1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማስረሻ አስተዋለ

ዓርብ፣ ጥቅምት 17 2010

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን  «ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት በነፃ አደርሳለሁ» የሚለው ማስረሻ አስተዋለ ነው። ይኸው መልካም ስራው ከሚኖርባት የጎንደር ከተማ አልፎ በተለያዩ ከተሞችም እየተወደሰለት ይገኛል።

https://p.dw.com/p/2mYFx
Äthiopien Gonder - Masresha Astewale hilft Frauen die die Wehen bekommen haben und fährt sie umsonst ins Krankenhaus
ማስረሻ አስተዋለምስል M. Astewale

በርካታ እናቶች ምጥ የሚይዛቸው ሊነጋጋ ሲል ወይም ሌሊት ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ታድያ  ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያን ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ወላዷን ሆስፒታል የሚያደርስ መኪና ከጎረቤት ወይም ከአካባቢው ፍለጋ ይገባል። በጎንደር ከተማ የሚኖሩ እና ማስረሻ ለወላዶች ይሰጠዋል ስለተባለው ነፃ አገልግሎት የሰሙ ደግሞ ወዲያው ወደእሱ ስልክ ይደውላሉ።

ማስረሻ አስተዋለ ጎንደር ከተማ ውስጥ «ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋም በነፃ የማድረስ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራተኛ ወሩ ነው።  ይህንንም የሚያደርገው ባለቤቱ ምጥ በያዛት ጊዜ የነበራትን ስቃይ በዓይኑ ስላየ ነው። ማስረሻ እስካሁን አምስት ወላዶችን ወደሆስፒታል በማድረስ ተባብሯል። ይህንንም አገልግሎት የሚሰጠው በተፈለገበት በማንኛውም ሰዓት ነው። ሌሊት እና ቀን ላይ የደወሉለት አሉ።

ማስረሻ በባጃጅ ሰዎችን በማጓጓዝ ነው የሚተዳደረው። ከማያውቀው ቁጥር የስልክ ጥሪ ሲደርሰው፣ ደዋዩ ርዳታ ፈላጊ ሊሆን ስለሚችል፣ ባጃጁን አንድ ዳር አቁሞ በተቻለው መጠን ስልኩን ለመመለስ ይሞክራል። « ያሳፈርኳቸውን ሰዎችም አስወርጄ ወደ ወላዳ መሄድ የነበረብኝ ጊዜ ነበር።» ይላል ማስረሻ

የ 22 ዓመቷ ፍትፍቴ ጌታሁን ፤ ማስረሻ በዚህ አመት ከተባበራቸው ወላዶች አንዷ ናት። «ፍትፍቴ የማስረሻ ርዳታ በአንድ ቀን አልተጠናቀቀም ትላለች። ከአንድ ሳምንት በኋላ ለነበራት የሆስፒታል ቀጠሮም ወስዶ በማድረስ ወጣቷን ተባብሯታል።

Äthiopien Gonder - Masresha Astewale hilft Frauen die die Wehen bekommen haben und fährt sie umsonst ins Krankenhaus
ምስል M. Astewale

የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት /UNICEF/ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ባለፈው የጎርጎሮሲያዊው 2016 ዓም በአማካይ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 15 000 ያህል ህፃናት በየዕለቱ ሞተዋል። አብዛኞችን ህፃናት ለሞት የዳረገው ሊድን የሚችል በሽታ ወይም የተመጣጠነ ምግብ ያለማግኘት ቢሆንም፣ በወሊድ ጊዜም በሚያጋጥሙ ችግሮች የሚሞቱት ህፃናትም ብዙ መሆናቸውን አመልክቷል። ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በርካታ ህፃናት ከሞቱባቸው አምስት ሀገራት አንዷ እንደሆነች UNICEF ገልጿል። ዶክተር አኒሳ በፍቃዱ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው። እናቶች ምጥ ሲይዛቸው ወዲያውኑ ሳያመነቱ ወደጤና ተቋም መሄድ አለባቸው ይላሉ።

ጥሩዬ ቦጋለ ነፍሰ ጡር እያለች ማስረሻ ባጃጁ ላይ ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋም በነፃ እንደሚያደርስ የለጠፈውን ስላየች ልትወልድ ስትል ወደእሱ ነበር የደወለችው። ይሁንና እንደተመኘችው መጨረሻው አላማረም። « ብዙም አላመመኝም ነበር። ባውቅ ኖሮ በፍጥነት እደውልለት ነበር። » ጥሩዬ ሆስፒታል ሳትደርስ ነበር ልጇን የወለደችው። በመጨረሻ ሰዓት ልጇ ባለመትረፉ ጥሩዬ ብታዝንም የሷም ህይወት አደጋ ላይ በነበረበት ሰዓት ማስረሻ መድረሱ እና እሷን ወደ ሀኪም ቤት በማድረሱ እጅግ ደስተኛ ናት።

ማስረሻ ባጃጅ ስለሚነዳና አካባቢውን ስለሚያውቅም የጠሩት ሰዎች ጋር በተቻለው ፍጥነት ደርሶ ወላጆቹን ወደ ጤና ተቋም ማድረስ ይሞክራል። ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነም ያውቃል። ይህንንም በፍቃደኝነት የሚያደርገው ስራ ነው። ከሰዎችም የሚያገኘው ምስጋና ውሳኔው ትክክል እንደነበረና ይበልጥ እንዲተባበር አድርጎታል። ማስረሻ «ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋም በነፃ አደርሳለሁ» የሚለው መልዕክቱን እና ስልክ ቁጥሩን ባጃጁ ላይ ለጥፎ በከተማይቱ ስራውን ሲሰራ ካለምክንያትም የሚደውሉለት ሰዎች አልጠፉም። « ያው እውነት የማይመስላቸው ሰዎች አሉ። ለማረጋገጥ ብለው ይመስለኛል የሚደውሉት።»

በማስረሻ በጎ ስራ የተረዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ታሪኩን የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያውያንም አወድሰውታል። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። በአብዛኛው ሲታይ  ሀኪም ቤት መድረስ ያለባቸውን ሰዎች በፍጥነት ወደ ሀኪም ቤት የሚያደርስ አምቡላንስ ባለመኖሩ ነው።  ይህንንም ችግር ዶክተር አኒሳ በሚሰሩበት ሆስፒታል ታዝበዋል። « እኔ በምመራበት ተቋም አብዛኞቹ በአምቦላንስ አይመጡት። እጅግ ውስን የሆኑ አምቦላንሶች ነው ያሉት። ጉዳዩ ትኩረት የሚሻ ነው።» ስለሆነም፣ ማስረሻ ማንኛውም ሰው በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ የበኩሉን አስተዋፅዎ እንዲያደርግ ይመክራል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ