1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውጥረት የሚታይበት የኮንጎ ምርጫ ዘመቻ

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2011

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ በጎርጎሪዮሳዊው ታህሳስ 23፣ 2018 ዓም ፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ ይደረጋል። ይሁንና፣ በምርጫው ለሚወዳደሩት ግለሰቦች ውጊያ በቀጠለበት በሀገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢ የምርጫ ዘመቻ ማካሄድ ግን እጅግ አዳጋች ሆኗል።

https://p.dw.com/p/35BPV
Chrispin Mvano steht am Berg
ምስል DW/S. Schlindwein

የዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ሬፓብሊክ ምርጫ ዘመቻ

በሙያ ጋዜጠኛ የሆነው የ40 ዓመቱ ክሪስፒን ምቫኖ  ከሶስት ወራት በኋላ ታህሳስ 23፣ 2018 ዓም በዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ሬፓብሊክ  በሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ በሀገሪቱ ምሥራቃዊ ከፊል ባለው የሰሜን ኪቩ ግዛት በሚገኘው ትውልድ ወረዳው ማሲሲ በእጩነት ለመወዳደር ወስኗል። የምቫኞ ዋና ዓላማም ለማሲሲ ነዋሪዎች ሰላም ማውረድ ነው። በኮንጎ ለተሰማራው የተመድ ተልዕኮ  አልፎ አልፎ በአማካሪነት፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በቀውስ ጉዳዮች ተንታኝነት የሚሰራው ክሪስፒን ምቫኖ ተራራማው የማሲሲ አካባቢ ካለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ወዲህ የጦርነት ቀጠና መሆኑን ገልጿል። ምቫኖ እንደሚለው፣ የመንግሥት ኅልውና የለም ሊባል በሚችልበት መንገድም ሆነ ትምህርት ወይም ሀኪም ቤትን የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት መዋቅር በጠቅላላ ተጓድሎ በሚገኝበት ውዝግብ በበዛበት በዚሁ አካባቢው  ከ10 የሚበልጡ የተለያዩ የኮንጎ እና የውጭ ሀገራት ዓማፅያን ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ፣ እያንዳንዱ መንደርም ከነዋሪዎቹ የተውጣጣ የራሱ ተከላካይ ኃይል አለው። ምቫኖ የምርጫ ዘመቻውን በሚጀምርበት 800 ሰዎች በሚኖሩበት ኮረብታማው የሾንጋ መንደር ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ውዝግብ መኖሩን ገልጿል።
« ሾንጋ ብዙ ችግር ያሳለፈ መንደር ነው። አንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው ባለሀብት በ2015 ዓም ወደ አካባቢው በመሄድ በዚያ ያለው የእርሻ መሬት በጠቅላላ የሱ እንደሆን ያስታውቃል። ያኔ የመንደሩ ሴቶች እና ህፃናት ሳይቀሩ በእግራቸው እስከ ግዛቱ ዋና ከተማ ፣ ጎማ ድረስ በመሄድ፣ አራት ቀናት ሙሉ ዝናብ ሳይበግራቸው በግዛቱ አስተዳዳሪ ጽህፈት ቤት ደጃፍ በመቆየት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ይህን ተከትሎ አስተዳደሩ ወደ ሾንጋ ፖሊስ ልኮ፣ የተቃውሞውን መሪዎች ሁሉ ካሰረ በኋላ መንደሩን በጠቅላላ እንዲቃጠል አድርገዋል። »
በማሲሲ ወረዳ፣ በሾንጋ መንደር በመሬት ሰበብ ውዝግብ የሚነሳበት ሁኔታ የተለመደ ሲሆን፣ በጎሳዎች መካከል በሚፈጠር ልዩነት ሰበብ አዘውትሮ ወደ ኃይል ግጭት ሲቀየር ታይቷል። ከነዚሁ ውዝግቦች መካከል ብዙዎቹ ዛሬም ከ20 ዓመት በላይም በኋላ መፍትሔ አላገኙም።  በማሲሲ የሚኖሩ የቱትሲ ጎሳ አባላት በጎረቤት ርዋንዳ ከተከሰተው የጎሳ ጭፋጨፋ በኋላ የሁቱ ተወላጆችን ጥቃት በመፍራት የእርሻ ቦታቸውን እየተው ቢሸሹም ፣ አሁን በማሲሲ በግብርና ከሚተዳደሩት የባሁንዴ እና የሁቱ ጎሳዎች አባላት ጋር በመሬት ሰበብ ሲወዛገቡ ይገኛሉ።  የባሁንዴ ጎሳ ተወላጅ የሆነው ምቫኖ ከመዲናይቱ ኪንሻሳ ርቆ ሊ,ሚገኘው እና የማዕከላዩ መንግሥት ትኩረት ያላገኘው የሾንጋ መንደር ነዋሪን ችግር ለማስወገድ እንደሚሰራ በምርጫው ዘመቻ ለማዳመጥ ለተሰበሰበው ሕዝብ ቃል ገብቷል፤ እርግጥ፣ ካሁን ቀደም አንድም እጩ ተወዳዳሪ አይቶ የማያውቀው የሾንጋ ሕዝብ ምቫኖን ሀሳብ ቢደግፈውም፣ የተገባው ቃል እውን መሆኑን ተጠራጥሮታል፣ ምቫኖም  የሾንጋ ነዋሪዎች ጥርጣሬ ከምን እንደመነጨ በሚገባ እንደሚያውቀው ነው የተናገረው።
« ለሾንጋ ሕዝብ ቅሬታ ተጠያቂው የፖለቲከኞች ድክመት ነው፣ ምክንያቱም፣ እነዚህ ፖለቲከኞች አንዴ ለስልጣን ከተመረጡ በኋላ የሚወክሉትን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል በመሞከር ፈንታ ራሳቸውን ለማበልጸግ ብቻ ነው የሚሰሩት። »
ይህን የሕዝቡን ቅሬታ ለመቀየር የሚቻለው ፣ እንደ ምቫኖ አስተያየት፣ በየጊዜው ምርጫ በማካሄድ እና ሕዝቡም በምርጫ እምነት እንዲያደርበት በማድረግ ነው።
« ለኛ ወሳኙ ነገር የህብረተሰቡ አስተሳሰብ አንድ ቀን በዴሞክራሲያዊ ሂደት አማካኝነት እንዲቀየር ነው። ሂደቱ አሁን እንዳለው ከቀጠለ ፣ ፖለቲከኞች ለሕዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚገደዱበት አንድ ቀን ይመጣል። በሀገሪቱ የሚደረግ ምርጫ በጥሩ ሁኔታ ተደራጀ አልተደራጀ፣ እስከተካሄደ ድረስ አንድ ቀን በጥሩ ሁኔታ ተደራጅቶ ሊደረግ ይችላል የሚል እምነት አለን። » 

Chrispin Mvano hält Ansprache in Kirche
ምስል DW/S. Schlindwein
Demokratischen Republik Kongo - Rathaus von der Stadt Goma
ምስል DW/F. Quenum


አርያም ተክሌ/ዚሞነ ሽሊንድቫይን

ነጋሽ መሀመድ