1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወባን የማጥፋት ዕቅድ

ማክሰኞ፣ መስከረም 22 2011

ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ ባልታየባት ኢትዮጵያ ወባን የማጥፋት መርሃ ግብር እንዲነደፍ ተስፋ የሰጠ መስሏል።  እንዲያም ሆኖ አሁንም በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የወባ ስርጭት ያን ያህል እንዳልቀነሰ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/35sSQ
Kenia Netz gegen Malaria-Mücke
ምስል picture-alliance/dpa7S. Morrison

ባለፉት አምስት ዓመታት የወባ ወረርሽኝ አልነበረም

በኢትዮጵያ ከዝናብ ወቅት ወደ ሙቀቱ መሸጋገሪያ በሆኑት ወራት የወባ ትንኝ የምትራባበት በመሆኑ ይለያል። የብሔራዊ የወባ መርሃግብር አስተባባሪ አቶ መርሃቶም ኃይለ  ለDW እንደገለፁት ከመስከረም እስከ ኅዳር ባሉት ጊዜያት ይህ የተለመደ ነው። ይህ ወቅትም መኸር የሚሰበሰብበት፣ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚገቡበት በመሆኑም ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጫና እንደሚኖሩም አመልክተዋል። የወባ በሽታ ተጠናክሮ በሚታይባቸውም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በዚህ ወቅት የወባ ትንኝ እንዳትራባ እና እንዳትስፋፋ አስቀድመው መሠራት የሚገባቸው የመከላከያ ርምጃዎች መኖራቸውን እና ዘንድሮም መከናወናቸውን አቶ መብርሃቶም እንዲህ ዘርዝረዋል።

«በዋናነት ከምንጠቀምባቸው ስትራቴጂዎች አንዱ የትንኝ ቁጥጥር ነው። የቤት ውስጥ ርጭት ይከናወናል፤ ዘንድሮም ዋና የወባ መተላለፊያ ወቅት ከመምጣቱ በፊት በዋናነት የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራ የሚሠራው በክልዖች ባሉት ወራዳዎች ቀበሌዎች ላይ ነው። ስለዚህ አስቀድመን የሠራነው ሥራ ምንድነው፤ አንደኛ ያው ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ራሱን ከወባ በሽታ እንዲጠብቅ እና የወባ መከላከያ የሆነውን አጎበር እንዲጠቀም እንዲሁም ቤቱ በጨረ ወባ ኬሚካል ርጭት እንዲያስረጭ እነዚህ ሥራዎች አስቀድመው ተሠርተዋል።»

ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ የወባ መርሃግብር አስተባባሪው እንደገለፁት፣ ከሦስት ዓመት በፊት ለኅብረተሰቡ የተሠራጩ አጎበሮችን ለመተካት በ2010ዓ,ም ወደ 11 ሚሊየን የሚሆኑ አጎበሮችን ማሰራጨት መቻሉንም አስረድተዋል። በዚያም ላይ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የወባ ትንኝ ልትራባበት የምትችለውን ውኃ የሚያጠራቅሙ ስፍራዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠሩም ይናገራሉ።

«በኅብረተሰብ፤ በማኅበረሰብ በተለያዩ አደረጃጀት የሚሠሩ የወባ ቁጥጥር ሥራዎች አሉ፤ ኅብረተሰቡ ባለው አደረጃጀት መሠረት የማዳፈን ሥራ ይሰራሉ፤ ያቆሩ ዉኃዎችን ያፋስሳሉ፤ እነዚህ እነዚህ ሥራዎች በታች የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው።»

Mücke Malaria
ምስል picture-alliance/dpa/P. Pleul

የወባ በሽታ መስፋፊያ ሳይደርስ ኅብረተሰቡ እነዚህን መሠል የመከላከል ተግባራት ቢከናወኑም ድንገት በወባ የመያዝ አጋጣሚ ሊከሰት ስለሚችልም ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ምርመራም ሆነ ሕክምናውን በነፃ ማግኘት እንደሚችል ነው አቶ መብርሃቶም የገለፁት።

«የወባ ህክምና ምርመራ በሁሉም የመንግሥት የጤና ተቋማት በነፃ ነው የሚሰጠው። ይኼም በዋናነት አገልግሎት የሚሰጠው በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካኝነት በየቀበሌው አገልግሎቱን ያገኛሉ። ስለዚህ ማንኛውም የኅብረተሰብ አካል በ24 ሰዓት ውስጥ ትኩሳት ሲሰማው ወደ መንግሥት ጤና ተቋማት በመምጣት ምርመራ ማድረግ ይችላል በነፃ። ወባ ከተገኘበትም መድኃኒት በነፃ ያገኛል ማለት ነው።»

የብሔራዊ የወባ መርሃግብር አስተባባሪው እንደሚሉት በተለይ ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የክትትልና የበሽና ቅኝት ሥራ በየሳምንቱ ይሠራል። በዚህ መሠረትም  በየአካባቢው የጎደለው መድኃኒትም ሆነ የመመርመሪያ መሣሪያ እየታየ አስፈላጊው ይከናወናል።

ቀደም ሲል ወባ በሽታ ከሚያጠቃቸው ሃገራት አንዷ መሆኗ በሚነገርላት ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት በወባ ሰበብ የሚሞተው ሰው ቁጥር ከሰማንያ በመቶ በላይ መቀነሱን የሚናገሩት አቶ መብርሃቶም የታማሚዎችም ቁጥር እንዲሁ በ50 በመቶ ገደማ ዝቅ ማለቱን ያስረዳሉ። ይህ አያያዝም ወባን ከመከላከል የማጥፋቱ ስልት እንዲነደፍ ምክንያት ሆኗል።

Symbolbild Malaria Medikamente Mülltonne
ምስል picture-alliance/dpa

«በሀገር አቀፍ ደረጃ ወባ ለመጨረሻ ጊዜ ወረርሽኝ ተነሳ ተብሎ የነበረው በ2003 እና 2004ዓ,ም በፈረንጆቹ ነው። ስለዚህ ላለፉት 15 ዓመታት ወባ እንደወረርሽኝ በሀገር ደረጃ አልተነሳም ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ መነሻ በማድረግ አሁን የስልት ወይም የስትራቴጂ ለውጥ በማድረግ ወደ ወባ ማጥፋት ወይም ማስወገድ የሚል ስትራቴጂ ቀርፀን ወደ 2009 ገብተናል የተወሰኑ 239 ወረዳዎች በ2020 እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር የወባ ማጥፋት ሥራ በተግባር የሚጀመርባቸው ወረዳዎች ናቸው 239ኙ ወረዳዎች ማለት ነው።»

አቶ መብርሃቶም የገለፁት «የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻሉ፣ ወባን ለመከላከል የሚደረጉት የመድኃኒት ርጭትም ሆነ የአጎበር ማዳረሱ ሥራ ተጠናክሮ በመሠራቱ፤ ወባ በወረርሽኝ መልክ የሚነሳበት አጋጣሚ በመቅረቱ በሽታውን ፈፅሞ ማጥፋ ይቻላል የሚለው ስልት መነደፉን፤ በጎርጎሪዮሳዊው 2030ዓ,ም ወባን ለማጥፋት መታቀዱን» ይመለከታል። የተመድ የነደፈው ዘላቂነት ያለው የልማት ዕቅድም ይህን ጊዜ የወባ በሽታን ከመላው ዓለም ለማጥፋት በግብነት ይዞታል።

Simbabwe Moskitozelt
ምስል DW/P. Musvanh

ኢትዮጵያ ወደ 545 የሚደርሱ ወባ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ቢኖሩባትም ከቦታ ቦታ የወባ ስርጭቱ እንደሚለያይ ያስረዱት አቶ መብርሃቶም፤ ጋምቤላ ፣ ቤንሻንጉል፤ ወደ ሰሜን ጎንደር እና ምዕራብ ትግራይ አካባቢ የሚገኙት ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው መሆናቸውም ጠቅሰዋል።  ባለፈው ዓመትም ወደእነዚህ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን ከወባ ትንኝ መከላከል የሚያስችሉ አጎበሮች በአግባቡ መዳረሳቸውንም እንዲሁ። አሁን ወባን ለማጥፋት በታቀደው ስልት ውስጥ የተካተቱት 239ኙ ወረዳዎች መካከለኛ እና ዝቅተኛ የወባ ስርጭት እንዳለባቸውም ተናግረዋል። እነዚህ ወረዳዎች ላይ ከሦስት ዓመታት በኋላ የሚጀመረው ወባን የማጥፋት ሥራ ሲጠናቀቅ ደግሞ ተጨማሪ 200 ወረዳዎችን በማከል የወባ ስርጭቱ ቀስ በቀስ ከመላ ሀገሪቱ እስከ 2030 በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር እንዲጠፋ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሠራም ዘርዝረዋል። ይህንን እውን ለማድረግም የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ጨምሮ ኅብረተሰቡን በአንድ አይነት ሃሳብ ሆኖ የማነቃነቅ ሥራ ወሳኝ መሆኑን፤ ባለድርሻ አካላት የሆኑ የሀገር እና ዓለም አቀፍ ለጋሾችም ሚና ዋና እንደሆነም አመልክተዋል።

የዓለምየጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም ወባ በመላው ዓለም 445 ሺህ ሰው ፈጅቷል። በዚሁ ዓመትም በወባ የተያዙት ሰዎች ከ200 ሚሊየን ይበልጣሉ። እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ከሆነ ኢትዮጵያ ወባን በመቆጣጠር ብሎም ለማጥፋት በምታደርገው ጥረት የታዩት ውጤቶች ዘላቂነት ያላቸው የልማት ግቦች በሚል የተመድ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት አዎንታዊ ጎዳና ላይ መሆኗን ያመለክታል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ