ከ200 በላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከየመን ተመለሱ
ሐሙስ፣ ኅዳር 20 2011ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ የመን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን መመለስ መጀመሩን አስታዉቆ ነበር። ድርጅቱ ከየመን በቃል አቀባዩ በሚስተር ሳባ አልሙላሚ በኩል እንደገለፀዉ ፤ኢትዮጵያዉያኑን ስደተኞች በአዉሮፕላን ከሰንዓ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ነበር ያመሩት።በዚህም መሰረት ከ200 በላይ ኢትዮጵያዉያን አዲስ አበባ መግባታቸዉን የIOMኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ሰይፈ ስላሴ ለDW ገልፀዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ቀናትም ድርጅቱ ተመላሽ ስደተኞቹን ከአዲስ አበባ ወደየ ትዉልድ ቀያቸዉ እንደሚያጓጓዝ ገልፀዋል። ከተመላሽ ስደተኞቹ መካከል ህፃናትና ሴቶች የሚገኙ ሲሆን ከመካከላቸው የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉና የጤና ዕክል የገጠማቸዉ እንዳሉ አቶ አለማየሁ ገልፀዋል።ከህፃናቱ መካከልም ከቤተሰብ ጋር ተለያይተዉ የሚገኙ በመኖራቸዉ ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር እስኪገናኙ ድረስ በድርጅቱ ማቆያ ጣቢያ እንደሚሰነብቱ አስረድተዋል።
አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሳዉዲ አረቢያ ለመሻገር በህገ ወጥ መንገድ በሱማሌ ላንድ ቦሳሶ እንዲሁም በጅቡቲ በኩል ወደ የመን የገቡ ሲሆን በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ዝርፊያ በድብደባና መንገላታት የደረሰባቸዉ ናቸዉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬዉ ዕለት ባወጣዉ መግለጫም ከዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር ባደረገዉ ትብብር በጦርነትና በረሀብ በምትታመሰዉ የመንበ ህይወታቸዉ ለአደጋ የተጋለጠ በህግ ከለላ ስር የነበሩ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጭምር ባለፉት ሁለት ቀናት በሰላም ወደ ሀገራቸዉ ገብተዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ጋር በመሆንም «ዜጎቻችን በሰላም ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ እንሰራለን »ሲልም በመግለጫዉ አመልክቷል።ለዚህም አስፈላጊዉን ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM እንዳስታወቀው ከትናንት ወዲያ የጀመረዉ ስደተኞቹን በፈቃዳቸዉ የመመለስ ዘመቻ እስከ ጎርጎሮሳዉያኑ ታህሳስ 30/2018 ድረስ ይቀጥላል። በዚህ ዘመቻ ወደ 600 የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ከየመን ወደ ሀገራቸዉ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ