1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ አወዛጋቢዉ የአዲስ አበባ ማንነት ጥያቄ

ሰኞ፣ መስከረም 28 2011

አዲስ አበባ ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ እንዲያገኝ አሁን መነሳቱ አስፈላጊ ነዉ የሚሉ ሰዎች የመኖራቸዉን ያህል፤ በዉጭ የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ያላቸዉ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲገቡ በተፈቀደበትና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ እየተሰራ ባለበት ወቅት፤ መግለጫዉ መዉጣቱ ለለዉጡ ደንቃራ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸዉን የሚገልፁ አሉ።

https://p.dw.com/p/367QK
Addis Abeba
ምስል Haile

«ሃገርን ለሕዝብ በመመለስ ጉዳይ መሥራት አለብን»

ባለፈዉ መስከረም 15፤ ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚቃወሙ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያወጡት መግለጫ በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር «ኦነግ»፤የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ «ኦፌኮ»፤ የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፤ የኦሮሚያ ነፃነት አንድነት ግንባር እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ካነስዋቸዉ ጉዳዮች መካከል ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ስላሏቸው ሚድያዎች፣ በሃገሪቱ እየታየ ስላለው ለውጥ እና ስለፌደራሊዝም አስተዳደር እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማን የባለቤትነት ጉዳይ ይገኙበታል።

በመግለጫዉ የተነሱት ጉዳዮች በተለይም የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ብዙዎችን ያነጋገረ እያከራከረ ሲሆን ድጋፍና ተቃዉሞ እንዲሁም ትችትና ወቀሳም አስተናግዶአል። እንደሚታወቀዉ  ኢህሃዴግ  ሃሪቱን መምራት ከጀመረ ከ 1983 ዓ.ም ወዲህ  ሃገሪቱ በብሔር ላይ ያተኮረ የፊደራል ሥርዓት እየተዳደረች ትገኛለች። ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባን በተመለከተ ከተማይቱ የፊደራል መንግስት ርዕሰ ከተማ ከመሆንዋ በተጨመሪ በኦሮምያ ክልል ዉስጥ የምትገኝ በመሆንዋ የኦሮምያ ክልል አስተዳደር ልዩ ጥቅም እንዲያገኝ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን የሕግ ባለሞያዎች ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜ እና በተለያዩ አካላት ሲነሳ የነበረ ጉዳይ ቢሆንም አምስቱ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ጊዜ በይፋዊ መግለጫ ጉዳዩን ሲያነሱት የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደገና የመወያያ አጀንዳን ፈጥሮአል። የአዲስ አበባ ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ እንዲያገኝ  አሁን መነሳቱ አስፈላጊ ነዉ የሚሉ ሰዎች የመኖራቸዉን ያህል፤ በዉጭ የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ያላቸዉ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲገቡ በተፈቀደበትና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ እየተሰራ ባለበት ወቅት፤ የእርቅ የመደመር፤ የፍቅር የመረጋጋት ጊዜ እንዲሆን እየተሰራ ባለበት ሁኔታ መግለጫዉ መዉጣቱ ለለዉጡ ደንቃራ ይሆናል፤ አልያም ለተጀመረዉ ለዉጥ ጫና ይፈጥራል የሚል ሥጋት የሚያነሱ ወገኖችም አሉ። ከዚህም በተጨማሪ መቅደም ያለባቸዉ የመልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች አሉ የሚሉም አሉ።

አምስቱ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸዉ ግን አቋማቸዉ ትክክል እንደሆነ አስታዉቀዋል። በተለያየ አጋጣሚዎችም እየገለፁ ነዉ። የአዲስ አበባ ማንነት ጥያቄ እና የአምስቱ ፓርቲዎች መግለጫ ዉዝግብ የዛሬዉ ዉይይታችን ርዕስ ነዉ። በዚህ ርዕስ ላይ እንዲወያዩልን የጋበዝናቸዉ፤ አቶ በቀለ ገርባ፤  የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ተቀዳሚ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማ ሰይፉ ፤ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ፤ አቶ ተማም አባቡልጉ ሕግ ባለሙያ ናቸዉ።

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ