን አስተምሕሮ አቀንቃኝ አይደሉም።ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ።

ለከፍተኛ ትምሕርት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ከመጓዜ በፊት ማርክሲዝምን አንብቤ ነበር።» ብለዉ ነበር ባንድ ወቅት። «በ1949 ደብብ አፍሪቃ ስገባ ግን የማሕተመ ጋንዲ አስተምሕሮ በጣም ማርኮኝ ነበር።» ቀጠሉ ያኔ።ግን እንደ ጋንዲ የሠላማዊ ትግል አራማጅ፤ እንደ ኃይማኖተኛም «ቀኝ ጉንጭሕን ለፀፋሕ ግራሕን፤ ስጠዉ» ብሎ አስተምሕሮ አይገባቸዉም።

በ1970ዎቹ የፓርቲያቸዉን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሥብሰባ ሲጀምሩ እና ሲጨርሱ ግን እንደ ማርክሲስቶቹ በመፈክር፤ እንደካፒታሊስቶቹ በፊርማ-ዉል አልነበረም።በፀሎት እንጂ።

የደኃ አናፂ ልጅ ናቸዉ።በልጅነቱ ካቶሊክ ሚስዩን ትምሕርት ቤት ተማረ።ወጣቱ ሮበርት እንደ ብዙ የእድሜ አቻዎቹ የአረዳ፤ሁዳድ፤ሜዳ ጨዋታ፤ሩጫ፤  ቡረቃ ድብድብ ብዙ አይጥመዉም ነበር።በዚም ምክንያት አንዳድ ጓደኞቹ «ፈሪ» ይሉት ነበር። እሱ ግን ያነባል፤ መፅሐፍ ቅዱስን፤ ሌሎች መንፈሳዊ መፅሐፍትን፤ ካስተማሪዎቹ የሚያገኘዉን መፅሐፍ ጋዜጣ ያገኘዉን ሁሉ ያነባል።

የልጅነት ጓደኞቻቸዉ እንደሚሉት ወጣቱ ሮበርት አልፎ አልፎ በተለይ በቤት ዉስጥ ጨዋታዎች ከተሳተፈ ሁሌም የመሪነቱን ሥፍራ መያዝ ይፈልጋል።«ጨዋታዉ ሥለቤተ ክርስቲያን ቢሆን እንኳ» ይላሉ አንድ የጥንት ጓደኛቸዉ «ሮበርት የሚፈልገዉ ጳጳሱን ሆኖ መጫዎት ነዉ።»

Simbabwe Harare Jubel nach Entmachtung Robert Mugabes
ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Curtis

ሥልጣን በተለይም መሪነትን ያኔም ይወዳሉ ነዉ መልዕክቱ። ትምባሆ እና አልኮል አይቀምሱም።አለባበስ፤አጊያጌያጣቸዉ ሁሌም ዘመናይ እና ማራኪ ነዉ።«ሽክ» ያሉ ናቸዉ-በአዲስ አበቦች ቋንቋ።ደግሞ በተቃራኒዉ የአፍሪቃዊ ነባር ባሕል እና ወግን አክባሪ ናቸዉ።ዛሬም።

                               

«እሴታችንን፤ ባሕላችንን እና ትዉፊታችን የሚፃረሩ አዳዲስ መብቶች ሲታዘዝልንም አንቃወማለን።ግብረ ሶዶማዉያን አይደለንም።»በ1980 የጠቅላይ ሚንስተርነቱን  ሥልጣን ከመያዛቸዉ ጥቂት ቀደም ብለዉ በሰጡት መግለጫ እሳቸዉና ብጤዎቻቸዉ የነጮች አገዛዝን በመቃወም የሚታገሉት ካባት አያቶቻቸዉ ከሰሙት ታሪክ እና እራሳቸዉም ያዩትን ግፍ ለማስወገድ አልመዉ ነዉ።

                                           

«እንደሚመስለኝ አብዮቱ የጀመረዉ ወላጆቻቸን ከነገሩን ታሪክ በመነሳት ነዉ።ነጭ እንዴት ወደ ሐገሪቱ እንደገባ፤ መሬታቸዉን እንዴት እንደወሰደባቸዉ ከነገሩን ነዉ።ዋና አላማዉ እራሱን ማበልፀግና ሌሎችን መበዝበዝ የሆነ መደብ ባለበት ማሕበረሰብ ዉስጥ ካለሕ መበሳጨትሕ ተፈጥሯዊ ነዉ።አብላጫዉ ሕዝብ ሲጨቆንና ሲበዘበዝ እያየሕ አርፈሕ መቀመጥ አትችልም።የሞራል ልዕልና ካለሕ የሆነ ነገር ለማድረግ ትነሳለሕ።»

በ1958 አስተማሪ ሆነዉ ጋና ሔዱ።«ጋና የሔድኩት ነፃ አፍሪቃዊ መንግስት ምን እንደሚመስል ለማየት ነዉ» አሉ ባንድ ወቅት።በ1960 ጋናዊቱን ኮረዳ አግብተዉ ሐገራቸዉ ተመለሱ።የነጭ አገዛዝን በመቃወም ቀጥታ ትግል ጀመሩ።የፖለቲካዉን መሰላል ለመወጣጣት ለአንደበቱ ርቱዑ፤ ለባለሰወስት ዲግሪ ሙሑሩ ብዙም ከባድ አልነበረም።ግን በ1963 ታሰሩ።

Simbabwe Mugabe verkündet bei TV-Ansprache nicht wie erwartet Rücktritt
ምስል picture alliance/AP Photo/Zimbabwe Herald

በ1974 ሲፈቱ በሰወስቱ ዲግሪ ላይ ሌላ ሰወስት አክለዉ ባለስድስት ዲግሪ፤እዉቅ ፖለቲከኛም ሆነዉ ከወሕኒ ቤት ወጡ።የዚምባቡዌ የአፍሪቃ ብሔራዊ ሕብረት (ዛኑ) የትጥቅ ትግል ለማስተባበር ወደ ሞዛምቢክ ተሰደዱ።የፓርቲዉን የመሪነትን ሥልጣንም ጠቀለሉ።አብዛኛ ህዝባቸዉን ያዘምሩ፤ያስጨፍሩ፤ ያስፈክሩ፤ በአብዛኛ ሕዝባቸዉ ይደነቁ ገቡ።

                                

ሙጋቤ ቀዳሚዎቻቸዉን ሁሉ መስለዉ ሙጋቤን ሆነዉ እንደ ሸማቂ እየተዋጉ፤ እንደ ፖለቲከኛ እየሻጠሩ፤ አንዳዴም እየገደሉ፤ እያሰሩ፤ እንደ ዲፕሎማት እየተደራደሩ፤ የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎችን፤ የጥቂት ነጭ ጨቋኞችን፤  የነአቤል ሙዘሬዋ፤የነጆሽዋ ንኮሞ ተቀናቃኞቻቸዉን ተራበተራ ጠራርገዉ ዚምባብዌን እንዳሻቸዉ ይዘዉሯት ያዙ።

በ2000 ነጮች ይቆጣጠሩት የነበረዉን ሰፋፊ የእርሻ መሬት፤ መሬት ለሌላቸዉ ጥቁሮች በተለይም ለቀድሞ የነፃነት ተዋጊዎች ማከፋፈል ሲጀምሩ ግን ከማይገፉት ተራራ ጋር ተላተሙ።ከብሪታንያ ጋር።በብሪታንያ በኩል ከምዕራባዉያን ጋር። እርግጥ ነዉ የብሪታንያን የቅኝ አገዛዝ ትልቅ ተራራን ባንድ ወቅት በነፍጥም፤በዲፕሎማሲ፤ በዉጪም ድጋፍ ብለዉ ዚምባዌ ምድር ላይ ንደዉት ነበር።የ2000ዋ አፍሪቃ ግን እንደ 1970ዎቹ ለአፍሪቃዉን ነፃነት በጋራ የቆመች አይደለችም።

በ1970ና ሰማኒያዎቹ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች፤ራዲዮ ጣቢያዎች፤መተላለፊያ ወደቦች፤የሞዛምቢክ፤የዛምቢያ፤የታንዛኒያ ወዘተ ሜዳ ጫካዎች ለዚምባቡዌ የነፃነት አርበኞች ክፍት ነበሩ።የሶቬት ሕብረት፤የኩባ፤የቻይና ድጋፍ በሽ ነበር።2000 ሁሉም የለም።ሁሉም West is besete እያለ ለምዕራብ ሰግዷል።

የዚምባብዌ ምጣኔ ሐብት በማዕቀብ ሲዳከም፤የነሞርጋን ቻንግራይ ኮኮብ ደመቅ፤የሙጋቤ ጀምበር ዘቅዘቅ እያለች ለጥልቀትዋ ትጓዝ ያዘች።ሽማግሌዉም አላወቁበትም።ለሚወዷት ባለቤታቸዉ ሥልጣናቸዉን ለማዉረስ የብዙ ዓመታት ታማኞቻቸዉን ከስልጣን እያሽቀነጠሩ ሲጥሉ፤ ታማኙ ጦራቸዉ ካዳቸዉ።ሮብ በቁም አሰራቸዉ።ትናት ደግሞ ለዘመናት የመሩት ፓርቲያቸዉ በቁን አላቸዉ።አስወገዳቸዉ።

                           

«ዉሳኔዉ ከዚሕም በተጨማሪ፤ ጓድ RG ሙጋቤ ከፕሬዝደትነቱ እና ከዚምባቡዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ርዕሰ-ብሔርነት ሥልጣን እንዲነሱ (የዛኑ-ፒ ኤፍ ፓርቲ) ወስኗል።እስከ ነገ ሕዳር 20፤ 2017 ድረስ እኩለ ቀን ድረስ ስልጣናቸዉን ካላስረከቡ፤ የዛኑ ፒ ኤፍ የምክር ቤት አባላት  በዚምባብዌ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 97 መሠረት ሥልጣን እንዲያስለቅቅ ታዟል።»

                         

ይሕ ማለት ሙጋቤ ሥልጣን አለቅም ካሉ፤ ሥልጣን እንዲለቁ የሐገሪቱ ምክር ቤት ዛሬ ቀትር ላይ ይወስናል ማለት ነበር።ሙጋቤ ትናንት ሥልጣን አልቅም ብለዉ ነበር።ዛሬ ደግሞ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ እያረቀቁ ነዉ ሲባል ነበር።በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ እስራ-ሁለት ሰዓት ድረስ ግን የዘጠና ሰወስት ዓመቱ አዛዉንት ሥልጣን አለቀቁም።ምክር ቤቱም አልወሰነም።

የቀድሞ የፓርቲ ታዛዦቸዉ ግን አጨበጨቡ፤ ዘፈኑ፤ ሙጋቤ ክጥቂት ሳምንታት በፊት ያባራሯቸዉን ምክትላቸዉን ኤመርሰን ምናን-ጋግዋን መርጠዉ አላገጡባቸዉም።

                           

የፖለቲካ ተንታኝ ብሌሲንግ ቫቫ  ግን ይጠይቃሉ ምናን-ጋግዋን ከሙጋቤ በምን ይሻላሉ እያሉ።«ምናን-ጋግዋ፤ ፕሬዝደንት ሙጋቤ የሚያዙት የአብዛኛዉ የሐይል እርምጃ ተሳፊ እና አስፈፃሚ ነበሩ።የሙጋቤ አልሞ ተኳሽ ዓይነት ነበሩ።ሥለዚሕ ለኔ የመሪነታቸዉ ብቃት ገና መታየት የሚገባዉ ነዉ።ይሁንና በግልፅ ከሚታየዉ እና አብዛኛዉ የዚምባቡዌ ሕዝብ ከሚለዉ ብንነሳ ይሕ ሰዉ ሰይጣን ነዉ።ጨካኝ ነዉ።ገዳይ ነዉ።ስለ ኤመርሰን ምናን-ጋግዋን ስንሰማ ያደግነዉ እንደዚሕ ነዉ።»

Kopenhagen Klima-Konferenz 2009 Robert Mugabe Präsident Simbabwe
ምስል picture-alliance / photoshot

ማንም መጣ ማን የዘጠና ሰወስት ዓመቱ አዛዉንት የሥልጣን ጀምበር በርግጥ ጠልቃለች።ከአፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ሞቡቱ ሴሴኮ፤ ከዚያድ ባሬ፤ እስከ ቃዛፊ፤ ከቤን ዓሊ እስከ ሙባረክ እንደተከበሩ፤ እንደተፈቀሩ፤ እንደተደነቁ መጦርን እንቢኝ ያሉ የደረሰባቸዉን ከሙጋቤ እኩል ያየ አይኖርም።እሳቸዉም ደገሙት እንጂ አልተመሩም።«መጨረሻዬን አሳምርልኝ» ብሎ አባባልን ፖለቲከኞች አያዉቁት ይሆን?ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ